ያለፈው እሁድ እለት በአማራ ክልል ፕሬዘዳንት በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው ልዑክ ቡድን ጋር ለመወያየት በዋሺንግተን ዲሲ በተጠራው ስብሰባ ተገኝቸ ነበር::
በጣም ጥሩ የሆነ ውይይት ነበር:: የአዴፓ አመራር አባላትም ለተነሱት ጥያቄዎች የሰጧቸው መልሶች የሚያረኩ ብቻ ሳይሆኑ የአመራሩንም ብስለትና ዝግጅት ያስመሰከሩ ነበር ብል ማጋነን አይሆንም::
አንድ በእጅጉ ያረጋገጥሁት ነገር ቢኖር ለውጡን እየመራው ያለው ቲም ለማ ተቢሎ የሚታወቀው ኃይል በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እየተናበበ የሚጏዝና የሚሰራ መሆኑንም ጭምር ነው:: እኛ በደንብ አልተረዳናቸው ይሆናል እንጅ እነርሱ ለውጡ ግቡን ሳይመታ ላይመለሱ አምረዋል:: የእኛ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ዋናው ተግባር ከምር ወገባችንን ጠበቅ አድርገን በሁሉም መስክ የለውጥ ኃይሉን ማገዝ መሆን ይኖርበታል ብየ በፅኑ አምናለሁ::
ተሰብሳቢው ብዙ ጥያቄ በማቅረቡ የተነሳ ሁሉን ጠያቂ ማስተናገድ የሚቻል ስላልነበረ እኔም ልዑኩን ለመጠየቅ ስላልቻልሁ ያዘጋጀህዋቸውን ጥያቄዎች በሚድያ በኩል እንዲደርሳቸው በማሰብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ:: መልስ ይሰጣሉ ብየ ተስፉ አድርጋለሁ።
1. መጪው ብሄራዊ ምርጫ
ለውጡን ተከትሎ ግጭቶች በተብራከቱበት ሰላም ገና ሙሉ በሙሉ ባልተረጋገጠበት ለዉጡን ለማደናቀፍ የወሰኑ ኃይሎች ሌት ከቀን በሚሰሩበት ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ህጎችና ደንቦች ተሟልተው በሌሉበት የምርጫ ቦርድ አዲስ ከተሾሙት መሪው በስተቀር ገና እስከ ታች ድረስ ባልተዋቀረበት የፍትህ አካላቱ ተጠናክሮ ባልተዋቀረበት አንዳንድ ክልሎች የፌደራል መንግስቱን መመሪያዎች ለማስፈፀም ሙሉ ፍላጎት በማሳዩበት የገዥው ቻርቲ ድርጅቶች እጅግ በተራራቀ ሁኔታ ላይ ባሉበት አንዳንድ ክልሎች ከጎረቤት ክልል ጋር ጦርነት ቀረሺ አቲካራ ውስጥ ባሉበት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገና በቅጡ ራሳቸውን ፈትሸው ቁጥሪቸውን ቀንሰው በመቀናጀት ባልተመዘገቡበት የሚድያ አጠቃቀም ህግ ባልወጣበት ህገ መንግስቱ ሳይሻሻል ወይንም ሳይለወጥ ህዝቡን እያፋጀ ያለዉ ክልል ፈርሶ በሁሉም የፌደራል አወቃቀር መርሆዎች ላይ የተመረኮዘ የአስተዳደር መዋቅሮች ሳይዘረጉ ባለበት ሁኔታ እንዴት ትክክለኛና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ይታሰባል። ሁለት አመት ማራዘምና ለምርጫ ተገቢ ዝግጅት ማድረጉ አይሻልምን?
2.አማራው ላይ የደረሰው ግፍ
ሕወሀት ሲመሰረት አማራ ጠላቴ ነው በማለት ከአርባ አመት በላይ በአማራው ላይ መሬቱን ቆርሶ ከመውሰድ ባሻገር ተዘርዝሮ የማያልቅ በደል ማድረሱ ይታወቃል:: ነገር ግን ሞረሽ ወገኔ የተባለ የሲቪክ ድርጅት ያቀረበው መፅሀፍና አንዳንድ ወገኖች ያቀረቧቸው መጣጥፎች ሁሉንም ዝርዝር በደል በፖለቲካው ከአገር አስተደር ጨርሶ ማግለል በኢኮኖሚ እንዲዳሺቅ ማድረግ ህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ በትምህርት በልማት እንዳያድግ በጤና እንዲጎዳ ይህ ሁሉ በስልትና በፖሊሲ ደረጃ ተቀርፆ ስለተሰራበት ሁሉም መታወቅ ስላለበትና መልስም ስለሚሻ ጥናት የሚያጠናና ውጤቱን በሪፖርት መልክ ለመንግስትና ለህዝብ የሚያቀርብ ቡድን ለማቋቋም የአማራ ክልላዊ መንግስት አቅዷል?
3. ኢፍትሀዊ የገጠር መሬት ፖሊሲ
በአስራ ሰባቱ የደርግ ስልጣን ወቅት የገበሬ ማህበር የሴቶች ማህበር የወጣቶች ማህበር የፍርድ ሸንጎ አባል የአገልግሌት ማህበር አመራር ብቻ ተመርጠው ያገለገሉ ገበሬዎች በሙሉ አድሀሪ ገበሬዎች ተብለው በመፈረጅ የነበራቸው መሬት ተነጥቅው ቤተሰባቸውን አርሰው ማስተደር እንዳይችሉ ተደርገው 28 የስቃይ አመታት በመግፋት ላይ ይገኛሉ:: በዚህ ከመሬት አላግባብ መነቀል ምክንያት የተሰደደውና የሞተው ቁጥሩ አይታወቅም::የቀረውም ወንድም ከወንድሙ ተስማምቶ እንዳይኖር የተደረገ ሲሆን ይህንን የተበላሸና ኢፍትሀዊ የሆነ የመሬት ፖሊሲ ለመለወጥ አዴፖ ምን እያደረገ ነው?
4.የየዳና ጨሞጋ ሀይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት
በድሮው አስተዳደር አጠራር ሶስት ወረዳዎችን ማለትም አዋባል አነደድና ባሶ ሊበን የተባሉ በምስሪቅ ጎጃም ከደብረ ማርቆስ ከቅርብ እርቀት የሚገኙትን ብዙ ህዝብ የሚኖርባቸውን ቀበሌ ገበሬ ማህበራት በማንሳት በለምነቱና በጤፍና በሌሎችም የሰብል አይነቶች ምርታማነቱ የታወቀለት እጅግ ሰፊ በሆነ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀበሌ ገበሬ ማህበራትን ባካተተ ስፍራ ሊሰራ የታቀደውን ግድብ አስመልክቶ ህዝቡ በግዳጅ መሬቴን ቦታየን ለቅቄ ለመሄድ ወስኛለሁ ብለው በግዳጅ እንዲፈርሙ ተደርገው ከዛሬ ነገ ተነሳን እያሉ በሀዘንና ሰሚ አጥተው በጭንቅ ላይ እንዳሉ ባልታወውቀ ምክንያት ፕሮጀክቱ ለጊዚው ተቋረጠ ተባለ::
ከነ ጭሪሹ ካልቀረ መንግስት እንደገና እንዲያጠናው ቢደረግ በሺሆች የሚቆጠር ህዝብ ከቀየው ማፈናቀሉን ያስቀራል። አስፈላጊነቱ በእውነተኛ ጥናት ከተረጋገጠ ህዝብ ሳይበደል ተገቢው ክፍያ ተሰጥቶት መኖሪያና የእርሻ የሚሄን ትክ መሬት ተሰጥቶት ቢከናወን አዴፓ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስባል?
5. የደብረ ማርቆስ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ
ጥንታውቷ የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ከተማ ደብረ ማርቆስ ለኢትዮጵያ ነፃነት የራሷን ድርሻ አበርክታለች:: ግርማዊ ጃንሆይ ከሱዳን በኦሜድላ መተከል በኩል ድፍን ጎጃምን ከአርበኞች ጋር በመጏዝ ደብረ ማርቆስ በመግባት ለአንድ ወር አካባቢ ከአባ ኮስትር በላይ ዘለቅ እንዲሁም ከሁሉም የጎጃም አርበኞች ጋር በክብር ተስተናግደው ጉዞ ወደ አዲስ አበባ በማድረግ ወራሪው ጣሊያን ተሸንፎ በድል አድራጊነት የኢትዮጵያ ነፃነት ዳግም ተረጋገጠ::ነገር ግን ደብረ ማርቆስ አንደ አንዳንድ የአገራችን ከተሞች በጣም ተዘንግታለች።
ደብረ ማርቆስ በንጉሱ አስተዳደር ጀምሮ የአውሮፕላን ማረፊያ ነበራት:: ነገር ግን ስራውን አቁሞ የከብት መዋያ ሜዳ ከሆነ ብዙ አመታት አለፈ:: በዚህ የለዉጥ አስቸጋሪ ጊዜ አሁን ላነሳው የፈለግሁት በቅርቡ አንድ የአውሮፕላኖች ባለቤት የሆነች ኢትጵያዊት ባለሀብት የክልሉ መንግስት ጥርጊያውን ከሰራ ህዝቡ በጣም ስለሚጠይቅ በረራ ለማድረግ እንችላለን ስትል በቲቪ ስላየሁ እንዴት ታዩታላችሁ ብዩ ለመጠየቅ ደፈርሁ?
ለማጠቃለል ጥያቄ ማዥጎድጎድ ብቻ ሳይሆን እኔም በምችለው ነግር ሁሉ እናንተን የለውጡን ኃይሎች ለማገዝ ቃል በመግባት ጭምር ነው::
የዶክተር አምባቸውን አባባል ልዋስና ተሸናፊዉ ኃይል የተሸነፈ ሳይመስለው በህዝቡ መራራ ተጋድሎና የለውጥ ኃይሉ ባሳየው የፖለቲካ ብልህነትና ድፍረት ከሁሉም በላይ በፈጣሪ ፈቃድ በድል ሙጠናቀቁ እጅግ የሚደነቅ ነው:: ነገር ግን ደግሞ እጅግ በሰከነ መልኩ መመራትን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን በንቃት ሊጠበቅ የሚገባውም ነው ለውጡ::

