በሰው የሚጠሉት ወይም እንደሚጠሉት የሚናገሩትን ራስ ሲያደርጉት የማያስጠላ ከሆነ የተሳከረ ስብዕና (MPD) ባለቤት የመሆን ችግር አለ ማለት ነውና በቶሎ መታከም ያስፈልጋል፡፡ እኔ ለምሣሌ በወንድሜ ወይ በጓደኛየ ላይ የማየውንና የምቃወመውን መጥፎ የመሰለኝን ምግባር እኔ ራሴ ባደርግና እንደነውር ባልቆጥር ትክክል አይደለሁም፡፡ ጨለማና ብርሃን ኅብረት እንደሌላቸው ሁሉ በአንድ ሰውነት ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ ተቃራኒ ሰውነቶች ሊኖሩ አይችልም፡፡ እንደዚያ ያለ ችግር በፖለቲካው መስክ በጉልኅ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ አንቀጽ መግቢያየ መሆኑ ነው፡፡

ትናንት የሀገራችን – በአዲሱ አጠራር – የፖለቲካ ተፎካካሪዎች በጠ/ሚኒስትሩ ተጠርተው ውይይትና የምሣም ግብዣ ማድረጋቸውን በሚዲያ ተከታትለናል፡፡ እጅግ በጎ ጅምር ነው፡፡ በሀገራችን ለዘመናት ስንመኘው የነበረና በነዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ እንቅስቃሴ ጎልቶ በታየባቸው ወራት ውስጥ እናያለን ብለን ያልገመትነው ነገር ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ከዚህ መልካም ጅማሮ ብዙ ነገር እንደተማሩ መገመት ይቻላል – ለመማር ፈቃደኛ ከሆኑ፡፡ በባህላችን እንካ ያሉት ዳቦ እርካሽ እንደሆነ መኖሩ አውኮን እንጂ በቀደምት አምባገነን ገዢዎች ዘንድ እንደዜጋና እንደሰውም መቆጠር ብርቅ እየሆነባቸው በየማጎሪያ ቤቶች እየታጨቁ ስንትና ስንት ግፍና በደል ይደርስባቸው የነበሩ ተቃዋሚዎች ይህንን የመሰለ ክብር ሲያገኙ ቢያንስ የጌቶች ጌታ የሆነውን ኅያው እግዚአብሔርን – የሚያምኑ ከሆነ ነው እሱም-  ቢበዛ ደግሞ ለዚህ ማዕረግ ያበቃቸውን የሕዝብ ትግልና የወጣቶች መስዋዕትነት ክብር ሊሰጡት በተገባ ነበር፡፡ ይቺ ዕድል እንዲህ በቀላሉ አልተገኘችም፡፡ እንኳንስ ተቃዋሚዎች ጠ/ሚ ዐቢይ ራሱ የንጹሓን ዜጎች ደምና አጥንት ነው ወደላይ አሽቀንጥሮ ለዚህ የታሪክ ኃላፊነት ያበቃው – ኃላፊነቱ ባለው እቶናዊ የሚጋረፍ ሙቀት የተነሣ የሚቀናበት ባይሆንም፡፡ ነገር ግን በሀገራችን የተለመደው ነገር ሌላ ሆነና ተቸገርን፡፡ አንድ ያገሬ የኔ ቢጤ (“ለማኝ” ላለማለት ነው) እንዲህ አለ ይባላል – “ስንቅ ያለቀበት ጌታ ‹ደጅህ ላይ ቆሟል› ብለህ ለጌታህ ንገረው!”፡፡ መግደርደርና መኮፈስ በመንደር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በላይኛው እርከንም መታየቱ እየጎዳን ነው፡፡… እንጂ አሁን “በምድርህና በሕዝብህ መሀል በሰላም ታገል” ተብሎ ተጠርቶ ሲያበቃ ሕዝብን ማመስና ትጥቅ አልፈታም ማለትን ምን ያመጣው ነበር? ለማንኛውም የነፃነትን አየር ገና በጨረፍታው ከመተንፈሳችን ያን ለዘመናት ያንገፈገፈንን የቆሪጥ አገዛዝ እንዳታመጡብን ተቃዋሚዎች አቅል ግዙልን፤ ከራሳችሁም፣ ከመንግሥትም ጋር በቀናነት ተግባቡ፡፡ እናንተስ ሾልካችሁ ብትሄዱ መውጫ መግቢያውን ታውቁታላችሁና ምንም አትሆኑም፡፡  ለኛ ለተገፋነው አስቡልን፡፡ …

የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ስብሰባ በቲቪ ስመለከት ብዙ የተደበላለቀ ስሜት አደረብኝ፡፡ ጎላ ብሎ የተሰማኝ ግን ሀገራችን በሁሉም ረገድ ዕድለኛ አለመሆኗ ነው፡፡ በርካታዎቹ ፖለቲከኞች ዕድሜያቸው ከመግፋቱ የተነሣ ራሳቸውን ችለው ስለመራመዳቸውም ተጠራጠርኩ፡፡ እንዲህም አልኩና ራሴን ጠየቅሁ “ይሄ ፖለቲካ የሚሉት ነገር ጡረታ የለውም ማለት ነው?” ጥያቄየ ሳላስበው ቀጠለ “እነዚህ ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባሉ ነገሮች ከትግራይ – ከወያኔ ትግሬዎች መፈልፈያ ዋሻ –  ብቻ ሣይሆን ከመላው ፖለቲከኞቻችን ጭንቅላት ውስጥም ሙልጭ ብለው ወጥተው ይሆን?” አልኩ፡፡ ነገር በሦስት ሲሆን ይጸናልና እንዲህ ስል ጥያቀየን ሰለስኩ – “በዚህ ሁኔታ የዚህች ሀገር የመኖር ዋስትና ምንድን ነው?” አዎ፣ ከ“ታላላቆች” እንዲህ ያለ ስሜት-አልባነት (insensitivity) ከተስተዋለ ከተራው ዜጋማ ምን ሊጠበቅ? “የዓሣ ግማት ከአናት” መባሉ ትክክል ነው፡፡ ሁላችን ተያይዘን የዝቅጠት ቁልቁለቱን የምንነጉደው አለምክንያት አልነበረም፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን?

አንዱ አንዱን ሲያማ ጀምበር ልትጠልቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በመንግሥት ወንበር ላይ ያሉትን “ሥልጣን ርስተ ጉልት መሰላቸው እንዴ? የሥልጣን ገደብ ተበጅቶለት መሪዎቻችንን በዙር ለምን አንመርጥም?” ለማለት የሚቀድሙት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ይህን የሚሉ ተፎካካሪዎችን በየድርጅታቸው በሚገኙ ወንበሮች አንዳንዶቹ ከ25 ዓመታት በላይ መጎለታቸውንና በፈረንጅኛው አነጋገር እዚያው ወንበር ላይ vegetate ማድረጋቸውን ሳስበው አፈርኩ፡፡ በሀገሬ ዕድልም አዘንኩ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂት ጎልማሦችን ብቻ ነው ያየሁት፡፡ አብዛኛው ያረጀው ያፈጀው የኢህአፓውና በኋሊዮሽ አቆጣጠር ከዚያም የሚያልፈው ትውልድ ነው – አንዳንዶቹ እንዲያውም ከዐቢይ ጋር መግባባት ሊሣናቸው የሚችሉ ጎምቱዎች ናቸው፡፡ ደግነቱ የመድረኩ መሪ – ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ – ወጣት መሆኑ ትንሽ ተስፋ አጫረብኝ እንጂ ዱሮ ወጣት ሳለሁ የፖለቲካ ቡድን መሪ የነበሩ የያኔዎቹ አንጋፋዎች አሁንም በ80 እና በ90ዎቹ ዕድሜያቸው እዚያው ሙጭጭ ብለው ስመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ ንግግርና ተግባር እጅግ የተለያዩ መሆናቸውን አስታወስኩ – አወውሮፓ ውስጥ ብሆን ኖሮ – ብቻየንም ብሆን ሠልፍ ወጥቼ “shame on you dear octogenarians and nonagenarians!” እል ነበር – ዕድሜ ፀጋ መሆኑንና በአግባ ከተጠቀሙበት የሚያስከብር መሆኑን አውቃለሁና ትችቴን ከዐውድ ውጪ በሌላ መልክ እንዳትተረጉሙብኝ አደራ፡፡ ይህ ራስን የማምለክና ሌሎችም እንዲያመልኩብን የማስገደድ አባዜ ቤተ መንግሥቱን አልፎ ወደ ተቃዋሚዎች መውረድ ነገንም ከዛሬው በበለጠ እንድንፈራው ቢያስገድደን አይፈረድብንም፡፡ ክፉ ዐመል፡፡

በዚህች የበሬ ግምባር በማታህል ሀገር እንደሚባለው 70 እና 80 የፖለቲካ ኩይሣ ካለ የበሽታ እንጂ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ከ310 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አሜሪካ እንኳን ሁለት ታላላቅ ፓርቲዎች ናቸው ያሏት፤ ከዚህ አንጻር የኛ በርግጥም አለመታደል ብቻ ሣይሆን ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ፓርቲ ደግሞ በጎሣ የተመሠረተ ነው ማለት አንችልም፡፡ ለይምሰል ያህልም ቢሆን የሃሳብና የአመለካከት ልዩነትም አለበት፡፡ ስለዚህ ችግሩ የጎሣና የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን እነሱን ሽፋን አድርጎ በሃሳብና በአመለካከት የተለያዩ በማስመሰል የጥቅምና የሥልጣን ፍትጊያ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ከ“ፍቅር እስከመቃብር”  የሚቀጥል “የሥልጣን ጥም እስከ መቃብር” በሚል መጽሐፍ ቢጻፍ ጥሩ ነው፡፡

አንዲት ትል ከመሀል ሸዋ በጧት ተነስታ እየገሠገሠች ስትሄድ እዚያው መሀል ሸዋ አንድ ሰው ያያታል አሉ፡፡ “አንች ትል ወዴት ትሄጃለሽ?” ብሎ ይጠይቃታል፡፡ እርሷም “መተማ!” ብላ ትመልስለታለች፡፡ እሱም ይቀጥልና “ትደርሻለች?”ይላታል፡፡ እርሷም “ልብማ!” ትለውና መንገዷን ትቀጥላለች፡፡ እኛም በነዚህ ጎምቱ የፖለተካ አበጋሮች የዴሞክራሲ ጥማታችን ሊረካ ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡…