የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ሁነት) አሁን ማምሻውን ከግንቦት 7፣ ከኦነግ፣ ከሰማያዊና ከአብን ተወካዮች ጋር የደረገውን ውይይት ተከታትየ ነበረ፡፡

የኦነጉ ተወካይ ኦነግ ለምን እንደተመሠረተ ተጠይቀው ሲመልሱ “በቋንቋችን እንዳንናገር፣ ባሕላችንን ማንነታችንን እንዳንጠብቅ እንዳንንከባከብ ተከልክለን ስለነበር በቋንቋችን የመጠቀም መብታችንንና ባሕላችንን ማንነታችንን ለማስከበር ነው ኦነግን መሥርተን የታገልነው!” ብለው ተናገሩ፡፡

በዚህ የኦነጉ ተወካይ በተናገሩት ላይ አቶ አንዳርጋቸው እንዲጨምሩበት ሲጠየቁ “የነበረው ግፍና በደል ከዚህም በላይ ነው ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ የነበረው ሕዝብ ጭሰኛ ነበር፡፡ ጭሰኝነቱ ከባርነት ያልተናነሰ ነበረ…!” እያለ ምንም በማያውቀው ጉዳይ ቀበጣጠረ፡፡

እጅግ በጣም ያሳዝናል!!! ለመሆኑ መቸ የትና በምንስ ሁኔታ ነው ኦሮሞም ሆነ ሌላ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ “በቋንቋቹህ አትናገሩም፣ ባሕል ማንነታቹህን አትጠብቁም!” ተብሎ የተከለከለው??? እስኪ በሉ ዝም ብሎ በባዶ አሉባልታ ሳይሆን በተጨባጭ መረጃቹህን ይሄ ይሄ ብላቹህ አቅርቡ???

ይታያቹህ እንዲህ ብለው የሚከሱት የጃንሆይ መንግሥት እኮ ከብሔራዊው የኢትዮጵያ ራዲዮ በተጨማሪ ዝግጅቶቹን በኦሮምኛ ብቻ የሚያቀርብ የሐረር ራዲዮ ጣቢያ ከፍተው ለቋንቋው እድገት ስንት አስተዋጽኦ ያበረከተውን፣ ባሕላቸውን ለመንከባከብ የባሕል የሙዚቃ ቡድን እያቋቋሙ ስንት የደከመውን መንግሥት እኮነው “በኦሮምኛ መናገር፣ ባሕል ማንነታችንን መጠበቅ መንከባከብ ስለከለከለን!” ብለው የሚከሱት፡፡ ኦነግ የተመሠረተው የጃንሆይ መንግሥት ሊወድቅ አንድ ዓመት ሲቀረው መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡

የጃንሆይ መንግሥትም ሆነ ከዚያ በፊት የነበሩ መንግሥታት ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን በቋንቋቸው እንዳይናገሩ የከለከሉ ከሆነ እንዴት ታዲያ አሁን ቋንቋቸው ብቻ ሳይሆን ባሕላቸው ማንነታቸው በዚህ ዘመን ሊገኝ ቻለ??? መሬት ውስጥ ቀብረው አስቀምጠውት ቆይተው ነው እነ ነፈዞ??? ኧረ ተው ኧረ ተው ግፍን ፍሩ??? ጥቂትም እንኳ ይሉኝታ ይሰማቹህ???

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም ሲያጋግል ይሄንን ሐሰተኛ ክስ በመቀበል ጭራሽ እንዲያውም “ግፉ ከዚህም በላይ ነው!” ብሎ ስለ ጭሰኝነት በማውራት አማራን ግፈኛ ለማስመሰል ጥረት ማድረጉ በጣም ገርሞኛል፡፡ ይሄ ሰውየ መቸ ነው ግን የሚታረመው??? የአብን ተወካይ የተባለውም ይሄንን ሐሰተኛ ክስ መከላከል ወይም ማስተባበል አለመቻሉም በጣም አስከፍቶኛል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ለመሆኑ ጭሰኝነት ኦሮሚያና ደቡብ ባልከው የሀገሪቱ ክፍል ብቻ ነው የነበረው??? በአማራስ አልነበረም ወይ??? በአማራ ሕዝብ ላይም ጭሰኝነት እንደነበረ እየታወቀ ኦሮሞዎችንና ደቡቦችን ብቻ በመጥቀስ አማራን የበደለ ማስመሰሉ ለምን አስፈለገ አንተ ፀረ አማራ ወንበዴ???

ጭሰኛ ጭሰኛ ትላለህ እንጅ ስለጭሰጭነት ምንም ሳታውቅ ዝም ብለህ አፍህን እንደምትከፍት አሁን ላረጋግጥልህ እችላለሁ፡፡ ኦሮሚያና ደቡብ ባልከው የሀገሪቱ ክፍል ጭሰኝነት የተፈጠረው ዐፄ ምኒልክ 2ኛ ኢትዮጵያን መልሶ አንድ ለማድረግ ኦሮምያና ደቡብ ወዳልከው የሀገሪቱ ክፍል መዝመታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ በአማራ ግን ከዚያ ዘመን በፊት ለረጅም ዘመናት ጭሰኝነት ነበረ፡፡

ኦሮሚያና ደቡብ ባልከው ግን በተለይም ከአድዋ ጦርነት መልስ የዚያ ዘመኑ የመንግሥት ጦር ደሞዝ ስለሌለውና የአገልግሎቱ ክፍያ መሬት ስለነበረ በአድዋው ጦርነት ለተሳተፈው አርበኛ ኦሮሚያና ደቡብ ባልከው የሀገሪቱ ክፍል መሬት እየተሰጠው ተመራ፡፡

ይሄም ሲባል ደግሞ በነዚህ ስፍራዎች መሬት የተሰጠው የዐፄ ምኒልክ ሠራዊት አርበኛ (ነፍጠኛ) አማራ ብቻ እንዳይመስልህ፡፡ አቶ አሰፋ ጫቦ ነፍሳቸውን ይማረውና ኦሮሚያና ደቡብ ባልከው የሀገሪቱ ክፍል የደም ዋጋ ተብሎ መሬት ከተሰጠው የዐፄ ምኒልክ ሠራዊት (ነፍጠኛ) ውስጥ 95 ከመቶ የሚሆነው ኦሮሞ እንደነበር አቶ አሰፋ ጫቦ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡

ይሄንን ብቻ አይደለም አቶ አሰፋ ጫቦ በጥልቅ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ያረጋገጡት፡፡ ዐፄ ምኒልክ የተረሳውንና በግራኝ አሕመድ አውዳሚ ወረራ ምክንያት ማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ተዳክሞ ከማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሆኖ የቆየውን ኦሮሚያና ደቡብ ያልከውን የሀገሪቱን ክፍል መልሰው ለመቀላቀል ከመዝመታቸው በፊት ኦሮሞዎች ባደረጉት መስፋፋት በርካታ ነባር ጎሳዎችን ባሕል ቋንቋዎቻቸውን በኃይል አጥፍተው ኦሮሞ እንዳደረጓቸውና እምቢ ያሉትንም ከሞቃዲሾ እስከ ታጁራ በተዘረጋው የባሪያ ንግድ እያጋዙ ለባርነት ይሸጧቸው እንደነበረ ጭምር ከመረጃ ጋር አሳምሮ ጽፎታል፡፡ ይሄንን ግፍ ያስቆመው የዐፄ ምንሊክ ሀገሪቱን እንደገና ለመቀላቀል ያደረጉት ዘመቻ ነው፡፡

እናም አቶ አንዳርጋቸው እባክህን ይሄንን ግልብ መረዳትህን ይዘህ አትደንፋብን ተሳስተህ ሕዝብ እያሳሳትክ ነው፡፡ ከያ ትውልድ ጋር ሆነው ይህችን ሀገር የቀበርካት ይበቃሃል አንተና መሰሎችህ ከፖለቲካው ውጡልን!!! መቸም የምትማሩና የምትታረሙ አይደላቹህምና!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com