መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው ለመነጋገር ዝግጁ ነን – አቶ ዳውድ ኢብሳ

On Dec 21, 2018 1,477

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተናገሩ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ በህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ወደ ሀገር ከገባ 4 ወራት መቆጠራቸውን አንስተዋል።

አቶ ዳውድ በመግለጫቸው፥ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ለውጥ የመጣው የኦነግ አባላት፣ የኦሮሞ ህዝብ በተለይም ደግሞ ወጣቱ በከፈለው መስዋእትነት ነው ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል።

ለውጡ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲሸጋገር እና ስልጣን የህዝቡ ሆኖ ህዝቡ በምርጫ ተወካዩን እንዲመርጥ እና ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረትም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ወስዶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦነግ መካከል ጦርነት ነው የነበረው፤ አሁን ግን ኢህአዴግ ለውጡን ወደ ራሱ ተቀብሎ መንቀሳቀስ በመጀመሩ ጦርነት ለማቆም ተስማምተናል ይላሉ።

የመከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊሶች ፓርቲን ሲያገለግሉ ነበር ያሉት አቶ ዳውድ፤ ከመንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት የፀጥታ ሀይሉ ገለልተኛ እንዲሆን የመንግስት እንጅ የፓርቲ እንዳይሆን በሚል መስማማታቸውንም ገልጸዋል።

የኦነግ ሰራዊት በፀጥታ መዋቅር እንዲካተት እና ይህንን የሚስራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከስምምነት እንደተደረሰም ነው አቶ ዳውድ ኢብሳ በመግለጫቸው ያነሱት።

በአሁኑ ወቅት ግን ከመንግስት ጋር የተገባው ስምምነት እየተጣሰ ነው ያሉት አቶ ዳውድ፥ በስልጠና ላይ ያሉ የኦነግ ሰራዊት በአመራር አባላት እንዲጎበኙ አለመፍቀድ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ዳውድ በመግለጫቸው የመከላከያ ሰራዊት የኦነግ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ መስፈሩ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፥ ሰሞኑንም በምዕራብ ወለጋ በመከላከያ ሀይል እና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መፈጠሩንም አንስተዋል።

አሁንም መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንም ነው ሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ የገለጹት።

ምርጫን በተመለከተም አቶ ዳውድ ኢብሳ፥ የቀጣዩ ምርጫ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲካሄድ እንፈልጋለን ብለዋል።