በትግራይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በራያ በርካታ ወገኖች በሕወሃት ክልል ታጣቂዎች ተገድለዋል። ሰልፍ ለምን ወጣችሁ ተብለው።
አሁን ደግሞ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ሕወሃትን በመደገፍ፣ ሰው በላዉን የቀድሞ መሪ የመለስ ዜናዊን ፎቶ በማንገብ፣ የተለያዩ መፈክሮችን በማወለብለን፣ የትግራይ ሕዝብ ድምጹን አሰማ እያሉ ነው። ራያ ትግሬ ነው፣ ወልቃይት ትግሬ ነው የሚሉ መፈክሮችም ነበሩ። እንግዲህ ሰልፍ ለማን እንደሚፈቀድ፣ ለማን እንደሚከለከል፣ ማን ሲሰለፍ እንዲሚገደልና እንደሚታሰር፣ ማን ደግሞ ከፍተኛ የትግራይ ክልል የሚዲያ ሽፋን እንደሚያገኝ በግልጽ እያየን ነው።
ሰልፎቹን ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች የትግራይን ሕዝብን እየተቹ ነው። ከሌቦችና ነፈሰ ገዳዮች ጋር እየተባበረ ነው በሚል። ነገር ግን እነዚህ ወገኖች ያልተረዱት ነገር ቢኖር በሕዝቡ አንገት ላይ የተጠመደው ብረት በጣም የከፋ መሆኑን ነው።
ደርግ ሲመጣ ልጅ ነበርኩ። የአምስት አመት ልጅ። ትንሽ አደግ ስል ግን አስታወሳለሁ ወላጆቼ፣ በተለያዩ ሰልፎች ጠዋት ተነስተው ሰልፍ ሲወጡ። ሰልፍ መውጣት ግዴታ ነበር። ሰልፍ ካልወጡ የሚከተለውን ሰው ስለሚያውቅ ማንም አይቀርም ነበር። ያ ሁሉ ሕዝብ መስቀል አደባባይን ሲያጥለቀልቀቅ፣ ደርግን ደግፎ ነበር ብሎ የሚናገር ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም።
ታዲያ ገዳዮች፣ ጨካኞች፣ ግፈኞች ፣ የታጠቁ ሃይላት፣ በፈለጉ ጊዜ መሬት ላይ ሊደፉት እንደሚችሉ እያወቀ፣ ለመብቱ፣ ለነጻነቱ እንዲታገል፣ በቃኝ የሕወሃት አገዛዝ ብሎ እንዲወጣ የሚያደራጁት ድርጅቶች በሌሉበት፣ የትግራይ ህዝብ የሕወሃትን ጥሪ ተቀብሎ ሰልፍ ለምን ወጣ ብሎ ማለት አርቆ አለማሰብ ነው።
የፌዴራል መንግስት የትግራይን ሕዝብ ከሕወሃት መታደግ አለበት የሚል ጽሁፍ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አቅርቤ ነበር። በትግራይ የተደረጉ ሰልፎች ለጽሁፌ ተጨማሪ ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው። ምን ያህል የትግራይ ሕዝብ በፍርሃት፣ በሰቇቃ፣ በሽብር ውስጥ እንዳለ በግልጽ የሚያመላካት ነው።
ይሄን ሁሉ ድራማ ሕወሃቶች የሚያደርጉት አስበዉበት ነው። በጥናት ነው። ሌላው ማህበረሰብ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻ እንዲኖረው አድርገው፣ “እኛ ከሌለን ሌላ ቦታ መሄጃ የለህም፤ ሌሎች ይጠሉሃል፣ ያንተን ሕልው ከኛ ሕልዉና ጋር የተቆራኘ ነው” የሚለውን በሕዝቡ አይምሮ ውስጥ ለማስረጽ ነው። የትግራይ ህዝብ ቢጠላቸውም፣ እንዳይተፋቸው፣ እንደ መዥገር በርሱ ላይ ተጣብቀውና ተሸሽገው ለመኖር ፣ ደሙንም ለመምጠጥ ነው።
እኛም ሕወሃትንና የትግራይን ሕዝብ አንድ አድርገን በማየት፣ የአሁኖቹን ሰለፎችና ድራማዎች የምር፣ የሕዝቡን ስሜትን የሚያንጸባርቁ አድርገን በማሰብ፣ ጥላቻ በውስጣችን እንዲያድግ ካደረገን፣ ለሕወሃት ገጸበረከቶችን እየሰጠን መሆናችንን ማሰብ አለብን።
ከመቼውም ጊዜ በላይ ለትግራይ ሕዝብ አጋርነታችንን በማሳየት፣ ከሕዝቡ ጎን በመቆም፣ የፌዴራል መንግስት የትግራይን ሕዝብ ከሕወሃት እንዲታደግ ተጨባጭ እንቅስቃሴዎችን መዉሰድ እንዲጀምር ግፊት ማድረግ አለብን።
የፌዴራል መንግስቱ ሕወሃትና ከፌዴራል መንግስት ማባረር፣ የሕወሃት አመራሮችን ንብረትና የባንክ አካዉንት በመዝጋት ሕወሃት ለአገሪቷ ሕግ እንዲገዛ በሕዝቡ አንገት ላይ የጫነውን ቀንበር እንዲሰብር ማስገደድ አስፈላጊ ነው። እነዚህ እርምጃዎችም ሕወሃቶች ወደ ሕሊናቸው እንዲመለሱ ካላደረገ፣ የመከላከያ ሰራዊት ህዝብን ከወንበዴዎች ነጻ ለማወጣጥ መንቀሳቀስ መጀመር አለበት። የዶ/ር አብይ አስተዳደር መደመር፣ ፍቅር፣ ንግግር የማይገባቸው፣ የአስተሳሰብ ድሃ የሆኑ ቡድኖች እንዳሉ መገንዘባቸው አስፈላጊ መሰለኝ።