በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ እስኪ ዛሬ ትንሽ ልፈላሰፍባቹህ፡፡

ምን እንደሚገርመኝ ታውቃላቹህ?

ሰዎች የሚያሳማ ተግባር ይፈጽሙና ሲያበቁ ተግባራቸውን የሚያወሩባቸውን ሰዎች ሐሜተኞች!” ሲሉ፣ በሰዎች ዘንድ እንዲጠሉ የሚያደርጋቸውን ተግባር ይፈጽሙና ሲያበቁ ለክፉ ተግባራቸው የጥላቻ ንግግር ምላሽ ሲሰጣቸሁ የጥላቻ ንግግር ተሰነዘረብኝ!” እያሉ ኡኡ የሚሉ ሰዎች በጣም ይገርሙኛል፡፡

የጥላቻ ንግግር (hate speech) ማለት ምን ማለት ነው?

ይሄ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቂና ትክክለኛ ግንዛቤ የተያዘበት ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ እንዲህ የሆነበትም የራሱ ምክንያት አለው ብየ አምናለሁ፡፡ ወደኋላ እገልጸዋለሁ፡፡ ለማንኛውም የጥላቻ ንግግር ማለት አንድ አካል በመበደሉ በማጥፋቱ ምክንያት በተበደሉ አካላት የጥፋት ተግባሩና የፈጸመው በደሉ እየተጠቀሰ የሚሰነዘርበት የማንቋሸሽ፣ ዝቅ ማድድረግ፣ የማዋረድ ንግግር ማለት ነው፡፡ አንድ አካል ነውር ወይም የሚጠላ መገለጫ ሲኖርበትም ለጥላቻ ንግግር ሊዳረግ ይችላል፡፡ አንድ አካል ባላጠፋበት፣ ባልበደለበትና የሚያስነቅፍ ነገር የሌለበት በሆነበት ሁኔታ ሊሰነዘርበት የሚችል የጥላቻ ንግግር አይኖርም፡፡ ይሄንን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

የጥላቻ ንግግር (hate speech) ከማኅበረሰባዊ የቅጣት ዓይነቶች አንዱና ከተፈጥሯዊ ስሜት የሚመነጭ ጤናማ አጸፋዊ ምላሽም ነው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ጥፋትና በደል የፈጸመውን አባሉን የሚቀጣበት የማኅበረሰባዊ የቅጣት ዓይነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ማግለል፣ መንፈግ፣ ፊት መንሳት የመሳሰሉት፡፡ የተፈጸመው ጥፋት ወይም ስሕተት ከበድ ያለ ከሆነም እንደ እርግማን ያለ ከበድ ያለ ማኅበረሰባዊ ቅጣት ይሰነዘርበታል፡፡ መሃከል ላይ ላለ ጥፋትና ስሕተት ደግሞ ማኅበረሰቦች እንደየባሕላቸው በተለያየ መንገድ የጥላቻ ንግግር እንዲሰነዘርበት በማድረግ ይቀጣሉ፡፡

እንግዲህ መያዝ ያለበት ነጥብ ጥፋት፣ ስሕተት፣ በደል፣ ጥቃት፣ ግፍ ሳይፈጸም የጥላቻ ንግግር ሊከተል አለመቻሉ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር ለበዳይ አካል ማኅበራዊ ቅጣት የመሆኑን ያህል ለተበዳይ አካል ደግሞ ማኅበራዊ ፍትሕ ሆኖ እንደ የሥነልቡና ሕክምናና ካሳ በመሆን ያገለግላል፡፡

የጥላቻ ንግግር እንደ ቅጣትነቱ የበደለውን አካልም ከተመሳሳይ ጥፋትና ስሕተት እንዲቆጠብ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ሰው በሚበደልበት ጊዜ በደሉን በመናገር፣ በማልቀስ፣ በመተንፈስ መግለጽ የማይችል ቢሆን በምድራችን ላይ አንድም ጤነኛ ሰው ሊኖር ባልቻለ ነበር፡፡ የጥላቻ ንግግር ስድብንም ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ ሌባን ሌባ በማለት፣ ነፍሰገዳይን ነፍሰገዳይ በማለት…. አጥፊን በዳይን አካል ማሸማቀቅን ይጨምራል፡፡

የጥላቻ ንግግር ምክንያታዊ ከሆነና ለተበደለው አካልም ማኅበራዊ ፍትሕ (Social justice) ከሆነ ለምንድን ነው ታዲያ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሚከለከለው?” የሚል ጥያቄ መነሣቱ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፦ ሥልጣን በበዳይ አካላት እጅ ሲሆን እነኝህ በዳይ አካላት መበደላቸው ሳያንስ ማኅበራዊ ቅጣት እንዳያገኛቸው፣ እንዳይሰነዘርባቸው፣ ተበዳዮቹ በደላቸውን ተንፍሰው፣ ገልጸው፣ አውጥተው የበዳይን ማንነት እንዳይገልጹ ሥልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም ለማፈን የሚጠቀሙት ኢፍትሐዊ የአፈና እርምጃ ስለሚወስዱ ነው የጥላቻን ንግግር ወንጀል አድርገው የሚፈርጁት፡፡

እነኝህ አካላት ከበደሉ ካጠፉ በአጸፋው የሚሰነዘርባቸውን የጥላቻ ንግግርንም ለመቀበል የግድ መፍቀድ ነበረባቸው፡፡ ይሄ የሞራል (የቅስም) ፣ የአመክንዮ (logic) እና የፍትሕ ግዴታ ነውና፡፡ ይሄንን የአጸፋ ምላሽ ከጠሉ ደግሞ ከመበደልና ጥፋት ከመፈጸም መቆጠብ ነው ያለባቸው፡፡ እነሱ ግን የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ!” እንዲሉ መበደላቸው ሳያንስ አትናገሩን ብለው ሥልጣናቸውን በመጠቀም አፈና ይፈጽማሉ፡፡

እና ምን እያልኩ ነው ማለት ነው ሁልጊዜም ባይሆን አብዛኛውን ጊዜ የጥላቻ ንግግሮች የሚመነጩት ኃይል ወይም ሥልጣን ከሌላቸው፣ አቅም ካነሳቸውና በሌሎች ኢፍትሐዊ ቁጥጥር ስር ካሉ አካላት ነው እያልኩ ነው ያለሁት፡፡ ለዚህም ነው ጉዳዩ በዓለምአቀፍ ደረጃ ትክክለኛ ግንዛቤ ሊያዝበት ያልቻለው፡፡ ያው ዓለም የጉልበተኞች አይደለች??? ጉልበተኞች ደግሞ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሕግ እያወጡ ሳይቀር አቅመቢሶችን ይጨቁናሉ ያፍናሉ ወዘተረፈ.

የዐቢይ አሥተዳደርም ወደፊት ጉዱ እየተገለጠ ሲመጣ ውርደቱን መከናነቡንና ተከትሎት የሚመጣውን ማኅበራዊ ቅጣት በመፍራት እንዲሁም ጆሮ ሊሸከማቸው ለማይችላቸው የወያኔ ኩነኔዎች ምላሽ እንዳይሰጥ ለማፈን በማሰብ የጥላቻ ንግግርን የሚከለክልና የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ሕግ ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይሄንን ሸፍጠኛና አንባገነናዊ አፋኝ እርምጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥብቆ በመቃወምና በማውገዝ ለተፈጥሯዊና ማኅበራዊ መብቱ እንዲቆም አጥብቄ ማሳሳብ እወዳለሁ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com