
አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዛሬ ብራሰልስ ላይ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት ሀገራት የብሪታንያን ከህብረቱ ለመልቀቅ ያቀረበችውን ረቂቅ ስምምነት መቀበላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከህብረቱ ለመለቀቅ ረቂቅ የፍቺ ስምምነት ለካቢኔያቸው አቅርበው ተቀባይነት ማግኘታቸው የሚታወስ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ነው ዛሬ ብራሰልስ ላይ ሀገራቱ በስምምነቱ ዙሪያ ውሳኔያቸውን ያሰሙት ተብሏል።
ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ የደረሱት ከ18 ወራት ውጣ ውረድ በኋላ ሲሆን፥ ከህብረቱ ሀገራት መካከል ስፔን የጅብርላተር ጉዳይ እልባት አላገኘም በማለት ብሪታንያ ከህብረቱ ጋር ያደረገችውን ስምምነት እንዳልተቀበለችው ተገልጿል፡፡
ዛሬ በህብረቱ ተቀባይነት ያገኘው የስምምነት ፍቺ ከ10 ቀናት በኋላ ብሪታንያ ፓርላማ ቀርቦ ድምጽ ይሰጥበታል ተብሏል፡፡
ሆኖም ሌበር ፓርቲን ጨምሮ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሜይ ላቀረቡት ስምምነት ድምጻቸውን እንደሚነፍጉ ከወዲሁ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ለህዝቡ ይፋዊ የደብዳቤ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ከህብረቱ ጋር የደረሱት ስምምነት የብሪታንያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብሪታንያ 2016 ባካሄደችው ድምጸ ውሳኔ መሰረት መጋቢት 20 ፍቺው ተጠናቆ ከህብረቱ ትወጣለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፦ቢቢሲ
በአብርሃም ፈቀደ