December 16, 2018 e

አለቃ ገብረሐና ማን ናቸው?
(አብመድ)
አለቃ ገብረሐና በበጌ ምድር በደብረታቦር አውራጃ በፎገራ ወረዳ በናበጋ ቀበሌ ከመምህር ደስታ እና ወሮ. እታገኝ በ1814 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

አለቃ ገብረሐና ለሀገራቸው ጥበብን ይዘው ብቅ ማለታቸውን ከንጉሥ ዮሐንስ ሣልሳዊ (ዘመነ መሳፍንት እንደራሴ ከራስ አሊ) እስከ ዓጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት አስተማሪ ፍትሐ ነገሥትን ተርጓሚ ዳኛ እና አማካሪ የሆኑ የዘመኑ የበጌምደር የጥበብ ልክ እንደነበሩ መስፍን ሙላት ‹‹የአለቃ ገብረሐና ዛንታ›› በሚልው መጽሐፋቸው አስፍረውት ይገኛል፡፡
አለቃ የተወለዱበት ቦታ እጅግ የሚያምር የአትዮጵያ ደልዳላና የውኃ አዘል መሬቶች የሚበዙበት የጣና ሐይቅ እና የሸሸር ረግረጋማ ቦታወች መካከል በመሆኑ አካባቢው ከአውሮፓና ከእስያ የሚመጡ የዐዕዋፍ ዝርያዎች የሚበዙበት የዐዕዋፍ ዝማሬ እንዲሁም የዓሳ ምርት ቀጠና በመሆኑ አካባቢው የተሻለ ጥበብ የሚቀዳበት መሆኑ አለቃ ገብረሐናም በዘመኑ ብቻ ሳይሆን አሁንም አሻራወቻቸው ዘመን የማይሽራቸውና የአካባቢውን የወቅቱ የዕውቀት ደረጃ መለኪያ ሚዛን ተደርጎ ይታያል፡፡

ዕድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ ቅስና ትምህርት አባታቸው በናበጋ ጊዮርጊስ አስተምረዋቸው የዳዊት ትምህርት ከአጠናቀቁ በኋላ ዜማ ቤትም ትንሽ እንደተማሩ ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር በመሄድ የአካባቢውን የቅኔ ዕውቀት ዘርፈው ወደ ጎንደር ተመልሰው ሙሉ ፀዋትወ ዜማን፣ አቋቋምን፣ ድጓንና የመጻሕፍት ትርጓሜን በአጠረ ጊዜ አጠናቅቀዋል፡፡

አለቃ ገብርሐና ወ.ሮ ማዘንጊያን አግብተው የሦስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ልጆቻቸውም ስኑ፤ ተክሌ እና ጥሩነሽ ይባላሉ፡፡ ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸው የአባታቸውን ጥበብ ከሞላ ጎደል የተቀበሉ በመሆኑ የቤተ-ክርስቲያን አገልጋይነታቸው በዘር ሐረጋቸው እንደ አንጓ የሚመዘዝ እንደ ሆነ የአለቃን ትውልዶች በቅርበት የሚያውቁት አባቶች ምስክረነታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ስኑ የተባሉት ልጃቸው መምህር ኃይሉን ይወልዳሉ፤ መምህር ኃይሉም አሁን በሕይወት የሚገኙትን ቄስ ገደቤን ይወልዳሉ፡፡ በሕይወት ያሉት የአለቃ ገብረሐና ቤተሰቦች በናበጋ ቀበሌ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሌላኛው የአልቃ ልጅ ተክሌ የአለቃ ገብረሥላሴ አባት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

አለቃ ገብረሐና በ26 ዓመታቸው ጎንደር ሊቀ ካህን ሆነው ተሾመው ያሳለፏቸው 7 ዓመታት በስብከት ችሎታቸው ስመ-ጥር አደረጓቸው፤ በዚያ ላይ በቀልድ አፍላቂነታቸውም ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ ቆይተውም የፍትሐ ነገሥት ክብር አግኝተው የዳኝነት ሹመት ተሰጣቸውና የሥራው ፀባይ ስላልፈቀደላቸው ከቀልዱ ራሳቸውን ቆጠብ አደረጉ፡፡
ነገሩ ግን አልፎ አልፎ አንዳንድ ቀልዶችን ጣል ቢያደርጉም በወቅቱ ለሕዝብ ጆሮ ያልደረሱ ጉዳዮች ብዙ ነበሩ፡፡
ይህም ሆኖ ስማቸው እላይ የደረሰ በመሆኑ ከነገሥታት ጋር እየተቀራረቡ በተለያዩ ኃላፊነቶችና ግንኙነቶች ታሪካቸው ከነገሥታቱ ጋር የተቆራኘ ሆኖ እንድናየው አድርጎናል ፡፡
በዓፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ድርቡሾች የጎንደርን አካባቢ በመውረር አድባራትን አቃጠሉ፤ መነኩሳትንና ለቃውንትን ጨፈጨፉ፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ ሊቃውንት ተሰደዋል፤ አለቃ በዚህ ወቅት ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ለመደበቅ ምን ማደድረግ እንዳለባቸው ሲያስቡ ድርቡሾች በቂ ዝግጅት አድርገው ስለነበር ጣና ሐይቅ ከነአለቃ መንደር በድንገት ይደርሳሉ፡፡
ይሄኔ አለቃ ወ.ሮ ማዘንጊያንና ልጃቸው ጥሩነሽን ወደ መሀል በጌምድር ካሸሹ በኋላ ልጃቸው ተክሌ ወደ ወሎ ወርዶ ለራስ ሚካኤል እንዲያገለግል ነግረውና መርቀው ካሰናበቱት በኋላ እርሳቸውም ወዳጃቸውን ምኒሊክን ሊያገልግሉ ቆርጠው ወደ ሸዋ ተሰደዱ፡፡
አለቃ የተወለዱት ጣና ዳርቻ ላይ በመሆኑ አካባቢው የተለየ ውበት ልምላሜ እና የተፈጥሮ ቃና የበዛበት እንደመሆኑ መጠን ሕይወታቸው በብዙ መንገድ ከጣና ሐይቅ ጋር የተገናኘ ሆነ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከሐይቁ አጠገብ ቁጭ ብለው ተፈጥሮን እያደነቁ በውኃው ዳርቻ አካባቢ ያለው ሸንበቆ በውኃው ሞገድ እየታገዘ ከአንድ ጎን ወደ ሌላ ጎን እየዘመመ ሲያዩት አለቃም በጣም ተደንቀው ጣዕመ ዜማ የሚሰሙ ይመስል አብረው እንደ ሸንበቆዎቹ እየተወዛወዙ ክስተቱ ለአለቃ ብዙ ጥባባትንና ብልሃትን ወደ አዕምሯቸው እንዲያስገቡ አደረጋቸው፡፡

የሸንበቆውን ውዝዋዜ ያስተዋሉት አለቃ ገብረሐና ‹‹የሰው ልጅም በተመሳሳይ በእንዲህ ዓይነት ውዝዋዜ ውስጥ መግባት ይችላል›› ብለው የዝማሬ ትምህርትን እንደፈጠሩ ዴቪድ ዶናልድ የተባሉ ጸሐፊ ከኢትዮጵያውያን አፈታሪክ የሰሙትን መነሻ አድርገው ጽፈዋል፡፡

የሸንበቆዎቹ ውዝዋዜ በሂደት በትምህርት ዳብሮ የአለቃ ልጅ ተክሌ ከአባታቸው በአግባቡ ካጠኑት በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ በደብረታቦር ኢየሱስ ‹‹የተክሌ አቋቋም›› እየተባለ ያገለግላል፡፡
አለቃ ትምህርቱን አስፋፍተውት በመሀል ጎንደር እያስተማሩ ሳለ አልፎ አልፎ የሚቃወሟቸው ሰዎች መጡ፡፡ ከዚያ አለቃ ልጃቸውን ተክሌን ለብቻው አስተምረው በዕውቀት ላይ ዕውቀት አንዲጨምር አድርገውት ነው የተክሌ አቋቋም ለዚህ የበቃው፡፡

ተክሌ ወሎ ከንጉሥ ሚካኤል ጋር እንደደረሰ የተሰጠው ሥራ ለንጉሡ ፈረሶች ጭድ ማቀበል ስልነበር ብዙም ደስተኛ ሳይሆን ቆየ፡፡ የሰኔ ሚካኤል ንጉሥ ሚካኤል የተገኙበት የተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ንግሥ ግን ለተክሌ አንድ ዕድል ፈጠረ፡፡ በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ሲካሄድ ተክሌ ‹ጣነ ሞገሩ› ላይ አባቱ አለቃ ገብረሐና ያስተማሩትን ረዥም ዝማሜ አሳዬ፡፡ ንጉሡም ይህንን ሙያውን እንዳዩ ተደምመው ተክሌን ከንጉሡ በማይጠበቅ ከፍተኛ ስሜት አመሥግነው ከፈረስ መጋቢነት ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይት እንዲዛወሩ አዘዙ፡፡
ለብዙ ጊዜ በዚያው ካገለገለ በኋላ ተክሌ የጣና ጉዳይ እና የቤተሰቦቹ ናፍቆት ተደምሮ ወደ በጌምድር ናበጋ ጊዮርጊስ እንዲመለስ አደረገው፡፡
ከልጃቸው ወደ አለቃ ገብረሐና ታሪክ ስንመለስ አለቃ ለነገሥታቱ ፍትሐ ነገሥትን ይተረጉሙ ነበር፡፡ አለቃ ከቀልዶቻቸው በበለጠ በተግባራቸው ሚዛን የደፉ አባት ሆነው በ85 ዓመታቸው ሞቱ፡፡ እናም በናበጋ ጊዮርጊስ ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

የአለቃ ገብረሐና ለትውልድ የሠሯቸው እና ለወደፊት ታሪካቸውን ለመዘከር በስማቸው የሚታወሱበት ማስታወሻ ግን አልተቀመጠላቸውም፡፡ የፎገራ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ባለሙያ አቶ አብራራው ተሻገርን በአለቃ ማስታወሻ ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡
አቶ አብራራው ‹‹አለቃ ገብረሐና ተረት ተረት አይደሉም፤ የፍትሐ ነገሥት አባት፣ የተከሌ አቋቋም ፈልሳፊ ናቸው፡፡ የበጌምድር እንቁና ፈርጥ ነበሩ›› ብለዋል፡፡

የፎገራ ወረዳ የባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ መላኩ
የአለቃ ታሪክ ከዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ የግንኙነት ታሪክ የሚቀዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለአለቃ በናበጋ ጊዮርጊስ ቀበሌ ከልጅ ልጆቻቸው ጋር በመሆን ሀውልት ለመሥራት ዝግጅት አጠናቅቀናል፤ ገንዘብ እየሰበሰብንና ፕሮጀክት ቀርጸን ለሀውልቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያወቅን በመሆኑ ወደ ተግባር ለመግባት ለዞንና ክልል አካላት ዕውቅና ፈጥረናል›› ብለዋል፡፡

በፎገራ ወረዳ አንድ የሙዚዬም ማዕከል ላይ እርሳቸውን የሚገልጹ ፎቶዎችና ታሪካቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ የቆየ መሆኑን ገልጸው በወረዳው አስከ አራት መቶ ሰው የሚይዝ አዳራሽ በአለቃ ገብረሐና ስም ለመሰየም እንቅስቃሴ መጀመሩንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታደለ እሸቴ