በዚህ ሰሞን በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ስለተከሰተው ግጭትና ወያኔ አቀነባባሪነት በ1985 ዓ.ም. በዓለማያ ዩኒቨርስቲ ስተፈጸመው ግጭት ተመሳሳይነት
(ገብሬ ኪዳነማሪያም)
ይህችን አጭር ጽሑፍ እንድልክላችሁ ያነሳሳኝ ህወኃትና ተላላኪዎቿ ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ያቀነባበሩት የወንጀል ድርጊት ነው። አስቀድሜ ወያኔና ኦነግ ባመጡት የጎሳ ልዩነት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናቱን እየተመኘሁ፤ ወጣቱ ትውልድ ጠላቶቹ ከቀመሙለት መርዝ ራሱን እንዲጠብቅ አደራ እላለሁ።
እንደዚህ ጸሓፊ እምነት፤ የህወኃት የሰሞኑ ዓላማ ኢትዮጵያውያንን (በተለይም የአማራውንና የኦሮሞውን ወጣቶች) ደም በማቃባት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለመቀልበስና ከቻለች ወይ ወደነበረችበት ፈላጭ ቆራጭነት ለመመለስ፤ ወይ ደግሞ ሀገሪቱን ወደማያባራ ግጭት በመምራት ላቀደችው የትግራይ ሪፑብሊክ ምሥረታ (ለወንጀሎቿ ጠያቂ በሌለበት) መንገድ ማመቻቸት ነው። ወያኔና ግብረአበሮቿ በ1985 ዓ.ም. የፈጸሙት ድርጊት ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ከተፈጸመው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ስለማምን በ1985 ዓ.ም. የሆነውን በአጭሩ ከዚህ በታች አስፍሬአለሁ።
ወቅቱ 1985 ዓ.ም. ነበር፤ የቀድሞዉ የተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ አዲስ አበባን ሊጎበኙ መምጣታቸውን በመቃወም (ግብጻዊ በመሆናቸው የኤርትራን ከእናት ሀገሯ መገንጠል ደግፈዋል ተብሎ ስለታመነ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸዉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ሰልፍ በወጡ ተማሪዎች ላይ ወያኔ አባላቱን ከተማሪዎች ቀላቅሎ አስሰልፎ ዋና ጎዳና ላይ ከወጡ በኋላ ከመካከላቸው በጩቤና በሽጉጥ እንዳስወጋቸውና እንዳስደበደባቸው በዚያ ወቅት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመከታተል የደረሱ ሁሉ የሚያስታዉሱት ጉዳይ ነው።
![]() |
ህወሃት ያቀነባበረው በአሶሳ ዮንቨርስቲ ተማሪዎች የተፈጠው ግጭት
ህወሃት ባቀነባበረው በአሶሳ ዮንቨርስቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ
ተማሪዎቹም የደረሰባቸውን ጥቃትና ግድያ በመቃወም የትምህርት ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ በወቅቱ በትምህርት ጥራቱና በተማሪ ቅበላ ከሃገሪቱ ሶስት ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የነበረው የዓለማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በተደረገው ጥቃት የተሳተፉ በኃላፊነት እንዲጠየቁ በመጠየቅ እነሱም የትምህርት ማቆም አድማ አደረጉ። ከዩኒቨርስቲዉ አስተዳደር ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ቢደረግባቸውም ተማሪዎቹ በሕብረት በአቋማቸው ፀኑ።
ለማስታወስ ያህል፤ በ1985 ዓ.ም. ማለቂያ ገደማ ኦነግ ከወያኔ ተለይቶ አመራሩ በአብዛኛው ሀገር ለቅቆ የወጣበት ጊዜ ስለነበረ ወያኔ በኦነግ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረበት ወቅት ነበር። እንግዲህ ወያኔ ሁለት ታላላቅ ነገዶች ጥርስ እንደነከሱበት የተረዳበት ወቅት ነበር ማለት ነው። ስለዚህም እንዴት አድርጎ የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንዳለበት የተረዳበት ወቅት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም።
ይህንን ተከትሎ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች “እኛ ኦሮሞዎች የነፍጠኛው መሣሪያ አንሆንም!” እና ተመሳሳይ መፈክሮች እየጻፉ በተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ የማስታወቂያ ሰሌዳ መለጠፍ ጀመሩ። ባንዱ ቀን ይህንን ዓይነት መፈክር አንዱ የትግራይ ተወላጅ ሲለጥፍ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪ ያየዋል። ከዚያም ሄዶ “አንተ ትግሬ ሆነህ እንዴት በኛ ስም መፈክር ትለጥፋለህ?” ብሎ የተለጠፈዉን ገንጥሎ ይጥለዋል። በወቅቱ የትግራዩ ተወላጅ ያንን መፈክር ሲለጥፍ ራቅ ብለው ሲከታተሉት የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ከብበው ከኦሮሞው ተወላጅ ጋር ግብግብ ገጠሙ። ከዚያም ሁኔታዉን ያዩ ሌሎች ተማሪዎች ለግልግልና ለእገዛ ጣልቃ ገብተው ረብሻ ተነሳ። ከዚያም የዩኒቨርስቲዉ ጥበቃ አባላትና በአካባቢው የነበሩ የአገዛዙ ወታደሮች ወደ ምግብ አዳራሹ በመግባት የረብሻው አነሳሾች ናቸው የተባሉ ተማሪዎችን ሰብስበው ወደ ዩኒቨርስቲው እስር ቤት ወሰዷቸው። አመሻሹ ላይ የትግራይ ተወላጆች ሁሉ ተፈትተው ሌሎቹ እንዲያድሩ ተደረገ። በሚቀጥለው ቀን ይመስለኛል የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ተፈቱ።
የወያኔ ወኪሎች ግን ሴራቸዉን አቆሙ ማለት አልነበረም። አፈጻጸማቸውን ግን ቀየሩ። በዚያው ሰሞን አንድ ቀን ጥዋት ላይ፣ ከዩኒቨርስቲው ግቢ ውጭ የሚገኘውን ቤተክርስቲያን ሊሳለሙ ሲሄዱ የነበሩ ተማሪዎች አንድ የትግራይ ተወላጅ ተማሪ፣ ከላይ ከተጠቀሰው ተመሳሳይ የሆነ ኦሮሞውንና አማራውን ሊያጣላ ያለመ መፈክር ሲለጥፍ እጅ ከፍንጅ ያዙት። ከዚያም ለምስክርነት የሚሆን ቁጥር ስለነበራቸውና እራሳቸውም ስለያዙት በዩኒቨርስቲው የዲሲፕሊን ኮሚቴ በኩል ከሰሱት። ሆኖም በወቅቱ “የሰላምና የማረጋጋት ኮሚቴ” እየተባለ ይጠራ የነበረው (ግን ሕዝቡ “የሰላም ማናጋት ኮሚቴ” እያለ ይጠራው የነበረ) የወያኔ አባላት ድርጅት ተጽእኖ በማሳደር በዚህ ግለሰብ ላይ ምንም ሳይደርስበት በነጻ ትምህርቱን ጨርሶ ለመሄድ በቅቷል። (ስሙን እንጥቀሰው ከተባለ በርሄ አርከበ ይባላል)።
አሁንም ተማሪው በስላም በአቋሙ ጸንቶ ቀጠለ። ሆኖም የሰላም “ማናጋት” (ሰላምና መረጋጋት ይሉት የነበረው ማለት ነው) ኮሚቴው በበኩሉ በዩኒቨርስቲው ህብረተሰብ መካከል የነበረውን ግንኙነት የማበላሸት አፍራሽ ተልዕኮዉን ከመወጣት አልቦዘነም። ለኦሮሞ ተወላጆች “አማራዎቹ እንዲህ እያሏችሁ ነው”፤ ከአማራው ተወላጆች ደግም እየሄዱ “ኦሮሞዎቹ እንዲህ አያሏችሁ ነው” በማለት ያልተፈጠረ ጉዳይ እየፈጠሩ አሉባልታ እያስፋፉ ሰነበቱ።
ይህ በእንዲህ እያለ፤ በዚያው ሰሞን አንድ እሁድ ዕለት፤ ከሰዓት በኋላ፤ ሁለት የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ከግቢው ውጭ ሳሉ አንድ የአካባቢው ተወላጅ የሆነ ጎረምሳ እነዚህን ሁለት ተማሪዎች እየሰደበ ይከተላቸዋል (ጠባቸው በምን እንደተነሳ መረጃ የለኝም)። እነሱም ከግቢው ውጭ ታግሰውት ወደግቢው ውስጥ ሲገቡ ተከትሎ መሳደቡን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ ትዕግሥታቸው ያለቀው እነዚህ ተማሪዎች ለሁለት ይዘው በቡጢ መቱት። በወቅቱ እንደተወራው አንድ ጥርሱ ተሰበረ ሲባል ተሰምቷል።
ሌሊቱን ምን ሲሰራ እንዳደረ የሚያውቁት ወያኔና ተባባሪዎቻቸው ብቻ ናቸው። ሲነጋጋ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች የአልጋ ርብራባቸውን ይዘዉ የአማራው ተወላጅ ተማሪዎች በየአልጋቸው ላይ እያሉ በድንገት ዘመቱባቸው። ብዙ ተማሪዎች ለከፋ የኅሊናና የአካል ስብራት ተዳረጉ። ብዙዎች በዉስጥ ሱሪያቸው ብቻ ከመኖሪያ ሕንጻቸው እየወጡ በያቅጣጫው ሽሹ። ዓለምሰፋ በቀለ ጭጭአይበሉ የሚባል የሕጻናት አባት የሆነ (ጠና ያለ) ተማሪ ልጆቹንና እራሱን በትርፍ ጊዜው በጤና ረዳትነት እየረዳ የሚማር የአራተኛ ዓመት ተማሪ ነበር። በተማሪዎች ክሊኒክ ሲሠራ አድሮ መጥቶ ፊቱን እየታጠበ እያለ ከማጅራቱ ላይ በአልጋ ርብራብ ተደበደበ። ለሁለት ቀናት ያህል በሐረር በሚገኝ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ አለፈች። ዓለምሰፋ ትሁት ታታሪና በጓደኞቹ የተወደደና የተከበረ ሰው ነበር። የግፉዓን አምላክ ሕይወቱን በገነት እንዲያኖርልን የምናውቀው ሁሉ እንጸልያለን። ቅንድቧን የተነከሰች እህታችንም ነበረች፣ የነከሳትም ግለሰብ በዕድሜ ከርሷ በጣም የጠና ነበር።
ከዚያም የትምህርት ሚኒስቴር ባለሥልጣኖች (አቶ ጸጋዬ ይባል ነበር አንደኛው) መጥተው ተማሪዉን ለብቻ፣ መምህራኑን ለብቻ፣ የአስተዳደር ሠራተኛውን ለብቻ “ችግራችሁ ምንድን ነው?” እያሉ ጠየቁ። ከዚያም ብዙ ሰዎች በየዋህነት እውነቱን ተናገሩ። “መናገር የፈራችሁ በኤንቨሎፕ እያደረጋችሁ ከዚህ አድርጉልን” እየተባለም አንዳንድ የዩኒቨርስቲው አባላት ያላቸውን አስተያየት አስቀመጡ።
አሁንም ረብሻው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አገረሸ፤ ተማሪዎች ተበተኑ። ግማሹ ወደየቤተሰባቸው ሄዱ። ሌላው ግማሽ ወደ ሐረር የቀይ መስቀል ማህበር ጽህፈት ቤት በመሄድ ችግሩ ሳይፈታ አንመለስም ብለው በአቋማቸው ጸኑ። በሬዲዮም ተነገረ። ወያኔ የሚፈልገውን የሁለቱን ታላላቅ ነገዶች ግጭት ስላሳካ፤ በሌላ ዙር እስከሚመለስ ፊቱን ወደሌላ ለማዞር የወሰነ ይመስል ነበር። ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ያላቸውን ግለሰቦችና እንዲሁም የማይመለከታቸውን ግለሰቦች (በተለይ የምርምር ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩትን ዶ/ር ጎሹን) ከሥራ አነሳቸው። ዶ/ር ጎሹ በብሔረሰባቸው ሊፈረጁ ካልሆነ በቀር ከመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያገናኛቸው ጉዳይ አልነበረም። ግን ይህ ነው የወያኔ ፍትህ፣ ስለሆነም የቤተሰብ አስተዳዳሪና፣ ብዙ ላገራቸው ሊሠሩ የሚችሉ ምሁር ከሥራ ዉጭ ለመሆን ተዳረጉ። የተማሪዎች ዲን የነበሩትንም ግለሰብ እንደዚሁ ካለጥፋታቸው በየትኛዉም የመንግሥት መሥሪያ ቤት እንዳይቀጠሩ አድርጎ ካለምንም ክፍያ ከሥራ አስወገዳቸው። የዩኒቨርስቲዉንም ፕሬዚደንት እና የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት እንደዚሁ ካለምንም ክፍያ ከሥራ አስወገዳቸው።
ከዚህ በላይ ከብዙ በጥቂቱ ስለወያኔ የነገዶች ግጭት ፍብረካና አሁንም እየሆነ ካለው ይህ ትውልድ ሊማር የሚችለው ትምህርት እንዳለ በማለት የበኩሌን ብያለሁ። ሌሎች ደግሞ ብዙ ሊሉበት ስለሚችሉ ከነሱ እንስማ።
ቸር እንሰንብት።
***********
ገሬ ወዲ ሴሮ ገበረግዛብሄር ይባላ፡፡ በኢንቨስትመንትና ንግድ ስም አሶሳ ውስጥ የሚኖር ቀንደኛ የህወሓት ሰላይ ነው። የሰሞኑን የአሶሳን ዩኒቨርስቲ የተማሪወችን ግጭት በመፍጠር አማራንና ኦሮሞን ወደ ጠብ ለማስገባት ተልኮ ወስዶ ሲንቀሳቀስ የቆየነ ለ3 ተማሪወች መሞት ምክንያት የሆነ ነው፣ በጥቆማ ተይዞ ቤቱ ሲፈተሽም 2 ክላሽን ኮፕ መሳሪያ ከመሰ ጥይቶቻቸው፣ በርካታ የተለያዩ የባንክ ቸኮችና 400 የሚሆኑ የዩኒቨርስቲ የተማሪወች መታወቂያ ቤቱ ውስጥ ተገኝቶበታል። በአሁኑ ሰዓት ሕወሃት የትምህርት ተቋማትን የግጭት ማዕከል ለማድረግ ቆርጣ መነሳቷን የተለያዩ መረጃወች ያረጋግጣሉ!




