December 25, 2018

የአዳማ/ናዝሬት ከተማ በአብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ የሆነ ማህበረሰብ ነው። ባለፉት ከአሥር ስሎስት አመታት በፊት በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት ከከተማዋ ነዋሪ 60% የሚሆኑት አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሆን፣ 25% ኦሮምኛ፣ 15% 6% ጉራጌኛና 9% ደግሞ ከአማርኛ፣ ከኦሮምኛና ከጉራጌኛ ውጭ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የአፍ መፍጫቸው ቋንቋ ያላቸው ናቸው። ይሄም የኢያሳየው አዳም/ናዝሬት ብዙ ብሄረሰቦች ተደባልቀው የሚኖሩባት፣ ሕብረብሄራዊ ከተማ መሆኗን ነው።
ሆኖም አሁን አሁን አለው አወቃቀር አዳማ የኦሮሞ ክልል አካል በመደረጓ፣ የክልሉን የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆን በመደረጉ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪው የከተማ አንድ አራተኛ ብቻ ቢሆንም በከተማዋ አስተዳደር፣ በቀበሌ፣ በወረዳ ተመረጭና ተቀጣሪ ሆነው የሚሰሩት ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ብቻ ናቸው።
ይሄ አፓርታዳዊና ዘረኛ አሰራር የከተማዋን እድግት በማቀጨጩ ባሻገር ፣ የሕዝቡን ዲሞክራሲያዊ መብትን የረገጠ፣ ዜጎች በአገራቸው ሁለተኛ ዜጎች እንዲሆኑ ያደረገ መቀየር ያለበት አሰራር እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ አዳማ/ናዝሬት በፌዴራል ስር እንድትሆን በመጠየቅ ፣ በአዳማ/ናዝሬት ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚከተለው አቅርቢታል-
ሠሞኑን በአዳማ/ናዝሬት ለ4 ቀን የነዋሪዎች ስብሰባ ተደርጎ ነበር፤ የሚገርመው ነገር በከተማው በነዋሪነታቸው የማውቃቸው አንድም ሠው አለማየቴ አሳዝኖኛል፡፡ ሁሌም በከተማው የነዋሪዎች ስብሰባ በተደረገ ቁጥር ከመቆርቆር ጀምሮ ዛሬ እስከደረሰችበት ድረስ ከተማዋን ያቀኑና ለዚህ ያበቋት ነዋሪዎች መገፋት በእጅጉ ያሳስባል፡፡
በየጊዜው በከተማዋ የሚታዩት ነገሮች ለከተማዋ ዕድገት እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር ትክክለኛው የከተማው ነዋሪ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ቦታ እየተሰጠው አይደለም፡፡ ስለ ከተማዋ ሁሌም ውይይት ይኖራል፤ግን ሁሉን አሳታፊ አይደለም፡፡ እርስ በእርስ እየተመራረጡ ከመወሰን ውጪ የነዋሪውን ስሜትና ፍላጎት በጥልቀት የሚያውቅ አይደለም፡፡ ለልማት እና ለማይረቡ ጉዳዮች ግን የከተማው አስተዳደር እያንዳንዱን ነዋሪ ይፈልገዋል፡፡
ቋንቋ ሀገርም ሆነ ከተማ አይለውጥም፤የብሄርና የቋንቋ ጉዳይ ለሃገሪቱ ፈተና ሆኗል፡፡በየቀበሌውና በየመሥሪያ ቤቱ የሚቀጠሩት ሠራተኞች ለሥራውና ለከተማው አዲስ እየሆኑ መታወቂያ ለማደስ እንኳን ነዋሪው ለወር ለአስራ አምስት ቀን እያመላለሱ ነው፡፡ ለከተማዋ ወሳኝ ጉዳዮች ወሳኞች እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ከወለጋ አሊያም ከቦረና የመጣ ግለሰብ ከተማዋን ጠንቅቆ ሳያውቅ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናል፡፡ ሥራውን በአግባቡ ከማከናወን ይልቅ ባለመብት እሱ ብቻ መስሎት ያሻውን ቢሆን የሚጠይቀው የለም፡፡
ብዙዎቹ በየክፍለከተማውና በየቀበሌው ያሉት የአስተዳደሩ ሠራተኞች የሚቆጣጠራቸው የለም፡፡ ቅሬታ ማሰሚና የህዝቡን ብሶት ማዳመጫ የለም፡፡ አዎን! ከህዝቡ ሥልጣኔና ከከተማዋ ዕድገት ጋር የከተማው አስተዳደርና ሠራተኛው እየተግባቡና እየተመጣጠኑ አይደለም፡፡ ሩቅ ለሩቅ ናቸው፡፡ የከተማዋ የብልሹ አስተዳደር ክፍተቶች በየጊዜው እየሠፉ መጥተዋል፡፡ አጭበርባሪውና ሙሰኛውም የዚያኑ ያህል በርክቷል፡፡ ግዛቴ ነው የሚል ፍንጭ ያሳይሃል፡፡ አዳማ በፌዴራል ደረጃ እንድትመራ ለዓመታት ነዋሪው ሲቋምጥበት የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ግን ሊሳካ አልቻለም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳልኩት ሙስና በግልፅ ትጠየቃለህ፤የጎጥ ለቃቃሚ እንኳን ሲኩራራብህ ታዝናለህ፡፡ ለመንግሥት ደግሜ የምናገረው ነገር ከከንቲባው እስከ ታችኛው የጎጥ መዋቅር ፈርሶ እንደገና መዋቀር አለበት፡፡ የከተማዋ ችግር ሥር የሰደደ በመሆኑ ትኩረት ተደርጎበት ሊሰራ ይገባዋል፡፡
181
