ህዳር 13ቀን 2011ዓም ክህደት መረን ለቀቀ!
የይሥሙላ ምርጫ በማድረግና በማጭበረበር በአሸናፊነት መውጣት የለመዱት፣ ዛሬም ድረስ የጦርም ሆነ የኢኮኖሚ የበላይነት ያላቸው የትግሬ ነፃ አውጭ ግንባር (ትነግ) ወያኔዎች፣ እንዴት በቀላሉ ዶክተር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ ፈንቅሎ ሊወጣባቸው ቻለ? ብዙዎቻችን ተገርመን ይሆናል።
ዕውነታው ግን እንዲህ ነው። እንደሚታወቀው የቅንጅትን ምርጫ ተከትሎ፣ ምንም እንኳን ቅንጅት ባያሥተባብረውም፣ ሰኔ አንድ (1) ቀን 1997 ዓም የአዲስ አበባ ሕዝብ በራሱ አነሳሽነት የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ አደባባይ ሲወጣ በከባድ መሣሪያ አጋዚ የሚሉት ጦር ብዙ ወገኖች ገደለ።
በዚህ ግድያ ምክንያት፣ የእነመለስን መንግሥት ትነግ|ኢሕአዴግን ወደሥልጣን ያመጡት፣ ሥልጣንም ተቆናጦ እና ተጠናክሮ እንዲኖር ምክርና እርዳታ ያደረጉለትና እንዳይወድቅ ከጎኑ የነበሩትና ያሉት የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት፣ ቅሬታቸውን “ሀ” ብለው ሲገልጡ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተብዬው ጌቶቹን ያለመቀበል አዝማሚያ ማሳዬት ጀመረ።
በነገራችን ላይ፣ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ የውጭ ኃይላት ጣልቃ ገብነት ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው በኢሕአዴግ እንደሆነ ማንም አይሥተውም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኃያላኑ! ቀደም ሲል በተለያዩ ሀገራት የነበሩ መሪዎች “አሻፈረኝ” ሲሉ፣ በተለመደው የመንታ መንገድ አሠራራቸው ሲቀያይሩ እንደኖሩት ሁሉ፣ በአንድ በኩል የትነግን|ኢሕአዴግን ሊጠግኑት ሞክረዋል፣እንዲታረምም ብዙ ጥረት አድርገዋል።
ነገር ግን ይህ ልዩነታቸው እየሰፋ መጥቶ፣ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ፣ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ትነግን|ኢሕአዴግን ለነቀነቀው አመፅ፣ መንግሥት ተብዬው የሰጠው ምላሽ ግድያና እሥራት ከመሆንም አልፎ ጊዜያዊ አዋጅ በተከታታይ ሁለት ጊዜ መደረጉን አሥመልክቶ ኃያላኑ ተቃውሟቸውን በግልጭ ሲያደርጉ ነው።
በሌላ በኩል ኃያላኑ ከተቃዋሚዎች ጀምሮ በዚያው በራሱ በመንግሥት አካባቢ ካሉት ሰዎችም ጭምር በማነጋገር፣ በሥለላ መዋቅሮቻቸው አማካይነት ውስጥ ውስጡን ሲሰሩበት 13ዓመት አሥቆጥረል።
በመጨረሻም ለንደን ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት ተወካይ ተስፋዬ ዲንቃን፣ ሻዕቢያን፣ ትነግንና ኦነግን የአሜሪካው ኸርማን ኮህን ሰብስቦ ሥልጣን ለነፃ አውጭዎቹ በ1983 ዓም እንዳሥረከው ሁሉ፣ ዛሬም በተመሳሳይ ጦር ይዞ የኃያላኑን ፍላጎት የሚያሟላ ኃይል ከኢሕአዴግ ውጭ ሳይሆን ውስጥ ብቻ እንዳለ ኃያላኑ ራሳቸውን አሳመኑ።
ቀጥሎም ኃያላኑ! በኢሕአዴግ ውስጥ ዘመቻቸውን እንዳጠናቀቁ፣ የትነግን ሰዎች ከቁጥጥር በወጣ አመፅ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ፣አመራሩን ለሚገባው ወገን እንዲሰጡና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚል ቀጭን ተዕዛዝ እንዳሥተላለፉላቸው ዕሙን ነው።አቢይም አሽንፎ ሳይሆን በሌላ ኃይል ግፊት እንደመጣ የሚያውቅ ያውቀዋል።
ሌሎች ጦር የያዙ የተለያዩ ድርጅቶች ኃያላኑ ዓይን ገብተው ቢሆን ኖሮ በ1983 ዓም ለንደን ላይ እንደተደረገው “ተስብስበው ይህን አደረጉ፣ ሥልጣን ሊወስዱ ነው” ይባል ነበር።
ይኸኛው ግን በዚያው በኢሕአዴግ ውስጥ ሥለሆነ በውስጥ ለውስጥ አልቋል። ሌላው በውጭ ከነበሩትም ድርጅቶች መካከል ነጮቹ ያመኑባቸውን በሥቴት ዲፓርትሜንት ወጣ ገባ በማለት እንዲያልቅ አሥደርገዋል። እነለማ፣ እነገዱ፣ የትግሬ መሪዎችም ቀድመው አውቀውታል።
ይህ በውስጥ ለውስጥ ተሰርቶ ያለቀለት የዲፕሎማሲ ሥራ ነው።
ሌላው አመላካች ነገር ደግሞ በ1983ዓም ለንደን ላይ አጥምቆ አውሬ የላከብን ኸርማን ኮህን ቀደም ሲል በኢሳት ሲጠየቅ የትነግ|ኢሕአዴግ ሰዎች የገቡትን ቃል እንዳፈረሱ ተናግሯል። ለሁለተኛ ጊዜ ሲጠየቅ ሥልጣን ማን ቢይዝ ይሻላል የሚል ዓይነት ጥያቄ ተሰነዘረለት። ኸርማን ኮህን የሠጠው መልስ ግን “ኦሮሞ ቢመራ ወይም ቢሆን ይሻላል” በማለት በድፍረት ተናግሯል። እናም የአቢይ መምጣት ድንገት እንዳልሆነ ማወቅ ተገቢ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ኢሳያስንም ኃያላኑ አሥቀድመው እንዳናገሩት ግልፅ ነው።
በዚያን ወቅት የትግሬ ነፃ አውጭ ግንባር(ትነግ)! የጌቶቹ የነጮቹ ተዕዛዝ ባይሆን ኖሮ ደህንነቱም፣ጦሩም፣መሳሪያውም በእጁ ሥለሆነ፣አቢይንም ሆነ ለማን ለማስወገድም፣ለማሰርም ሆነ ለመግደል ደቂቃ አይፈጅበትም ነበር።የሚያዳግተው መሥሎ ቢታዬው ኖሮ እንኳን እሥከመጨረሻው አዲስ አበባ ላይ ጦርነት አውጆ የሞት የሽረት ትግል ያደርግ ነበር።
ምንም ተባለ ምን ትነግ በሌላ ሰው መመራትን ባይወደውምና ባይዋጥለትም፣ አዲስ አበባ ላይ የጌቶቹን የነጮቹን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከመሄድ ውጭ አማራጭ አልነበረውም። አቢይም ብዙውን ጊዜ ተዝናንቶ የሚሄደው በዚህ ምክንያት ነው።
አዲስ አበባ ላይ ሊገድሉት ነበር የተባሉት በቀጥታ ትነጎች አለመሆናቸውና የራሱ ኦሮሞዎች እንደሆኑ ታውቋል። በዚህ ጊዜ የአሜሪካም የሥለላ ድርጅት ገብቶ አጣርቶ ሄዷል።
በነገራችን ላይ አቢይ ከኦሮሞዎች ብዙ ደጋፊ የለውም። እሱን ከኋላ ሆነው የሚገፉት አክራሪ የኦሮሞ ድርጅቶች አቢይን ተጠቅመው ለጊዜውም ቢሆን የሚፈልጉትን ነገር እንዲሠራላቸው ካልሆነ በሥተቀር ደጋፊዎቹ አይደሉም። ይህም በአቢይ የድጋፍ ሰልፍ ጊዜ ግልፅ ሆኗል።
በቡራዩ ሕዝብ የመግደልና የማፈናቀል ወንጀል የሠሩትም ዘረኛ የኦሮሞ ቄሮዎች ከአቢይ በላይ ሥልጣን እንዳላቸው በገሀድ ታይቷል።
የሚነገሩን ነገሮች ዕውነት ከሆኑና ሕዝቡ እምነት እንዲጥል ከተፈለገ፣ “ግልፅነት! ግልፅነት” እያለ የለፈፈው የአቢይ አሥተዳደር፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ያለወንጀላቸው ወንጀለኛ አድርገው አቅርበው በማጋለጥ፣ ሲታሰሩም ሲፈቱም፣በሜዲያ ጭምር ሲያሳዩን፣
(1ኛ) ቡራዩ ላይ ወንጀል ሠሩ የተባሉትን ኦሮሞዎች!ታሰሩ ወዘተ የሚለው ቅብጥርጥርም እኛኑ ለማሳመን ካልሆነ በሥተቀር ይታሰሩ አይታሠሩ ያየነው ነገር የለም። እዚህ ላይ ግልፅነት አይሠራም??
እንደውም የእነሱን ወንጀል ለመሸፈን ሲባል ነው የአዲስ አበባ ወጣቶችን ወንጀለኛ አድርጎ ለማቅረብ የተጣረው። ይህ ቅጥፈት መቆም አለበት።
(2ኛ) አሁን በቅርቡም ወታደሮች ቤተ መንግሥቱ ድረስ መሄዳቸውን አሥመልክቶ “ልገደል ነበር”ብሎ አቢይ የተናገረውና ወንጀለኞቹ እንደተያዙ የተናገረውም አሳማኝ አይደለም። እነሱም ይታሰሩ አይታሠሩ ያየነው ነገር የለም። እዚህ ላይ ግልፅነት አይሠራም??
ይህንን የፈጠረው ዝናውን ከፍ ለማድረግና “ጎበዙ መሪ” በሚል ደጋፊዎችን ለማበራከት ነው እና የነፍሰ ገዳዩ ድርጅት የኢሕአዴግ ምርጫ ሲመጣ በግርግር እንድንመርጠውና እንደገና ሠቆቃችንን በትግሬዎችና በኦሮሞ አክራሪ ዎች ሊያራዝምብን ሥለፈለገ ነው።
ዛሬ እንደሚታየው ቀደም ሲል የትግሬ ዘረኞች በብቸኝነት ይዘውት የነበረውን የጭቆናውንና የቆራጭ ፈላጭነቱን መሣሪያ፣ ዛሬ ከኦሮሞ ዘረኞች ጋር በመጋራት በሥውርና በግልፅ እያደረጉት ነው። ለምሳሌ ኦሮሞዎች በአዲስ አበባ ኑዋሪዎች ላይ ያደረጉትን ግድያና እሥራት ልብ ይሏል።
ታግሎ ህልውናንና ማንነትን ማሥከበር የተፈጥሮ ህግ ነው!
እሥከዳር በላቸው