December 23,2018

የህወሃት ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ ከአይሁዶች ምን እንማራለን?
ክንፉ አሰፋ
(የኢትዮፎረም ድረ-ገጽ አዘጋጅ እና ሶፍትዌር ኢንጂነር – አምስተርዳም)

አዛውንቶቹ የህወሃት ቅሪቶች “ለመጨረሻው ፍልሚያ” ትንፋሽ ስበው፣ መሬት ልሰው ነብስ ለመዝራት ሲነሱ እና ሲወድቁ እየተመለከትን ነው። ከተከዜ በላይ እና ከተከዜ በታች ያለውን ወገን በሙሉ “ጠላት” በሚል ጸያፍ ቃል ማጀብ መጀመራቸው ግን የተስፋ መቁረጠቸው ምልክት ይመስላል። ሁሉን የክፋት መንገድ ሞክሮ የስኬትን በር ማየት ለተሳነው ደግሞ በዚህ መጠን የማነሱ አባዜ አዲስ ነገር ሊሆን አይችልም።
ስለ “መጨረሻው ፍልሚያ” ከነሱ ስንሰማ የሚታወሰን የጀርመኑ ናዚ ፓርቲ ነው። በእንግሊዙ ጋዜጠኛ ላውረንስ ሪስ የተጻፈውን “ዘ ሆሎካስት” መጽሃፍ ያነበበ ሰው ህወሃት እና ናዚ ፓርቲ ምን ያህል እንደሚመሳሰሉ ሳይገነዘብ አይቀርም።

“ክፋትን ማደን” (The hunt for evil) የሚለው የአይሁዶች ንቅናቄ የጀመረው ሁለተኛው አለም ጦርነት ባበቃበት ወቅት ነበር። በ 1945 እና በ1949 መካከል(እ.ኤ.አ.)። በአንድ በኩል፣ የናዚ ወንጀለኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የኑረንበርግ ችሎት የዓለምን ቀልብ ስቧል። የሰው ልጅ እንደ እንሰሳ ታጉሮ ለእርድ በሚቀርብበት የአይሁዶች ቄራ የነበረው ኦሽዊትዝ እና በሌሎች መሰል የማጎርያ ካምፖች የተፈጸሙ ወንጀሎች በዝርዝር እየቀረቡ ነው። ካዝናውን ያጨናነቀው ግዙፍ የወንጀል መዝገብ ለኑረንበርጉ ችሎት ለደቂቃም እረፍት ሊሰጡት አልቻሉም። ከዋነኞቹ የናዚ ፓርቲ ተፈላጊዎች ውስጥ ከፊሎቹ ራሳቸውን አጥፍተዋል። ጥቂቶቹ ደግሞ ተሰውረዋል።

የኦሽዊትዝ ማጎርያ አዛዥ የነበረው ካርል አዶልፍ ኢችማን የክሱ መዝገብ ላይ ቢኖርም ደብዛው ግን እንደጠፋ ነው። ይህ ሰው እንደ ፕሮፓጋንዳ ሚንስትሩ ጎብልስ ራሱን እንዳላጠፋ ሞሳድ አረጋግጧል። የኑረንበርጉ ችሎት ኮቴውን ሊያገኝ አልቻለም። የአዶልፍ ኢችማን ስልጣን በናዚ የዕዝ አደረጃጀት ከሂትለር እና ከሂምለር ቀጥሎ ስለነበር፣ ይህ ሰው በጣም ይፈለጋል።

ከጥቂት ወራት በኋላ ከወደ ላቲን አሜሪካ ሰበር ዜና ተሰማ። ኢችማን ጠፍቶ ብዙም አልቆየም። ሞሳድ የተሰነው የእስራኤል የስለላ ድርጅት በረቀቀ መንገድ ከቦይነስ አይረስ፤ አርጀንቲና አፍኖ ወደ እስራኤል ሃገር የመውሰዱ ዜና የአደባባይ ሚስጥር ሆነ። ይህ ሰው ከላቲን አሜሪካ መታፈኑ “ሰበር ዜና” አልነበረም። ግና ለናዚ ብቻ ተብሎ ወደ ተቋቋመው የጀርመን ኑረንበርግ ችሎት ያለመወሰዱ በወቅቱ አለምን አነጋገግሯል። ከአርጀንቲና ታፍኖ በኢል አል አውሮፕላን ወደ እየሩድሳሌም የተወሰደው ካርል አዶልፍ ኢችማን፣ ጦርነቱ እንዳበቃ በደም የተጨማለቀ ልብሱን ቀይሮ አርጀንቲና ውስጥ ቢደበቅም፤ ከሞሳድ ራዳር አላመለጠም።

ኢችማን እንዲህ ባለ መንገድ በህገ-ወጥ ተጠልፎ ሲያዝ እና ወደ እስራኤል ሲወሰድ የህግ አግባብ እየተነሳ አዋራ መነሳቱ አልቀረም። ከህግ ይልቅ ለሞራል እሴቶች የበለጠ ዋጋ የሚሰጠው ምዕራቡ አለም፤ 6 ሚሊዮን አይሁድን ለበላ አውሬ እምብዛም አልተንጫጫም። ካርል አዶልፍ ኢችማን ከ 14 ሳምንታት በኋላ በ 15 የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ በአደባባይ እንዲሰቀል ተደረገ።
ከእኛ ሃገር ለዚህ ሰው አቻ ቢፈለግለት ከደህንነቱ አለቃ ጌታቸው አሰፋ የተሻለ ሊገኝ አይችልም። ከግብረሰዶም እስከ ዘር ፍሬ ማኮላሸት፤ ከአስገድዶ መድፈር እስከ ባውሬ ማስበላት… ለዚያውም በወገኑ ላይ ግፍ እና ወንጀል ፈጽሞ የተደበቀ ሰው።
ኢችማንን የዳኘው የእስራኤል ችሎት፣ የናዚ ትውልድ ስህተት ለአዲሱ ትውልድ ትምህርት ይሆን ዘንድ ነበር እሳቤው። የፍርድ ሂደቱም ቢሆን ነጻና ፍትሃዊ ስለመሆኑ አለም መስክሯል።

የአይሁዶች አደን በኢቼማን ፍርድ ላይ ብቻ አላቆመም። “ናዚ አዳኝ” የሚል ግብረ-ሃይል አቋቁመው በየአለም ጥግ እና ማዕዘናት የተሸሸጉ የናዚ አባላት እና ተባባሪዎችን ጭምር ይለቅሙ ነበር። እየለቀሙም ለፍርድ ያቀርቡ ነበር።

ናዚዎች የ 6 ሚሊዮን አይሁድን ነብስ መቅጠፋቸው ብቻ አይደለም የሚዘገንነው። ወንጀለኞቹ ይህንን በደል የፈሰሙበት እጅግ አሰቃቂ መንገድ እረፍት ይነሳል። የወንጀሉ ግዝፈት ደግሞ ለአዳኞቹ የሞራል ልዕልናን ሰጣቸው። ፍርሃት አልነበረባቸውም። ይሉኝታም ሊኖር አይችልም። ሲችሉ በህጋው አግባብ፤ ሳይቻል ደግሞ በህገወጥ መንገድ እያፈኑ ወንጀለኞቹን በሙሉ ለፍርድ አቅርበዋል።

ይህ ታሪክ ሆኖ አለፈ። እንዲህ አይነቱን የቆሸሸ ታሪክ ሊማሩበት ሲገባቸው ህወሃቶች በወገን ላይ ሳይታክቱ እንደፈሰሙት በብሄራዊ ቴሌቭዥን ጭምር ተመለከትን። ይህ እጅግ ያማል። ድርጊቱ አፈጻጸም ኢትዮጵያውያንን በሙሉ እረፍት ይነሳል።

እርግጥ ነው። ያውም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመውን የበደል ጥግ በአይነ ብረታችን ተመልክተናል። እነዚያ በአስተሳሰብ ከእንሰሳ የማይሻሉ ጨካኞች ከናዚው ኢቼማን የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ቢኖር አረመኔነታቸው ብቻ አይደለም። በደም የተጨማለቀ እጃቸውን እንኳ በደንብ ሳያጸዱ የመደበቃቸው ጉዳይ ነው። ተደብቀውም አላረፉም። እንደ ጅብ ከተከማቹበት ጉድጓድ ሆነው ያለ እረፍት ይሰራሉ። ሀገር ተተራምሳ የደም ጎርፍ እስካላዩ ድረስ እንደማይተኙ እየነገሩንም ነው። የዚህ ቡደን ጥርስ ሲወልቅ እና አከርካሪው ሲመታ እንደ ኢችማን ወንጀሉን ሁሉ ሰርቶ በመሸሽ አላቆመም። ሸሽቶ ድምጽ አላጠፋም። ከተደበቀበት ጉድጓድ ሆኖ አሁንም ህዝብን ከህዝብ ደም ያቃባል።

ህወሃትን ከሂትለር ናዚ የሚለየው በወንጀሉ ግዝፈት ብቻ አይደለም። ናዚ ወንጀሉን የፈጸመው በራሱ ዜጋ ላይ ሳይሆን መጤ ባላቸው በአይሁዶች ላይ መሆኑ ነው። ናዚ ለጀርመን ብሄረተኝነት እና ለጀርመን የበላይነት ሲታገል ህወሃት ግን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እንኳ ለመጥራት የሚጸየፍ ቡድን መሆኑ ከነሱ ይለየዋል። እርግጥ ህወሃት መንግስት አልነበረም። እንደ መንግስት አስልሰራም። እንደ መንግስት አልቆየም። ይልቁንም የተደራጀ ሌባ እና ወንበዴ ቡድን እንደነበር ረፍዶም ቢሆን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተነግሯል።
የፌዴራል መንግስቱ ይህንን ደም የማቃባት ደባ እሰከመቼ እንደሚታገሰው ብዙዎችን ግራ ማጋባቱ አልቀረም። ትግራይ ላይ የተወሸቁ ወንጀለኞች ከህግ በታች መሆናቸውን ማሳየት ፌደራል መንግስት ሃላፊነት አለበት። ይህ የማይሆን ከሆነ ቡድኑ ከኢትዮጵያ በዘረፈው ሃብት ተጠቅሞ ቀጠናውን ሊበጠብጥ እንደሚችል ግልጽ ነው። አፍኝጫችን ስር ተሰባስበው፤ እንደ ቀድሞው እየረገጥን ካልገዛን ተደራጅተን ሃገር እናፍርስ ሲሉ መንግስት ይህን መታገስ የለበትም።

ህወሃት እንደ ናዚ ከምድረ ገጽ መጥፋት ያለበት ድርጅት ስለመሆኑ እስካሁን በወገን ላይ ያደረሰው ግፍ እና በደል ብቻ በቂ ነው። ሌብነትን እንደ ስራ ያስተማረ ቡድን። ሌብነትን በተግባር የኖረበት እና በመጨረሻም ሌቦችን የደበቀ ቡደን ነው ህወሃት። ዛሬ የአኢትዮጵያን ሕዝብ እንደበደሉት ሁሉ ነገም ወገን ያሉትን የትግራይ ሕዝብ እንደሚበሉት ጥርጥር አይኖርም። ድርጅቱን እንደተቋም፤ ሰዎቹን ደግሞ እንደ ጻድቅ የሚያዩ የዋሆች በየዓረናው አቶ አንዶም ገብረስላሴ በመቀሌው መድረክ የደረሰውን አይተው ይፈርዱ ይሆነል። ድርጊቱ ህወሃት እንደ ድርጅት የአንድን ዜጋ ሃሳብ መቀበል እንኳ የሚተናቀው የሃሳብ ድኩማን ስብስብ መሆኑን አስረግጦልናል። አቶ አንዶም ገብረስላሴ ያቺን ሃሳብ ስለተነፈሰ ብቻ “ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ” በሚል ክስ ቢቀርብበት አይደንቅም። ይህ የተለመደ አሰራር ነው። የትግራይ ሕዝብ የሚመጥነው መሪ አላገኘም እንጂ የሌባ እና የወንጀለኞች ተባባሪ እንደልሆነ ግን ለሌላው ግልጽ ነው።

የህወሃት ጡንቻ ፈርጠም ብሎ በነበረ ግዜ አጼ ደብረ ጽዮን፤ “ሁሉንም ሳይሆን ትምክህተኛውን አማራ፣ ሁሉንም ሳይሆን ጠባቡን ኦሮሞ እየነጠልን መምታት ነው ያለብን!” ሲሉ በትግርኛ መናገራቸውንም አንረሳም። ሂትለርም ሰለ አይሁድ ያለው ይህንኑ ነበር። ደብረ ጺዮን ዛሬም ወንጀለኞችን መደበቃቸው ሳያንስ የእንፈልጣለን እንቆርጣለን ፉከራቸውን አላቆሙም። ትምክህተኛ እና ጠባብ የምትለው ወያንያዊ ታርጋ ተለጠፈች እንጂ ሕዝብን በጅምላ መፈረጅ እና መምታት ከናዚ ቀጥሎ ያየነው በህወሃት ቡድን ለመሆኑ ከዚህ በላይ ምስክር ሊመጣ አይችልም።

ናዚዎች አይሁድነትን እንደ ወንጀል ቆጥረው ዘር እንዳጠፉት ሁሉ ህወሃትም አማራ መሆን ወንጀል እንደሆነ በ 1968ቱ ማኒፌስቶው አስፍሮታል። “የትግራይ ሕዝብ ዋናው ጠላቱ አማራ ነው” ሲሉ በማኒፌስቷቸው አስፍረዋል ። ቀጥለውም “አከርካውን ሰረናል። ገለን ቀብረነዋል” ብለውናል። በህወሃት ዘመን አማራነት እና ኦሮሞነት ወንጀል እንደ ነበር ደግሞ ከዘጋቢ ፊልሙ ተገንዝበናል።
ህወሃት በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያደረሰው በደል መትግራይ ሕዝብ ላይ እንደሚደግመው ከመቀለው ጉባኤ ሳይረዱት ይቀራሉ ለማለት ይከብዳል። ከበረሃ ደርበው የመጡት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ኮተት፣ የብሄር ፖለቲካ ጭንብል፣ የልማታዊ መንግስት እንቶ ፈንቶ ሃገሪቷን አንዲት ክንድ እንኳ ወደፊት ሊያስኬዳት እንደማይችል እነሱም ያውቁታል። ከጅምሩ ለሌብነት እንጂ ለፖለቲካ አመራር ያለመነሳታቸውንም አስደንጋጭ በሆነው የዘረፋ ስራቸው በተግባር አሳይተውናል።

የግዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም። ጎዶሎው ቀን አልፎ ግዜው ሲለወጥ ሙሉው ቀን ደግሞ ዳኛ ሆኖ መጥቷል። ገራፊ የሚሳደድበት፤ አሳዳጅ የነበረ የሚደበቅበት፣ ገዳይ ፍርድ የሚያገኝበት ላይ ደርሰናል። በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል እየፈጸሙ እድሜ ልክ መቆየት ያሰቡት ስፍራቸውን ቢለቅቁም ተበዳይ ግን ገና ፍትህን አላገኘም። ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር “መጀመሪያ ይንቁሃል። ከዚያ ቀጥሎ ይስቁብሃል። ገፋ ብለው ይጣሉሃል።… በመጨረሻ ግን ታሸንፋቸዋለህ!”

የጌታቸው አሰፋ ጋኔናዊ ጥፍሮች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ ናቸው። የጭፍሮቹ መርዛኛ አፍም እንደተከፈተ ነው። ይህ ሰው የፍትህን ደጅ ካልረገጠ በቀር ሃገር ሰላም አትሆንም። የፍትህ ሰቆቃ የተሰኘውን ዘጋቢ ፊልም አይቶ ወገን ሲያዝን ጭፍሮቹ ግን ይስቃሉ። በእርግጥ እነዚህ የሞት መልአክተኞች በዚህ ጭካኔ እና ግፍ ቢያዝኑ ነበር ሊገርመን የሚችለው።

ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከሞሳድ እና አይሁዶች መማር ይኖርብናል። ሞሳድ እና አይሁዶች የናዚ ቅሪቶችን እያሳደዱ ፍርድ እንዳቀረቡት ሁሉ፤ ኢትዮጵያዊም እነዚህን ግፈኞች እና ሌቦች ማደን እና ፍርድ ማቅረቡ ላይ መተባባር ይኖርበታል።

ከ 1950 ዎቹ ጀምሮ እስከ 80 ዎቹ ድረስ ሞሳድ አይሁዶችን እንደ ቤተ-ሙከራ አድርገው ግፍ የፈጸሙ የናዚ “የሞት መልአክተኞች” ሲያድን “ጀርመኖችን አሳደዳችሁ” ብሎ የተናገረ አልነበረም። የህወሃት ቅጥረኞች ግን በደለኞቹ እና ሌቦቹ ሲታደኑ የትግራይ ህዝብ ተነካ እያሉ በህዝቡ ላይ የማላዘን ፕሮፓጋንዳ ይሰራሉ። ይህ የተበላበት እቁብ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድም ተናግረዋል። “ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን . . . አድነን ለሕግ ማቅረባችን አይቀሬ ነው!” Sponsored by Revcontent