የኢትዮጵያ ነገር ቅንቅን ሆኖ ይበላኛል!!!
ታማኝ በየነ
 የአዲስ አበባ ጉዳይ
በዚህ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከተወለዱበት ካደጉበት አግብተው ከወለዱበት ቀዬ በተወሱኑ አጉራ ዘለል ወጣቶች ጥፉ ተብለው ሲሰደዱ ሲሞቱ ስመለከት ምን ያህል ኋላቀር ሕዝቦች እንደሆንን እያሰብኩ አዝናለሁ። አንተ መጤ ካልከው ኢትዮጵያዊ የበለጠ በዛ ምድር ምን መብት አለህ ብሎ የሚጠይቀው አለመኖሩ ያስቆጫል።
በዚህ ዘመን ሱማሌ ክልል ውስጥ የጅምላ መቃብሮች ተከፍተው በመቶዎች የሚቆጠሩ አፅሞች ሲወጡ (የደርግ ጥፋት ምን ነበር?) ሰዎች በቁም ሽንት ቤት ጉርጓድ ውስጥ ለቀናት በቁማቸው ሰንጠለጠሉ፣ እሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎችን አፈናቅለው በለሊት በጭነት መኪና ጭነው ሲወስዷቸው አንድ ጨቅላ ማልቀስ ሲጀምር ከጠባቂዎቹ አንዱ ዝም እንድታስብለው እናቱ ላይ ይጮሃል። እናት ጡት እየሰጠች እሽሩሩ እያለች ልታባብለው ብትሞክርም ልጁ ዝም ሊል አልቻለም። ጠባቂው ሁለተኛ እድል ሳይሰጣት ልጇን ከጉያዋ ነጥቆ በጨለማ ውስጥ በረሃው ላይ ወርውሮት ጉዟቸውን ቀጠሉ። ለሰከንዶች በዛች እናት ቦታ ሆኜ ሳስበው ይሰቀጥጠኛል። ሕዝቤ ግን ይህን መሰል ግፍ እየሰማ ብሄር ወይም ሞት ሲል ይገርመኛል።
በዚህ ዘመን በቢሊየን የሚቆጠር ብር በውጪ አገር ባንክ ደብቀው ወጣቱን ድሃና ተስፋ ቢስ ያረጉት ሌቦች ለፍርድ ይቅረቡ ሲባል በከፈሏቸው ጡሩንባዎች በኩል ብሄራችን ሊያጠፉ እያስባሉ ዘርፈው ድኻ ያረጉትን ወጣት “አዮኻ ናይና” በሚል መፈክር ለጦርነት ሊማግዱት ሲዘጋጁ ስታይ ያቅለሸልሽሃል። ወጣቱ ግን ለምን ብሎ አይጠይቅም። ግርርርርር
በዚህ ዘመን ዜግነታቸው ቀይረው በአውሮፓና አሜሪካ ተደላድለው እየኖሩ በችግርና በስራ ማጣት የሚሰቃየውን ድሃ ኢትዮጵያዊ እየቀሰቀሱ የሚያጋድሉ የእሬሳ ሸቃጭ ፖለቲከኞችን ስታይ ፌስቡክ ለምን ያስብልሃል።
በዚህ ዘመን አለም በኢኮኖሚና በፖለቲካ እየተባበረ ማርስን መኖሪያ  ለማድረግ ሲጥር እኛ ከአንድ መካከለኛ የአሜሪካ ድርጅት የማይበልጥ ሃብት ኖሮን 86 ክልል ልንመሰርት ስንሯሯጥ  ምን ጉድ ነን ያስብልሃል።
በዚህ ዘመን ስንት ሕዝብ ያጭበረበረውና የገደለው ጠንቋዩ አባባ ታምራት እንኳን በብሄሬ ምክንያት ነው የታሱርኩት ሲል ብሄር የሚለው ቃል ይሰቀጥጥሃል።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ይህን ዘመን የሚመጥን አንድ ከተማ መኖሩ ያፅናናል። አዲስ አበባ።
አዲስ አበባ ስትመጣ ማነህ አትልህም? ምን አለህ ግን ትልሃለች!
አዲስ አበባ ጥፋ አትልህም- ቤት ለእንግዳ ግን ተወዳደር ትልሃለች!
አዲስ አበባ ሰው ከሆንክ ተቀብላ ታላምድሃለች – ብሄር ከሆንክ ግን ሙድ ትይዝብሃለች! 
 
ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች አዲስ አበባ እየመጡ አንድ አመት ቢኖሩ ተለውጠው ይመለሱ ነበር!
 
አዲስ አበባ የቤንሻንጉሉ ሼህ ሆጀሌ (ሸጎሌ) የሚባል ሰፈር አላት።
አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አላት፣
አዲስ አበባ ፒያሳና መርካቶ ኢንዲጂኖ አላት።
አዲስ አበባ የኦሮሞው፣ የአማራው፣ የጉራጌው፣ የትግሬው፣ የሱማሌው፣ የአፍሪካዊያን ሁሉ ከተማ ናት።
አዲስ አበባ ትግሬው አብርሃ ደስታ ሲታሰር ሰሃን ቋጥራ ትጎበኛለች።
አዲስ አበባ ኦሮሞው አበበ ቢቂላ ሲያሸንፍ በስሙ ዘፈን ታሳትማለች። አዲስ አበባ ጥሩነሽ ዲባባን “ጥርዬ” እያለች ታቆላምጣታለች።
አዲስ አበባ አርከበ እቊባይ ጥሩ ሲሰራ በአዝማሪ ታወደሰዋለች።
አዲስ አበባ ብርሃኑ ነጋን ከንቲባ አርጋ መርጣለች።
አዲስ አበባ ለጋምቤላው ኦባንግ ሜቶ ታጨበጭባለች ተገቢውንም ክብር ትሰጣለች።
አዲስ አበባ የሁሉንም ብሄር ሙዚቃ አዘምና ትጫወታለች።
አዲስ አበባ በዚህ ዘመን የሰው ልጅ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ላይ ደርሳለች።
እናማ  ….
ብሄር ብሄረሰቦች መጤ የሚሏቸውን የሌላ ክልል ነዋሪ ጠርገው እንዳያባርሩ አንድ እንቅፋት አለባቸው። አዲስ አበባ።
አዲስ ሁሉንም አቻችላ እየኖረች ብሄሮች በየት በኩል ይገንጠሉ? ስለዚህ አንድ ቀን ኢትዮጵያን እንገነጥላለን የሚሉ ህልመኞች አዲስ አበባ የኔ ናት ይላሉ። ሌሎቹ ብሄሮችም ደስ ይላቸዋል እንጂ አይቃወሙም። አዲስ አባባ ግን የብሄር ከተማ ልትሆን አትችልም።
ያልገባቸው….
ውሃ ቁልቁል እንጂ ሽቅብ አይፈስም። አዲስ አበባ አንዴ ነቅታለች። አዲስ አበባን በሃይል መቀየር ቢችል መለስ ዜናዊ ይቀይራት ነበር። ግን አልቻለም። ሌሎቹም አይችሉም
በእርግጥ መንግስት አዲስ አበባ ላይ የተከተለው ፖሊሲ ስህተት ነበረው። በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት አዲስ አበባ ከሁለተኛው ከተማ በህዝብ ብዛትም በኢኮኖሚም ከ10 እጥፍ በላይ መብለጧን አንቤያለሁ። ኢኮኖሚው አንድ ቦታ ላይ መከማቸቱ በምንም መመዘኛ ትክክል አይደለም። የአዲስ አበባ ዘመናዊነት ሳይሆን አንፃራዊ  የኢኮኖሚ ልቀት ብሄር ብሄረሰቦችን  እንዲጓጉ አድርጓቸዋል።
የአዲስ አበባን መሬት ከኒውዮርክና ለንደን በሚስተካከል ዋጋ በካሬ ሜትር እየለኩ ቸርችረው ገበሬውን አላግባብ አፈናቅለውታል። በእርግጥ ገበሬው ወይ ከመሬቱ አልሆነ ወይ ስራ አልተፈጠረለት።  ይህ እድገት ለማን እንደጠቀመ ግልፅ ሲሆን የፍትሃዊነት ጥያቄ አስነስቷል። ጥያቄው በሁሉም ሕዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ወያኔን እንዲወድቅ ምክኒያት ሆኖታል።
ታዲያ ዛሬም ስልጣን ላይ ያለው ቡድን የአዲስ አበባን መሬት ከመሸጥ ውጪ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስበት ስልት የነደፈ አልመሰለኝም። በበኩሌ አዲስ አበባን ከዚህ በላይ ወደ ጎን መለጠጧን አጥብቄ እቃወማለሁ። ያልተመጣጠነ የከተሞች እድገት ፈፅሞ ጤናማ አይደለም። ለኢንቨስተሮች ማትጊያ መላሾ (ኢንሴንቲቭ) በመስጠት ሌሎች ከተሞች እንዲያለሙ ፖሊሲ ነድፎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ያኔ ሌሎቹ ከተሞችም እንደ አዲስ አበባ የደረሰችበት ይደርሱና በአዱስ አበባም መጣላት ያቆማሉ።
በነገራችን ላይ ዘንድሮ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አዲስ አበባ ላይ ይከበራል። ብሄር ብሄረሰቦች አዲስ አበባን ዘመናዊ ከተማ ያዱረጋት ሚሊኒየም አዳራሽ ሳይሆን የህዝቧ ዘመናዊነት ነው።
ቸር ያሰማን እስኪ።