
ማክሰኞ ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ስለ ዲሞክራሲና የምርጫ ስርዓትን ስለ ማሻሻል የመከሩበት መድረክ በተለየ መልኩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል ፤ መድረኩ በአዛውንት ወንድ ፖለቲከኞች የተሞላ መሆን።
የኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ ፊታውራሪዎች በተለይም ለአራት ወይም አምስት አሰርት ዓመታት በተቃውሞ በቆዩ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች መሆን ብዙዎችን ያነጋግር ይዟል። ወጣት ሴቶችና ወጣት ወንዶች በተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎአቸው ቦታቸው የት ነው? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ጎልቶ እንዲወጣም አድርጓል ሊባል ይችላል።
በሌላ በኩል ሴት በመብራት የሚፈለግበት መድረክ መሆኑን ተከትሎም “ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን” የሚሉ አስተያየቶችም በማህበራዊ ሚዲያ ተንፀባርቀዋል።
“ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን”
የስርዓተ ፆታና ህግ አማካሪ የሆነችው ህሊና ብርሃኑ “ሴቶቸን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን” ሲሉ ድምፃቸውን ካሰሙት አንዷ ነች።
ያለውን ስርዓት ክፍተትና ጉድለት እሞላለሁ ብሎ የተነሳ ተቃዋሚ ሴቶችንና ወጣቶችን አካታች አለመሆን ተቃርኖ አለው ትላለች ህሊና።
“አንድን ስርዓት የተሻለ አደርጋለሁ ብሎ አካታች አለመሆን፣ ፍትህና መፍትሄ ሳይዙ መምጣት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ነው። አካታች ሳይሆኑ ተቃዋሚ መሆን አይቻልም “ትላለች።
• “ሥልጣን ለደም ግፊት አጋልጦኛል” ኃይሌ ገብረሥላሴ
• ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶቿ ላይ ሽግሽግና ለውጥ ልታደርግ ነው
ወጣት ሴቶች በሁለት መልኩ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ እንዲሆኑ እንደሚደረግም ታምናለች ሕሊና። ለዚህም ወጣት ሲባል የሚታሰበው ወንድ ፤ ሴት ሲባልም የሚታሰበው ትልልቅ ሴት መሆኑን በምክንያትነት ታስቀምጣለች።
ስለዚህም ሴቶቸን በተለይም ወጣት ሴቶችን ሳይዙ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር የሚቻል አይደለም።
“አካታች ያልሆነ፣ በቁጥር ብዙሃኑን የማይጨምር ፖለቲካ በብሄር ቢሆን ያስነውር ነበር”
‘ወጣቱ አገር ተረካቢ ነው ‘ እንዲሁም ‘የሴቶች ተሳትፎና ወደ አመራርነት መምጣት ቀስ በቀስ ይመጣል ይስተካከላል’ የሚሉ አስተያየቶችንም አትቀበልም።
“ወጣት የነገ መሪ ነው በሚል ነገ ላይ እንጂ ዛሬ ላይ አይጠበቅም። ወጣት የሆንኩት፣ ሰው የሆንኩትና ጉዳይ ያለኝ ዛሬ ነው። ስለዚህ የዛሬ እንጂ የወደፊት አይደለሁም። የሴቶች ተሳትፎም መሆን እንደሚገባው ሳይሆን ቀስ ብሎ እንደሚመጣ ነገር ነው የሚታየው”
ህሊና እንደምትለው ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆነው መመዝገብ የሚፈልጉ ድርጅቶች በህግ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን እሄን ያህል ብሎ ቁጥር በማስቀመጥ እንደ መስፈርት ቢያስቀምጥ ጥሩ ነው። በዚህ አስገዳጅ መስፈርት ድርጅቶቹ የግድ አካታች ይሆናሉ።
በዚህ መልኩ የተጠናከረ ህግ መኖር ደግሞ ፓርቲዎቹ እንዲሁ መቃወም ብቻ ሳይሆን የጠራ የስርዓተ ፆታና የወጣቶች ፖሊሲ እንዲቀርፁ እንደሚያደርግ እምነት አላት።
“ትግላችን ይቀጥላል”
የአረና ፓርቲ መስራች የሆኑት የቀድሞ የህወሃት ታጋይ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ እስከ አሁን የኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ በጣም የተገደበ መሆን የተቃውሞ መድረክ ዛሬም በስልሳዎቹ የፖለቲካ ትኩሳት ወጣትቶች፤ በዛሬዎቹ አዛውንቶች እንዲመራ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
“ምህዳሩ በጣም ገዳቢና ነፃነት የሌለው ነበር። እስከዛሬ በተቃውሞ ያሉት በስልሳዎቹ ወጥተው ደፍረው መናገር የቻሉ ናቸው።ወጣቱ ግን የሴቶች ፣ የወጣት ማህበርና ወጣት ሊግ እየተባለ ታፍኖ የቆየ ነው”ይላሉ።
• የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ተዋሃዱ
ነገሮች ክፍት ሆነው ሰዎች በፈለጉበት መንገድ በነፃት የሚደራጁበት እድል እስካልተፈጠረ ድረስ አሁንም ለዓመታት ቀደምት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መቀጠላቸው እንደማይቀር ያመለክታሉ።
በተጨማሪ የፖለቲካው ሴቶችን አሳታፊ አለመሆን የአባታዊ ስርዓት ውጥረት እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ አረጋሽ ሴቶች በመደራጀት ለራሳቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም ተደራጅተው ይህን እውነታ መቀየር እንዳለባቸው ያምናሉ።
ለእርሳቸው በብዙ የትግል ድምር ውጤት ዛሬ ላይ መደረሱ አንድ ነገር ነው ። የህገ መንግስቱ መፅደቅ ደግሞ እንደ ትልቅ ስኬት ይመለከቱታል።
“ግን ይህ ህግ ስላልተገበረ ግን ዛሬም ስለ ዲሞክራሲ ችግር ስለ ሰብአዊ መብት ጥሰት እየሰማን ነው። ታገልን የተቻለንን አደረግን ግን ሂደት ነውና ምን ማድረግ ይቻላል። መሻሻል ፣ ለውጥ እንዲመጣ ትግላችን ይቀጥላል” ይላሉ ወ/ሮ አረጋሽ።
“ቆሞ የቀረ ተቃውሞ”
የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት የነበረው ዮናታን ተስፋዬ በሚኒስትር ፣ በፓርቲ እንዲሁም በመንግስት አስተዳደር ላይ ወደ ላይ እየወጡ ያሉ ሰዎች ሲታይ ኢህአዴግ የተሻለ አቋም ላይ ነው የሚል እምነት አለው።
በተቃራኒው “በ60ዎቹና 70ዎቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተቆጣጠሩት የተቃውሞ ፖለቲካ ቆሞ ቀርቷል” ይላል።
የተቃውሞ ፖለቲካው ለምን በአንጋፎች ተሞላ? ለሚለው መሪዎቹ ለተለየ ሃሳብ ክፍት ስላልሆኑና ወጣቱ ደግሞ በነበረው ‘ዘልማዳዊ ፖለቲካ’ ውስጥ ጊዜውን ከሚያጠፋ ለራሱ ሮጦ የፈለገበት መድረስ የሚፈልግ በመሆኑ እንደሆነ ይገልፃል።
ከነዚህ በተጨማሪም ጥናት የሚያስፈልጋቸው ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ያምናል።
“የሚሞክረውም በሴራና በዘልማድ በሚሰራ ስራ ተጠልፎ ይወጣል። የእኔም ቆይታ በዚህ ውስጥ ነበር። እናንተ ደግሞ ትናንት መጥታችሁ ፖለቲካ ልታስተምሩን ነው ይባላል”
በርካቶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አብዛኞቹ አባሎቻቸው ወጣቶች እንደሆኑና በአደረጃጀትም የወጣት ቡድን እንዳላቸው ይገልፃሉ።ይህ ከሆነ ወጣቶች ለምን ወጥተውና ጎልተው አይታዩም?
ዮናታን እንደሚለው ምንም እንኳ መዋቅሮቹ ቢኖሩም በዚህ ‘በጣም በታፈነ ‘ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ልምድ ለሌለው ወጣት ሰብሮ መውጣት ትልቅ አቅም የሚጠይቅ ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ደግሞ ከራሳቸው ውጭ ማንም ጎልቶ እንዲወጣ የሚፈቅዱ አይደሉም።
“ወጣቶችም አዛውንቶችም ያስፈልጋሉ”
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ድርጅታቸው በመዋቅር የተደራጀ የወጣት ሊግ እንዳለው ይናገራሉ ፤የወጣት ክንፉ ትግሉን በበላይነት የሚመራ ነውም ይላሉ። በግምት ሰማንያ በመቶ የሚሆነው አባላቸውም ወጣት እንደሆነ ይገልፃሉ።
ወጣቱን እንዴት ወደ ላይ ወደ አመራር እናውጣ? የሚለው ላይ ካልሆነ በስተቀር ትግሉን የተሸከመውና የዛሬውን ለውጥ ያመጣው ወጣቱ ነው ይላሉ።
“ከስር የወጣነው፣ ከውጭ የገባው እንዲሁም ምኒሊክ ቤተመንግስት የገባነውም በወጣቱ ትግል እንጂ በሌላ እኮ አይደለም”
በተቃውሞ ፖለቲካው አመራር ደረጃ ለምን የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎና አመራር አልታየም ለሚለው ከተቃዋሚ ድርጅቶች ይልቅ መንግሥት ተጠያቂ እንደሆነ ዶ/ር መረራ ይናገራሉ።
ጥያቄውን የሚመልሰውም የአገሪቱ ፖለቲካ ነውም ይላሉ።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት ከቀውስ ወደ ቀውስ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ መንግስት ወጣቱን ሲያሳድድ ፣ ሲገርፍና ሲገድል ነበር። ስለዚህም ወጣቱ ወይ እስር ቤት ወይ ስደት ላይ ነበር።
“ወጣቶችም አዛውንቶችም ያስፈልጋሉ” የሚሉት ዶ/ር መረራ በፓርቲያቸው በወጣቶችና በአዛውንቶች መካከል ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለና አንጋፎቹ ወጣቶቹ ላይ መንገድ እንዳልዘጉም ያስረዳሉ።
ጠቃሚውና ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት ወጣቱም አዛውንቱም የራሱን የቤት ስራ ቢሰራና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን የሚታገሉ ሰዎች ትግሉን ቢገፉ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ።