December 23, 2018
አንዳንድ ታርጋ ለመለጠፍ የሚተጉ ሰዎች “ቱሉ ሊበን ተደመረ” ቢለው ቢያፌዙ አይገርመኝም፤ በሀሳብ ሊሞግቱኝ ካልፈለጉ መብታቸው ነው። ይልቅስ የኔ ታርጋ ኦነግነት ነው፤ ከሀገሬም የወጣሁት በኦነግ ስም ሮሮና ማስፈራሪያ ሲበዛብኝ ነው። ከወያኔ ገበታ ሥልጣኑንም ገንዘቡንም መዛቅ ይቻል ነበር። አልሞከርኩትም። ኦነግነት መንፈስ ነው ብዬ በቅርቡ አንድ መጣጥፍ ጽፌአለሁ። ኦነግነት የኦሮሞ እውነት ነው፤ ፍትህንና ርትእን የጠየቀ ሁሉ በኦሮሚያ ውስጥ ኦነግ ተብሎ ተፈርጆ መከራና ግፍን ተቀብሏል። ተገድሏል፣ ታስሯል፣ ተገርፏል፣ ተሰዷል፤ ምንም ያልሆነው ነገር የለም። ለኦነግ ሕዝባችን ትልቅ ክብርና ፍቅር አለው። ይህን ፍቅርና ክብር በአግባብ አለመጠቀም ትርፉ ውርደትና ፀፀት ይሆናል።
ኦነግ ማለት ለኔ ሸኔ ማለት አይደለም ወይም አንዱ የኦነግ እንጃ ማለት አይደለም። ከዳውድና ከሌንጮ፣ ከገላሳና ከከማል ኦነግ ወዘተ ይኸኛው ይሻላል ብዬ ፍርድ መስጠትም አልፈልግም። ፍርዱን ለታሪክ እንተወው። የኦነግ መሪዎች ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል ይነስም ይብዛም አዎንታዊ ድርሻ አበርክተዋል ብዬ አምናለሁ። ኦነግ ባይፈጠር ኖሮ ቄሮ አይፈጠርም ነበር ብዬም አምናለሁ። የኦነግ መሪዎች ሰዎች ስለሆኑ በትግል ውስጥ ባለፉባቸው ዘመናት ስህተት የሠሩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ኦነግን ከፋፍለው የኦሮሞን ትግል ማቀጨጫቸው ራሱ ትልቅ ስህተት ነው።
ይልቅ በዚህ ሰዓት ሊያሳስበን የሚገባው ያለፈው ስህተታቸው ሳይሆን አሁን የሚሠሩት ስህተት ነው። አሁን በኦቦ ዳውድ ኢብሳ ሸኔ-ኦነግ በኩል ያለው ግርግር እያሳሰበን ነው። ከሎጂክ በመነሳት እንጠይቅ። በምን ሂሳብ ነው በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብሎ ለውጥን የተቀላቀለ ኃይል ሰራዊት አለኝ፣ ነጻ መሬት አለኝ፣ ትጥቅ አልፈታም ብሎ የሚከራከረው? ተወደደም ተጠላም በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት ሠራዊት አያስፈልግም። አይቻልምም። ኦሮሞ እንደ ሕዝብ ትጥቅ አይፍታ፤ በሌሎች ክልሎች ከሕዝብ ትጥቅ እየተፈታ አይደለምና ማለትና ድርጅቴ ትጥቅ አይፍታ ማለት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ይልቅስ ሠራዊቱን እንዴት ሕዝባዊና ህብረ ብሔራዊ ማድረግ ይቻላል በሚለው አጀንዳ ላይ መከራከር ይቻላል።
መቀሌ የመሸጉ ጉግ ማንጉግ የወያኔ ወሮበሎች የአብይን መንግስት እያብጠለጠሉ ሸኔ-ኦነግን ጉራ ወሸባዬ፣ ፊንፊኔ ልትገባ 70 ከሎ ሜትር ቀርቶሃል በርታ ሲሉት በኦሮሞ ሕዝብ ፍቅር ወድቀው ነው ብለን ራሳችንን ልናጃጅል እንችለን? ትናንት ኦፒዲኦን ጠፍጥፈው በኦሮሞ ስም የሠሩልን ወራሪዎች ዛሬ ሌላ ኦፒዲኦ ኦነግ በሚል የዳቦ ስም ጠፍጥፈው እንዲሠሩልን አንሻም።
አሁን ያለው ሠራዊት የወያኔ ነው በሚል ሰበብ ለውጡ ፈር እንዲለቅ ሰበብ ማብዛት አይጠቅመንም።
ሸኔ-ኦነግ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት የወያኔ ሠራዊት ነው፤ አይስማማኝም ካለ ወደ ሀገር ቤት መግባት አልነበረበትም ወይም ጣጣውን እዚያው አስመራ ሳለ መጨረስ ነበረበት። ሕዝባችንን ስንት ዘመን ሰላም ናፍቆታል። በኦነግ ስም ያላየው ፍዳ የለም። አሁን ኦነግ ተመልሶ መጣ ሲባል እንደገና ሌላ ቀውስ ውስጥ ሊገባ አይገባውም።
በግርግርና በአመፅ ለዚያች ሀገር የተሻለ ሥርዓት አመጣለሁ ብሎ የሚጃጃል ቡድን ካለ ራሱን ብቻ ነው የሚያታልለው። መንግሥትን ማዳከምና መጣል ይቻል ይሆን ይሆናል፤ ሰላምን ማምጣት ግን አይቻልም።
ኦነግን ከሽግግር መንግሥቱ ያባረረው፣ ሲያሳድደው የነበረና በአሸባሪነት የፈረጀው ህወሃት ሆኖ ሳለ የሕወሃቱ ራስ ስብሃት ነጋ በመቀሌ ላይ ለሸኔ-ኦነግ ታጣቂዎች ሞቅ ያለ አቀባበልና ድል ያለ ግብዣ አድርጎ አርማውን ከፍ አድርጎ ይዞለት ወደ ፊንፊኔ ሲሽኘው እያየን በምን ሞራል ነው ሸኔ-ኦነግ ኦዴፓን የወያኔ ተላላኪ ነው ብሎ ቡራ ከረዩ የሚለው?
አብይን ሊገድለውና ሊያጠፋው ሌት ተቀን የሚተጋው ወያኔ ሆኖ ሳለ አብይንና ለማን የወያኔ ተላላኪ ናቸው ብሎ ፕሮፓጋንዳ መስራት ለኦነግ ክብርና ደረጃ ጥሩ አይደለም።
ትናንት ኦህዴድ የወያኔ ተላላኪ ነበር፤ ምንም ክርክር አያስፈልግም። ዛሬ ግን አይንና ሃጫ ሆነው ሳለ፣ የአብይ መንግሥት የወያኔ ገዳዮችንና ዘራፊዎችን ለፍርድ እያቀረበ ሳለ የአብይን መንግሥት ፀረ ኦሮሞና የወያኔ ተላላኪ አድርጎ ማቅረብ ውሃ አይቋጥርም። ይልቅ የራስን ስህተት አርሞ በህዝብ ዘንድ የሚሸጥ አጀንዳ ይዞ መቅረብ ብልህነት ነው። ለሀገራችን በዚህ ሰዓት በየትኛውም መስፈርት በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊትም ሆነ በዓለም ህብረተሰብ ፊት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ እርምጃ ሊመራ የሚችለው የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ወይም የብርሃኑ ነጋ አርበኞች ግንቦት 7 ወይም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አይደለም። ለምን ቢሉ በሁሉም ላይ ሕዝቦች ጥርጣሬ አላቸውና። ሁሉም የመቻቻል ፖለቲካ ላይ ጥያቄ አለባቸው። ምናልባት አቅም የለውም እንጂ የዶር መረራ ጉዲና ኦፌኮ መድረክ የሚባለውን ስብስብ ይዞ ያን ሀገር እንደ ሀገር ለማቆየት አሁን ካለው ኦዴፓ/ኢህአዲግ ቀጥሎ አማራጭ ሊሆን በቻለ። ዳሩ ይህ ስብስቡ ተኝቷል። በምን ጠብቀው ቁመና ላይ አይደለም።
የአብይ አህመድ መንግስት ሁሉንም የሕዝቦችጥያቄ መልሷል ወይ? አልመለሰም። በወራት ዕድሜ ውስጥም የዘመናትን ክምር ችግር እንዲፈታ አይጠበቅበትም። አንዳንድ የሕዝብ ጥያቄዎችንም ኦዲፒዎች ከአቅም ማነስም ይሁን በፖለቲካ ስሌት ሲያዘገዩ እናያለን። ድክመታቸውን በግልፅ ነቅሰን ልንተቻቸው ይገባል። የኦሮሞም የሌሎች ኢትዮጵያውያን ጠላት ግን አይደሉም። ኦህዲዶችን በማብጠልጠል ስንትና ስንት መጣጥፍ ከዚህ ቀደም ጽፌአለሁ። አሁንም ከመፃፍ አልቦዝንም።
ኦዴፓ በሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ አሸንፎ ሀገር ቢመራ ወይም በምርጫ ከሥልጣን ቢባረር ግድ የለኝም። አሁን ግን የለውጥ ኃይሉን መደገፍ ሀገርን ማዳን ነው ብዬ አምናለሁ። ዝርዝር ውስጥ አልገባም። የለውጥ ኃይሉ እኔ በምፈልገው መንገድ ስላልሄደ መንግሥት ይፍረስ፤ ሀገር ይበጥበጥ ማለት ነውር ነው። ለሀገራችን የሚበጀው የአብይን መንግስት ድክመት እያረሙ፣ እየነቀሱ እየሞገቱ ሽግግሩን ማጎልበት እንጂ ይህን መንግስት ጠልፎ መጣል አይደለም።
በሀገራችን የመጣው ለውጥ የሕዝቦች ትግል ውጤት ነው። በግንባር ቀደምነት የቄሮ ውጤት ነው። በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ድርሻ ነበራቸው። ብዙ የሲቪል ኃይሎችም ወያኔን ለመጣል ድርሻ ነበራቸው። ይሁንና ከሥርዓቱ ውስጥ ተራማጅ ኃይል ባይወጣና የህዝቡን ትግል ባይቀላቀል ኖሮ ወያኔ መውደቁ ባይቀርም ሀገራችን ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ እንደሚትገባ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ስለዚህ የሸኔ ኦነግ መሪዎች ክብራቸውን ጠብቀው፣ እንደ ጎረምሳ ሳይሆን እንደ ሽማግሌ በእርጋታ አስበው የኦሮሞን ጥቅምና ሰላም በሚያስጠብቅ መልኩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይገባቸዋል።
ቸር እንሰንብት
እውነቱን ለመናገር የሞራል ግዴታ አለብን፡ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን መንግስት የምንደግፈው ለቅንጦት አይደለም። ፍርፋሪ ለመቀላወጥ፣ ለመሬትና ለስልጣንም አይደለም። ለሀገራችን ህልውና ሲባል ብቻ ነው።
