December 17, 2018e


የአዲስ አበባ መጅሊስ ምክትል ፕሬዝደንትና ዋና ፀሐፊውን ጨምሮ 15 ስራ አስፈፀሚዎች ከስራ ታገዱ።

ሙጂብ አሚኖ ዘ ኢስላም

በአሁኑ ሰአት እየተደረገ ያለው ምርጫ የህዝብን ፍላጎት የማያረካ በመሆኑ የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ በዝምታ አይመለከተውም!

የፌደራል መጅሊስ በትላንትናው እለት የአዲስ አበባ መጅሊስ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩትን ሐጅ ኑርሁሴይን ሙሀመድ ያሲን እና የመጅሊሱ ዋና ፀሐፊ አ/ቶ አዲስን ጨምሮ 15 የስራ አስፈፀሚዎችን ከስራ ማገዱ ተሰማ።

የፌደራል መጅሊስ እነኚህን በህዝብ ይሁንታ ያልተመረጡ ሹመኞችን በአሁኑ ሰአት ከስራ ቢያግድም ባለፉት አመታት ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖረው ሁከት ሲፈጥሩና የተለያዩ ተቀፅላዎችን እየሰጡ ሲፈርጁ የነበሩ በየክፍለ ከተማ ያሉ የመጅሊስ አመራሮች በድጋሚ በአ/አ መጅሊስ በታገዱ ግለሰቦች ቦታ ለመተካት ስብሰባ እያደረጉ ነው።

ታህሳስ 4 /2011ሐሙስ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ በተወያዩበት ወቅት የኮሚቴውን የእስካሁኑ የስራ ሂደት አድንቀው የኮሚቴውን ተግባራት በሚያደናቅፍን የትኛውንም አካል ላይ መንግስት በዝምታ እንደማይመለከት ገልፀዋል። እንዲሁም የኢፌድሪ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ሲባል ኮሚቴው በጋራ የሚወስናቸውን ዉሳኔዎች የመጅሊስ አካላት ጭምር ተቀብለው ሊተገብሩ አንደሚገባ ከስምምነት ተደርሷል። መጅሊስንም በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ለኮሚቴው ተሰጥቶታል።

ይሁንና በዛሬው እለት በታገዱት የአዲስ አበባ መጅሊስ ሐላፊዎች ቦታ ከየክፍለ ለመሾም እየተደረገ ያለው ሒደት ግልፅ አለመሆኑና በእጩነት የቀረቡት ግለሰቦች በአንድ አስተሳሰብ የታጠሩና ያለፉት ጊዜያት ህዝብ ሙስሊሙ መስጂዶችን፣ መድረሳዎችን፣ …የተለያዩ ተቋማትን እንዳያንፅ እንቅፋት ሲሆኑ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸው መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ።

የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ከዚሁ የአዲስ አበባ መጅሊስ አመራሮችን አውርዶ በነባሩ የክ/ከ አመራር መተካት ጋር ተያይዞ የተፈፀመውን ጉዳይ በጥልቀት በመመልከትና ዝርዝር ሁኔታዎችን በማጣራት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ እናስገነዝባለን።

በተያያዘም የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አባል የሆኑትና ከመጅሊስ በኩል የተወከሉት ሐጂ ከድር በአንድ መልኩ ከኮሚቴው ጋር እየሰሩ እንደሆነ ቢነገርም በሌላ ጎን ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ወጣቶችን በማደራጀት እየተከናወነ ያለውን መጅሊስን የማቋቋም ሒደት ለማደናቀፍ እየሰሩ መሆናቸው ታማኝ ምንጫችን አድርሰውናል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ታህሳስ 3/2011 ከሰላም ሚኒስትሯ ከወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ዉይይት ባደረጉበት ወቅት-የኮሚቴውን ተግባራት የሚያደናቅፍን የትኛውንም አካል በዝምታ እንደማይመለከት ገልፇል:: እንዲሁም የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት እና ሰላምን ለማስፈን ሲባል ከኮሚቴው ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።

በሌላም ዜና የአንዋር መስጂድ ኢማም ሸይኽ ጧሃ ልጅ አሚና ጧሃ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በእስር ላይ ትገኛለች። የዚህ መነሻ ምክንያትም በቅርቡ ከአዲስ አበባ መጅሊስ ቢሮ ገንዘብና የተለያዩ ዶክሜንቶች መጥፋታቸውን ተከትሎ ፖሊስ በቅጥር ጊቢው ፍተሻ በሚያደርግ ጊዜ ያልተገባ ሰነድ በቢሮዋ በመገኘቱ ምክንያት እንደሆነ ምንጫችን ገልፆልናል።