December 12, 2018

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 3 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
በዚህ የለውጥ ጉዞዋም የሚለወጡ ነገሮች አሏት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚህ ውስጥም የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ታግለው የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ካደረጉባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰብዓዊ መብታቸውን የሚያከብር ሥርዓት ለማስፈን እንደነበር አስታውሰው፥ የሰብዓዊ መብት አያያዝም ሆነ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመሠረታዊነት እውን የሚሆኑት ከግለሰቦች ፍላጎት ይልቅ የጋራ ፍላጎት በወለዳቸው ተቋማት መመራት ሲጀምር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ተዓማኒ የሆኑ የዴሞክራሲያዊና የፍትሕ ተቋማት ባልተመሠረቱበት ሁኔታ፥ ግለሰቦች እንዳሻቸው ሲሆኑ መመልከት በታሪኩ በተደጋጋሚ ለተመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ እንደማይሆንም አንስተዋል።
ሕዝቡ ሁልጊዜም አምባገነናዊ ሥርዓትን ለመገርሰስ ሲታገልና መሥዕዋት ሲሆን ግፍ እንዲቆም፣ ፍትሕ እንዲሰፍን እንጅ፥ ሌሎች ግፈኞችን ለመተካት አይደለምም ነው ያሉት።
በሕዝብ ትግል ሥልጣን ላይ የወጡ አካላት ግን ከራሳቸው ፍላጎት ውጭ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት አለመቻላቸውን ጠቅሰው፥ ሕዝቡ ከነገ ዛሬ ይሻሻላል ብሎ ቢጠብቅና ድምፁን ቢያሰማም ችግሩ እየባሰ መሄዱንም አውስተዋል።
በተለይም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እየጠበበ፣ ዜጎች በብሔራቸውና በያዙት የፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት የሚደርስባቸው በደል እየከፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየባሰና ሙስና ይበልጥ እየሰፋ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
እነዚህና መሰል ሁኔታዎችም ህዝቡን በደልና ግፍ በቃን ብሎ እንዲነሳ አድርገውታልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በሃገር ላይ ከፍ ያለ ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖች በነጻነት ሲንቀሳቀሱ በተቃራኒው ህግ ያልፈረደባቸውና ተፈጥሯዊ መብቶቻቸውን የተጠቀሙ ዜጎች የከፋ እንግልትና ግፍ ቀማሽ ሆነዋልም ነው ያሉት።
በሀብት፣ በንብረትና በፖለቲካ ተሳትፎ ከሚሠራው ግፍ በባሰ በዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠራው ግፍ ‹ምነው ባልተወለድኩ› የሚያሰኝ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በፖሊስ፣ በደኅንነት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶችና በሌሎችም የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ በሚገኙ ባለሥልጣናት ፈቃጅነትና መሪነት፣ ኅሊናቸውን ሸጠው ለሆዳቸው ባደሩ የግፍ ሠራዊት ተላላኪነት በዜጎቻችን ላይ አራዊት የማይፈጽሙት ሰቆቃ ይወርድባቸው እንደነበር አንስተዋል በመልዕክታቸው።
ግፍ ፈጻሚዎቹ ከሳሽም፣ ምስክርም፣ መርማሪም፣ አሣሪም፣ ዐቃቤ ሕግም፣ ዳኛም፣ ሆነው የግፉን ድራማ ተውነውታልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዓለምን በጎ አስተሳሰብ የቀረጹ ታላላቅ እምነቶች የሆኑት የክርስትና፣ እስልምናና የይሁዲነት ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ አብዛኛው ሕዝብ ሃይማኖተኛ የሆነ እና ለሞራል ድንጋጌዎች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ታዲያ እነዚህ ሰዎች እንዴት ይሄንን ሁሉ ግፍ ሊፈጽሙ ቻሉ ሲሉም በመጠየቅ እነዚህ ሰዎች ማኅበረሰባችንን ቢወክሉ ኖሮ ሊያጠፉ ቢችሉ እንኳን እንዲህ ግፍ በልተው ግፍ ባልተነፈሱ ነበር ብለዋል።
እነዚህ ሰዎች ሰውነትንም አይወክሉም በማለት ስግብግብነት፣ አምባገነንነትና የሥልጣን ጥማት ጫፍ ላይ ሲደርሱ ሰውን ወደ አውሬነት እንዴት እንደሚቀይሩት ማሳያ መሆናቸውን ነው የገለፁት።
አሁን ወሳኙ ጥያቄ ‹ምን እናድርግ?› የሚለው ነው በማለትም፥ ግፈኞች የግፋቸውን ዋጋ በሕግ እንዲቀበሉ ማድረግ እና ይህ ግፍ በልጅ ልጆቻችን ዳግም እንዳይፈጸም የሚያደርግ አስተማማኝ ሥርዓት መዘርጋት ለጥያቄው መልስ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከእነርሱ የተሻልን መሆናችንን በተግባር ማሳየት ነው ብለዋል።
እነርሱ ያንን ሁሉ ግፍ ፈጽመው ምንም ሳይመስላቸው በልተው የሚጠግቡ፣ ተኝተው የሚያድሩ ሆነዋል፤ እኛ ግን ግፉ ይሰቀጥጠናል፣ ያመናል፣ ዕረፍትም ይነሣናል፤ በተለይ ደግሞ የተፈጸመው በአንድ በኩል በዜጎቻችን ላይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማናውቀው ሁኔታ በየመንደራችን በሚገኙ ድብቅ እሥር ቤቶች መሆኑን ስናውቅ ሕመሙ ይብስብናል በማለት ድርጊቱ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ አልፏል ነው ያሉት።
ግፈኞች ግፍ ፈጽመው በሰላም ተኝተው እንዲያድሩ መፍቀድ የለብንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ስለዚህም ይህን ግፍ የፈጸሙ ሁሉ በሕግ ፊት ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ተተኪዎቹ ትምህርት፣ ተጎጅዎቹም የኅሊና ዕረፍት እንዲያገኙ ማድረግ አለብን ብለዋል።
ይህንን ግፍ የፈጠሩትን ቀዳዳዎች መድፈን፣ ሕጎችን ማሻሻል፣ አሠራሮችን ማስተካከል፣ ተቋማትን ማብቃት፣ የዝርፊያንና የአምባገነንነት በሮችን መዝጋት እንደሚገባና አሁን እየተከናወኑ በሚገኙ የማሻሻያ ሥራዎች ጠንክሮ መግፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በሚገባ የሚያከብርና የሚያስከብር ሥርዓት መገንባት እንደሚገባም ገልፀዋል።
በፍርድ ቤቶች፣ በምርጫ ቦርድ፣ በሚዲያ ተቋማት፣ በመከላከያና በደኅንነት ተቋማት፣ በፖሊስና በማረሚያ ቤቶች እየተወሰዱ የሚገኙ ማሻሻያዎች ዓላማቸው ይሄንን ዘላቂ ሥርዓት እውን ለማድረግ እንደሆነ በመግለፅም፥ ለወደፊቱም በሌሎች ተቋማት ላይ ማሻሻያው እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ይህን ግፍ የፈጸሙ ሰዎች በሄዱበትም ሆነ እኛ እንድንሄድ በሚፈልጉት መንገድ መጓዝ የለብንም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመልዕክታቸው ግፈኞች በጥላቻ ተሞልተው ይህን በደል ቢፈጽሙም ጥላቻቸውን መውረስና በበቀል መታወር እንደማይገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ግፈኞች ሕግን የማያከብሩ፣ ፈጣሪን የማይፈሩ ሆነው የመከራ ዶፍ በሕዝባቸው ላይ ቢያወርዱም፤ እኛ ግን ፈጣሪን እንፈራለን፣ ሕግንም እናከብራለን ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት።
ግፈኞቹም ቢሆን ራሳቸውን እንጅ ግፋቸው በምንም መልኩ የበቀሉበትን ሕዝብ እንደማይመለከተው እናምናለን ብለዋል፤ የትኛውም ብሔርም ሆነ ዘር ግፈኞችን፣ ገራፊዎችንና ጨቋኞችን ሊያፈራ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
አንድ ብሳና ባጠፋ ጫካውን ሁሉ እንደማንቀየመው፣ ግለሰቦች ባጠፉ የምንቀየመው ወይም ጣት የምንቀስርበት ብሔር አይኖርም።
አብዲሳ አጋን፣ ጸጋዬ ገብረ መድኅህንን ወይም ታደሰ ብሩን ያፈራው የኦሮሞ ሕዝብ ጽዩፍ የሆኑ እኩያንን የማያበቅልበት፤ ጀግናው አሉላ አባ ነጋን ወይም ማኅሌታይ ያሬድን ለሀገር ያበረከተው የትግራይ ሕዝብ ታሪክ የማይረሳው በደል የፈጸሙ ወንጀለኞችን የማያፈራበት፤ እነ ቴዎድሮስን፣ በላይ ዘለቀን ወይም ገብርዬን የሸለመው አማራ ሌሎች ግፈኞችን ከውስጡ ሊያስገኝ የማይችልበት ምክንያት የለምም ብለዋል በመልዕክታቸው።
ወንጀለኛ ራሱን ችሎ ወንጀለኛ ለመሆን ከምንም ጋር መለጠፍ እና ማንም ላይ መደገፍ አያስፈልገውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወንጀለኛ በቁሙ ወንጀለኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ግፍ የሠራው ሰው የሚናገረው ቋንቋ ኦሮሚኛ ቢሆን ኦሮሞውን፣ ትግርኛ ቢናገር ትግሬውን፣ ከአማራ ክልል ቢወለድ አማራውን፣ ከሲዳማ ቢመጣ ሲዳማውን የሚወቅስ ሰው ካለ እሱ ከታሪክ የማይማር ደካማ መሆኑንም ነው ያነሱት።
እኛ ታሪካችንን በሚገባ የምንረዳና ነጋችንን ለማቅናት የምንተጋ እንጅ፣ ለአንድ ገጽ ብለን መጽሐፍ የምንቀድ ሞኞች አይደለንም፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ ነገም ወደፊትም ወንጀለኞች መፈጠራቸው አይቀርም። ሁልጊዜም ወንጀለኞቹን ሊደበቁበት ከሚፈልጉት ብሔር ነጥለን ማየትና እስከመጨረሻው ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባም አስረድተዋል።
እነርሱ ሊደበቁበት የሚፈልጉት ብሔር በምንም መንገድ የእነርሱን ግፍ ተመልክቶ የሚያለቅስ እንጅ ለእነርሱ ግፍ የሚያጨበጭብ ነው ብለን አናምንም፤ ይህ ምንጊዜም የማይቀየር አቋማችን መሆን አለበት።
ከዚህ ባለፈም ፈጽሞ የእነርሱ ስሕተት እንደማይደገምና እነርሱ በቀደዱልን ቦይ እንደማንፈስ ጠቁመው፥ እነርሱ እንደ እኛ እንዲሆኑ እንፈልጋለን እንጅ እኛ እንደነርሱ አንሆንምም ብለዋል።
ቂምና በቀልን ሳይሆን ፍርድና ፍትሕን ማሰብ ይገባል ያሉ ሲሆን፥ ይህ ሁሉ የሚደረገው እንደነርሱ ከጥላቻ ተነስተን ሳይሆን የሕግ የበላይነት መስፈን ስላለበት መሆኑንም ነው ያነሱት።
በተጨማሪም ያንን የግፍ ታሪክ መዘጋት ስላለበትና ያንን መድገም ስላማያስፈልግና ሌሎች ትምህርት እንዲያገኙበት በማሰብ መሆኑንም በመልዕክታቸው አብራርተዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን፣ ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ፣ የትኛውም ወገን ይጩህላቸው፣ በወንጀል እስከተጠረጠሩ ድረስ ካሉበት አድነን ለሕግ ማቅረባችን ግን አይቀሬ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ወሰንም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ድንበር ወንጀለኞችን ለፍርድ ከመቅረብ እንደማይታደጋቸውና ለዚህም መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን በመጥቀስ።
በአንድ በኩል ራሳችንን ከወጥመዳቸው እየተከላከልን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግፈኞች ፍትሕ እንዲያገኙ መሥራታችንን እንቀጥላለን።
ከእንግዲህ እምነታችን በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን በጠንካራና ተዓማኒ ተቋማት ላይ ነው፤ ግለሰቦች፣ ፍላጎታቸውና ጠባያቸው እንደየጊዜው ተቀያያሪ መሆኑን በታሪካችን ከበቂ በላይ ተጽፏል።
አሁን አዲስ ታሪክ መጻፍ እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ አቅማችንን የሁላችንም ፍላጎት ተቀናጅቶ በሚፈጥራቸው ጠንካራ ተቋማት ላይ ማፍሰስ ይገባልም ነው ያሉት።
እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ዘላቂና በጊዜ ሂደት የማይቀያየሩ፣ ሰቆቃን የሚያስቀሩ፣ ሁላችንንም እኩል የሚያይ ሥርዓት የሚዘረጉ እንጅ ለግለሰቦች ፍላጎት የሚገዙ አለመሆናቸውንም አውስተዋል።