በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባሉ አንዳንድ የዞን ም/ቤቶች የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች ከደኢህዴን ጉባኤ አቅጣጫ ውጭ መሆናቸውን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ገለፀ፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ መምከሩን የማዕከላዊ ኮሚቴው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናግረዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደርና አስተዳደራዊ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም ሂደት አንዱ በዝርዝር የታየ ጉዳይ መሆኑን ኃላፊው ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የውሳኔዎቹ የትግበራ ሂደት ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ ሞገስ አስተዳደራዊ አደረጃጀትን በተመለከተ ዝርዝር ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝና ጥናቱ ሲጠናቀቅ በጉባኤው የፀደቁ አዳዲስ የመዋቅር አደረጃጀቶች በክልሉ ም/ቤት ህጋዊ ማዕቀፍ ኖሯቸው ይቋቋማሉ ብለዋል፡፡

ምንጭ – EBC