ትንታኔ
የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትርክት መፈናቀልን አባብሷል፡፡
“ኢንተርናሽናል ዲሲፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር” የሚባለው እና በዓለም በሀገራቸው ላይ ስደተኛ የሆኑ ዜጐችን ጉዳይ የሚያጠናው ተቋም ይፋ እንዳደረገው ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የስደተኞች ቁጥር ዓለምን ትመራለች:: ተቋሙ እንደገለፀው በፈረንጆች 2018 አጋማሽ ብቻ በዓለም ሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዜጐች ሲፈናቀሉ በኢትዮጵያ ደግሞ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጐች ተፈናቅለዋል:: ይህ አኃዝ ጦርነት ካለባቸው ከነ የመን እና ሶሪያ ሁሉ የበለጠ ነው::
በ2018 አጋማሽ በኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጐች ከሶሪያ በ200ሺህ ይበልጣሉ:: ኢትዮጵያ የፖለቲካ ብልሽት እና የተፈጥሮ አደጋ ከገጠማቸው ሀገሮች ሁሉ በልጣ በሀገር ውስጥ ስደተኛ ብዛት ኡጋንዳን ተከትላ ደግሞ ከአፍሪካ ሀገራት ቀደሚ ሆናለች:: የኢትዮጵያዊያን መፈናቀል ከባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጋር ሲነፃጻር በስድስት እጥፍ እየጨመረ እንደሄደ ጥናቱን ጠቅሶ አፍሪካ ኒውስ አስነብቧል::
የመፈናቀል መንስኤው
የህግና የፌዴራሊዝም ስርዓት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ደሳለኝ በላቸው ይፋዊ ጦርነት ካለባቸው ሀገራት ይልቅ ኢትዮጵያ የራሷን ዜጐች በማሰደድ የምትመራው ቀደም ሲል ሀገሪቱ ስትከተለው በቆየችው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምክንያት ነው ይላሉ :: አሁን እየተሸረሸረ ቢሆንም የኢህአዴግ ርዕዩተ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው::
አቶ ደሳለኝ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በባህሪው የጨቋኝ እና የተጨቋኝ፣ የአሸናፊ እና የተሸናፊነት ሜዳ በማዘጋጀት ህዝቦች በተቃራኒ እና በጐራ እንዲከፋፈሉ ያደርጋል ይላሉ:: ስርዓቱ የተዋቀረበት መንገድም ጥላችን እንደ ፖለቲካ መርህ በተከተለ ቅኝት በመሆኑ “እኛ እና እነሱ” የሚል የማያገናኝ የልዩነት ሸለቆ ተፈጥሯል::
“በአሸናፊ እና ተሸናፊነት ጐራ የተሰናሰለው ስርዓት ሀገሪቱን አሸናፊ ሊያደርግ አይችልም:: ሁሉም ካላሸነፈ ሀገሪቱ አታሸንፍም” የሚሉት አቶ ደሳለኝ መፈናቅሉም ህገ መንግስታዊ መሠረት ያለው ነው ብለው ይሞግታሉ::
በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሆ መሠረት የተቃኘው የየክልሎች ህገ መንግስትም “ነባር እና መጤ” ብሎ ዜጐችን አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ብሎም ይፈርጅሉ ይላሉ አቶ ደሳለኝ::
የክልሎች ህገ መንግስት እና መፈናቀል
ከአማራ ክልል ውጭ ያሉት የብዙ ክልሎች ህገ መንግስት የመሬት ባለቤትነቱን ነባር ብለው ለሚያስቡት ብሔረሰብ ብቻ ይሰጣሉ:: ለአብነት የቤሽንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት ከበርታ እና ከጐሙዝ በእኩል አማራ እና ኦሮሞም በክልሉ ቢኖሩም ለአማራ እና ለኦሮሞ ህገ መንግስቱ እውቅና ይነፍጋል:: ቢሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ አማራ መጤ መባሉ ህገ መንግስታዊ እና ስርዓታዊ ሆኖ ተዋቅሯል ይላሉ::
ስርዓቱ ግጭትን እንደ ፖለቲካ ማራዘሚያ ይጠቅምበት ስለነበር ከሦስት ሺህ ዘመን በላይ በጋራ የኖሩ ህዝቦች መለያየትን፣ መገደደልን፣ መጨካከን ክፉኛ እየለመዱት ይገኛል:: በአንድ ሀገር ውስጥ ልጅና የእንጀራ ልጅ እንዲፈጠር ስርዓቱ በተቋም ደረጃ ሰርቷል:: ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ከኢትየጵያ በመፈናቀል ከዓለም የመጀመሪያ በመሆን ያደፈ ታሪክ እንዲኖራት እያደረገ መሆኑንም አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል ::
በህገ መንግስቱ ጉደይ ጥናት የሰሩት እና “አንቀፅ 39 ” የሚል መፅሐፍ የጻፉት አቶ ውብሸት ሙላትም ህገ መንግስቱ “ታጋይ” ነን የሚሉ ወገኖች ጫካ ላይ እያሉ የፃፉት በመሆኑ የጫካ እሳቤ ይስተዋልበታል ይላሉ:: የህገ መንግስቱን መሻሻል በመፍትሔነትም ይወሰዳሉ::
ህገ መንግስቱ የፈጠረው ህዝባዊ እሳቤ
የዜግነት እና የሀገር ክብር በብሔር ላይ ብቻ ወድቋል:: ከሀገር በላይ ብሔር በመግነኑም ብሔርተኞች ከኔ ወዲያ ሌላው አይመለከተውም ብለው በራሳቸው ግዛት የሚኖረውን የሌላ ብሔር አባል እየገፉት ነው ይላሉ አቶ ደሳለኝ::
አማራን በጠላትነት ፈርጆ የተነሳው ስርዓት ገና ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአማራው ላይ መፈናቀል አስከትሏል:: ይህ መፈናቅል በአማራው ላይ ተጀምሮ ተጠናክሮ ይቀጥል እንጅ ሌሎች ህዝቦችንም አዳርሷል” የሚሉት አቶ ደሳለኝ ህዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩ ህጐችና ስርዓቶች ሠርተው አልፈዋል ሲሉ ያስረዳሉ::
በሰመራ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት መምህር ጌትነት አያሌውም እንደ ስርዓት አማራን በጨቋኝነት ፈርጆ የተነሳው ስልተ መንግስት ጥላቻን አምርቶ በማህበረሰቡ ዘንድ ጥርጣሬን አንግሶ ወደ ማያባራ መፈናቀል መርቷል ይላሉ::
መፈናቀል እና ኢኮኖሚ
ካደጉበት ቀየ፣ ቡና ተጠራርተው ከኖሩበት መንደር፣…. በድንገት ተፈቅሎ መውጣት ስነ – ልቦናዊ ሸክሙ ከባድ ነው:: ይህ የስነ – ልቦና እና የማህበረሰባዊ ትስስር መላላት በተፈናቃዮች ጤና ላይ እክል ይገጥማል:: ጤነኝነታቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃል::
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ – ምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ዶክተር ለጤናህ እጅጉ በተፈናቃዮች ላይ የሚደርሰው መገፋት ጤነኝነታቸው ላይ እንቅፋት ስለሚፈጥር መንግስት ተጨማሪ የጤና ተቋማት ያስፈልጉታል:: ይህ ደግሞ ከመደበኛ በጀት ውጭ በመሆኑ ልማትን ይጐዳል:: መፈናቅል አቅም ያለውን ሰራተኛ በድንኳን እንዲኖር ስለሚያደርግ የሀገር ኢኮኖሚ እንዲንገዳገድ ያደርጋል::
ከሰብአዊ መብት ጥስቱ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ መፈናቅል የስራ ወኔንና ዘላቂ ልማትን በማዳከም እድገትን ቁልቁል እንዲጓዝ እንደሚያደርግ ዶ/ር በጤናው ያስረዳሉ::
የመፈናቀል መፍትሔው ምን ይሆን?
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ጌትነት አያሌው ከህግ አኳያ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2009 የካምፓላ ስምምነትን ተቀብላ ማፅደቅ አለባት ይላሉ:: የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ በካምፓላ በተካሄደ ጉባኤ 40 የአፍሪካ ሀገራት ፈርመዋል:: 27 ሀገራት ፈርመው አፅድቀዋል::
“ኢትዮጵያ ፈረመች እንጅ አላፀደቀችም” የሚሉት መምህሩ፤ ብታፀድቅ ኑሮ ተፈናቃዮች ከዓለም አቀፍ ተቋማት እርዳታ እንዲያገኙ ይረዳ ነበር ይላሉ:: መንግስት ግዴታውን እንዲወጣም ስምምነቱ ያዝዛል ይላሉ:: ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ ምክር ቤት በ1980 ዎቹ ከተቋቋመው የብሔራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁት ኮሚሽን ውጭ በምክር ቤቱ የሚመራ ብሔራዊ የተፈናቀዮችን ጉዳይ የሚመለከት ተቋም ያስፈልጋል ይላሉ::
አቶ ደሳለኝ በላቸው ደግሞ የህግ ክፍተቶችን ማረም፣ ሀገራዊ እና ብሔራዊ ማንነቶችን ማጣጣም፣ ህዝብና ህዝብን ማቀራረብ ተገቢነት እንዳለው ያስረዳሉ::
ተፈናቃዮች ምን አሉ
በዚህ ሰሞን ብቻ ከተለያዩ ክልሎች ከ28ሺ በላይ አማራዎች ተፈናቅለዋል:: መንግስት ለተፈናቃዮች የሰጠው ምላሽ ደካማ እንደሆነም እየተናገሩ ነው:: መምህር እያሱ በርሄ እና የግብርና ባለሙያው አቶ አማረ ዳርጌ ከመደበኛ ስራቸው ከትግራይ ክልል ከሐምሌ ጀምረው ተፈናቅለው ቆቦ ከተማ በድንኳን ኑሯቸውን እየመሩ ነው:: ከቤተሰብ ጋር መገናኘትም ሆነ ወደ ስራ ለመሰማራት ተቸግረዋል:: መንግስትም ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንዳልቻለ ይናገራሉ፤ ለአምስት ወራት ያህልም ያለስራ ተቀምጠዋል::
በአዴፓስ በኩል መፍትሔው ምንድን ነው?
ለዘመናት በተሰራው አማራ ጠል ፖለቲካዊ ትርክት እና አማራ በሀገር ግንባታ ምክንያት በተለያዩ ክልሎች እንደመገኘቱ ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ ልዩ ትኩረትን እንደሚሻ የህግ ባለሙያዎቹ ያሰምሩበታል::
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓም/ መስከረም መጨረሻ አካባቢ ባደረገው ጉባኤ ከክልሉ ውጭ ያለው የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና እንዲያገኝ እስራለሁ ማለቱ ይታወሳል:: ለመፈናቀል መንስኤ የሆነውን የተዛነፈ ታሪክ ለማረቅም እንደሚሰራ ገልጾ ነበር::
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአምና እስከ ዘንድሮ ተፈናቃዮች ከተፈናሉባቸው ቦታዎች ድርስ በመሄድ ምላሽ እየሰጠን ነው ብለዋል:: በዘላቂነት ለመፍታትም አዴፓ መዋቅሩን በሌሎች ክልሎችም ዘርግቷል:: እንደ ቤኒሻንጉል ባሉ ክልሎች ደግሞ የአዴፓ መዋቅር እስከ ወረዳ ድረስ እየተዘረጋ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ለተፈናቃዮች ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት ደግሞ የምግብ እና መጠለያ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ባይሆንም እየቀረበ ነው ብለዋል::
አቶ ንጉሱ መፈናቀሉን ከየክልሎች እና ከፌዴራል መንግስቱ ጋር በመነጋገር እልባት ለመስጠት እንቅስቃሴ ላይ ነን ያሉ ሲሆን፣ለዘላቂ መፍትሄውም እንሰራለን ብለዋል::
በኩር ጋዜጣ
በየሺሀሳብ አበራ ታሕሳስ 08/2011 ዕትም