አብን በአማራ ሕዝብ ላይ አስቀያሚና አደገኛ ቁማር መቆመሩን አንድ ብሎ የጀመረው መጭው ምርጫ
እንዲራዘም የማይፈልግ መሆኑን አቋም በመያዝ ከዐቢይ አሥተዳደር ወይም ከወያኔ/ኢሕአዴግ
ጎን በመሰለፍ ነው፡፡
ለነገሩ አብን “ለአማራ ሕዝብ መብት ነጻነት ጥቅም ህልውና ደኅንነት ቆሜያለሁ!” እንደማለቱ መሰንበቻውን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎቹ ላይ በአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን ለማስቆምና መብታቸውን ለማስጠበቅ የአጋርነት መግለጫ ለማውጣት እንኳ ሲያዳግተው ሲታይ፣ እንደ ክትባት ባሉ የአማራን ዘር የማጥፋት ስውርና አደገኛ እንቅስቃሴዎች ጉዳይ በያገባኛል ስሜት የሕዝቡን ሥጋት ሊቀርፍ በሚችልና
መተማመን ሊፈጠር በሚያስችል ደረጃ አለመንቀሳቀሱ በአማራ ሕዝብ ዘንድ የአብን የአማራ ድርጅትነት
ጥያቄ ውስጥ እንደገባና እያስጠረጠረው እንዳለ በግልጽ እያየን ነው፡፡
አሁን ደግሞ ጭራሽ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጎን ተሰልፈው ማንነታቸውንና ለማን እንደሚሠሩ ይበልጥ ግልጽ አድርገውት ቁጭ አሉ፡፡ እጅግ የሚገርመው ደግሞ “ምርጫው መራዘም የለበትም!” የሚል አቋም ለመያዛቸው በምክንያት ለማስደገፍ የሔዱበት እርቀት ነው፡፡ የጠቀሷቸው ምክንያቶች አስመሳይነታቸውን ይበልጥ ግልጥ አድርጓል፡፡
ምክንያት ብለው የጠቀሷቸው ምክንያቶች ምርጫው የግድ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ መሆን እንዳለበት
የሚያስገድዱ እንጅ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ በማያስችል በማያመች ሁኔታ ላይ የይስሙላ ምርጫ እንዲደረግ የሚያስገድዱ አይደሉምና ነው፡፡
ወያኔ/ኢሕአዴግ አሁን ያለው ሀገር አቀፍ ችግር “አወናብዶ ለማለፍ ያመቸኛል!” ብሎ ስለሚያምን ስለሚያስብ ግጭቱ፣ አለመረጋጋቱ፣ አለመተማመኑ፣ ባልተፈታበት ባልተቀረፈበት ሁኔታ መጭው ምርጫ በተያዘለት ጊዜ እንዲደረግ ይፈልጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ይሄንን በየቦታው
የሚቀሰቅሰውን ግጭት፣ አለመረጋጋት፣ አለመተማመን እስከምርጫው ድረስ ይዞት ሊሔድ ይፈልጋል፡፡
ወያኔ/ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን “ግርግሩ፣ ግጭቱ፣ አለመረጋጋቱ፣ አለመተማመኑ፣ ቀውሱ ተጠቃሚ ያደርገናል!” ብለው ያሰቡ ኦነግና ሌሎች ኦሮሞን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶችም በሙሉ ምርጫው በምንም ምክንያት መራዘም ሳያስፈልገው በተያዘለት ጊዜ እንዲደረግ ይፈልጋሉ፡፡
አብኖች ምርጫው መራዘም የለበትም ለማለታቸው የጠቀሷቸው የተቀባቡ ምክንያቶች የሚከተሉት ቸው፦
የአማራ ሕዝብ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ተደርጎ እኛ እንድንመራው ስለሚፈልግ፣ ምርጫው እንዲራዘም
መደረጉ የአማራን ሕዝብ የመከራ ዘመን ስለሚያራዝም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕዝብ ቅቡልነት በሌለው መንግሥት መመራት ስለሌለበት፣ ከክልሉ ውጭ ከባርነት ባልተናነሰ አኗኗር የሚኖረውን አማራ ከዚህ መከራ ቶሎ ለመታደግ፣ በአጠቃላይ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል ለማድረግ ትክክለኛ የአማራ ሕዝብ ወኪል ስለሚያስፈልግና ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በምርጫ ስለሆነ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ መደረግ አለበት።
በማለት የምርጫ መራዘም ሐሳብን እንደማይቀበሉና ከዐቢይ ጎን በመቆም በተያዘለት ጊዜ እንዲደረግ
እንደሚፈልግ አብን አስታውቋል፡፡
አየ እነ አብንiii ጥያቄው እኮ በዚህ አጭር ጊዜ የለውጥ እንቅፋቱን ኃይል በቁጥጥር ስር አውሎ ሀገር ጫታ ሆኖ፣ መረጋጋት ተፈጥሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የእምነተ አሥተዳደር ቡድኖች) በመላ ሀገሪቱ በነጻነት ተዘዋውረው ማኒፌስቷቸውን (አቅደ ዓላማቸውን) ለሕዝብ ማስተዋወቅ የሚችሉበት ሁኔታን መፍጠርና ነጻ
ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ወይ??? ፣ የሕግ አካላትን ከወያኔ/ኢሕአዴግ አገልጋይነት አላቆ የሕዝብ አገልጋይ ማድረግ ይቻላል ወይ??? ፣ አምስት መቶ ሽህ የወያኔ ካድሬ (ወስዋሽ) ምርጫ አስፈጻሚው
በሙሉ ተቀይሮና የሚተኩት ነጻና ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችም የምርጫ አፈጻጸም ሥልጠና ወስደው ዝግጁ በማድረግ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ወይ??? ነው እኮ ጥያቄው እንጅ ይሄንን ማድረግ ቢቻልማ የሕዝብ ፍላጎትኮ ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ ሳይሆን ነገውኑ ምርጫ ቢደረግ ነው ፍላጎቱ፡፡
ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ይሄንን ማድረግ የማይቻል በመሆኑና በዚህ አጭር ጊዜ ያሉ ችግሮች ሁሉ ተቀርፈው አንድም ምክንያት የማይጠቀስበት ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሮ ምርጫ ማድረግ የማይቻል በመሆኑ ነው ይራዘም እየተባለ ያለው፡፡
የሕዝብ ፍላጎት ይሄ ነው እንጅ “የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል!” እንዲሉ ሕዝቡ ፍርሐቱ ሳይለቀው፣ መሸማቀቅ ስሜት እንደተጫነው በየአቅጣጫው በሚፈጸሙ ግርግሮች እየተዋከበ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ በማያስችል ሁኔታ ምርጫ ተኪያሒዶ ወያኔ/ኢሕአዴግ “አሸናፊ ሆንኩ!” ብሎ
የሚወጣበትን ሁኔታና እንደገና ወደቀውስ የምንገባባትን ሁኔታ አይደለም ሕዝብ የሚፈለገው፡፡
ሀቁ ይሄ ሆኖ እያለ “ሁኔታዎች ምቹ ይሁኑ አይሁኑም ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መፈጸም አለበት መራዘም የለበትም!” ብሎ ማለት ይሄ አንድና ሁለት የሌለው ቅጥረኝነት ነው፡፡ ቢያንስ እንኳ “እስከዚያ ጊዜ ድረስ ችግሮች ከተፈቱ!” የሚል ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጡ እንኳ አንድ ነገር ነበረ፡፡ እነሱ ግን ቅጥረኞች ናቸውና ይሄንን ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጡ ምንም ይሁን ምን ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መደረግ አለበት የሚል አቋም ያዙ፡፡
ወይኔ ወገኔ! የማንም ቁማርተኛ መጫወቻ መሆኑ ብቻ ነው የሚያንገበግበኝ፡፡ ይሄ የአብን አቋም ምን ማለት እንደሆነ የአማራ ሕዝብ ይጠፋዋል ብየ አልገምትም፡፡ እውን አብን ወያኔ የአማራ ክልል ብሎ ከሚጠራው ጭ
ያለው የአማራ ሕዝብ ደኅንነትና ህልውና የሚያሳስበው ቢሆን ኖሮ ይህ ያለው ችግር ተቀርፎ ወያኔ የኦሮሞ ክልል በሚለውና በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ያለውን አማራ አደራጅቶ “መብቱን ማስጠበቅ፣ የሚወክለውን ተመራጭ ማቅረብ የሚችልበት ሁኔታ የግድ መፈጠር አለበት!” ብሎ አቋም ይይዝ ነበር እንጅ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ ይፈልግ ነበረ ወይ??? ዛሬ ማንም እንደሚያውቀው አማራ ኦሮሚያ ሚሉት
መብቱን ከሚያስጠብቅለት የአማራ ፓርቲ ጎን በነጻነት የሚቆምበት ሁኔታ ሊኖር አይደለም እንደሰው እንኳ ተረጋግቶ መኖር የማይችልበት መራራ እውነታ በሰፈነበት ሁኔታ ነጻነትና ምቹ ሁኔታ ያለ በማስመሰል ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መደረግ አለበት!” ማለት በአማራ ሕዝብ ላይ አደገኛና ይቅር የማይባል ክህደት መፈጸምና በበርካታ ሚሊዮኖች (በአእላፋት) በሚቆጠሩ ወያኔ የአማራ ክልል ከሚለው ውጭ በሚኖሩ አማሮች ነፍስ መቆመር ነው፡፡
እጅግ በጣም ያሳዝናል!!! የአማራ ሕዝብ ሆይ! ብአዴን በነፍስ በሥጋህ ተጫውቶብሃል፡፡ ትክክለኛ የሚወክልህን ፓርቲ አቋቁመህ ለምርጫ እንዳትቀርብ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ብን ያድርጋቸውና
ብአዴን ካድሬዎቹን (ወስዋሾቹን) እና ሆዳሞችን ሰብስቦ አብን የሚባል ብአዴን ቁጥር ሁለትን አቋቁሞ
አቀረበልህ፡፡ እውነት መስሎህ ስትቀበል አብን የተባለው ተመሳስሎ ለአገዛዙ እንዲሠራ የተመሠረተ ሆኖ ተገኘ፡፡
አብዛኛው አማራ ይሄንን ለማረጋገጥ ገና ጊዜ የሚፈጅበት መሆኑ ነው አሳዛኙ ነገር፡፡ በዚህም ምክንያት ቶሎ ነቅቶ ትክክለኛ የሚወክለውን ፓርቲ በሐቀኛ ልጆቹ አቋቁሞ ለምርጫ መቅረብ ሳይችል መቅረቱ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት አማራ ገና ገና ብዙ ብዙ አሳር መከራ አለበት ማለት ነው፡፡
እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው!!! ዐቢይ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር ባደረገ ጊዜ “በምርጫው መራዘም አለመራዘም ጉዳይ መንግሥት እስከ አሁን አቋም አልያዘም፡፡ ይሄንን ጉዳይ እኛ ፓርቲዎች በድምፅ ብልጫ የምንወስነው ጉዳይ ይሆናል!” ብሎ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ዐቢይ ይሄንን ባለበት ማግስት ግን በቃለ አቀባይዋ በኩል ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መደረግ እንዳለበት የዐቢይ አሥተዳደር አቋም መሆኑን መገለጹ ይታወሳል፡፡
እንግዲህ ይታያቹህ ዐቢይ በድምፅ ብልጫ እንወስናለን የሚለው ከእነ አየለ ጫሚሶ፣ ከነ ትዕግሥቱ አወሉ፣ መኢአድን አንድነትን አፍርሰው ለወያኔ ካስረከቡ ቅጥረኞችና ወያኔ ደሞዝ ከሚከፍላቸው መኢብንና ሌሎች ለቁጥር ከሚያታክቱ ሐሰተኛ የወያኔ ጥቅም አስከባሪ ተካፋይ ጉጅሌዎቹ ጋር ቁጭ ብሎ ሊያስወስን ነው የሚፈልገው፡፡
የዐቢይ አሥተዳደር የለውጥ አሥተዳደር ነኝ፣ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ እያለ ባለበት ሰዓት ተሸኝቷል የሚባለው የወያኔ/ኢሕአዴግ አሥተዳደር ምርጫንና ሒደቱን ለማወናበድ፣
ለማጭበርበር፣ ለማምታታትና እራሱን አሸናፊ ለማድረግ በማሰብ የፈጠራቸውን ሐሰተኛ አጫዋችና
ሚዛን ጠባቂ ፓርቲዎችን (ቡድኖችን) አሁንም ተለወጥኩ በሚልበት ሰዓት ይዟቸው መቅረቡን ማየት ብቻ
መጭውን ምርጫ አጭበርብሮ አወናብዶ ለማለፍ ምን ያህል እንደተዘጋጀና እንዳሴረ ለውጥ የሚባለውም ውሸት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከላይ እንደገለጽኩላቹህ ግጭትና ግርግሩን እስከምርጫው ጊዜ ድረስ በማስቀጠል
ሊጠቀምበት ይፈልጋል፡፡ ምርጫው ከተራዘመ ግን እስከተራዘመው ጊዜ ድረስ ያለውን አለመረጋጋት ግጭት ወዘተረፈ እስከዚያ ድረስ ይዞ መቀጠል በገንዘብም በምንም እነሱን የሚጎዳና አዳጋች ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ወያኔ/ኢሕአዴግ ምርጫው እንዲራዘም የማይፈልገው፡፡
ሕዝቡ እውነት ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ የማድረግ ቁርጠኝነቱና ዕድሉ ካለ ምርጫው ቢያንስ ለሁለት
ዓመት ቢበዛ ለሦስት ዓመት እንዲራዘም የሚፈልግበት ምክንያት ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ
አሁን ያሉ ሁኔታዎች ፈጽሞ የማያስችሉ ስለሆኑና ሐሰተኛ የወያኔ ተከፋይ ቁማርተኛ ፓርቲዎችን
ማስወገድን ጨምሮ አምስት መቶ ሽህ ካድሬ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በሙሉ ሸኝቶ በታማኝ
የሕዝብ ልጆች መተካትና በምርጫ አስፈጻሚነት ሥልጠና ብቁ አድርጎ ማዘጋጀት፣ እዚህም እዚያም ረብሻ፣ የእርስበርስ ግጭት፣ አለመረጋጋት እየፈጠሩ ያሉ የለውጥ አደናቃፊ የሚባሉ ኃይሎችን በሙሉ በቁጥጥር ስር በማዋል እየፈጠሩት ያሉትን ችግር ማስወገድ የመሳሰሉት የግድ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ስላሉ ነው፡፡
“ምርጫው መራዘም አለበት!” ሲባል ዝም ብሎ ተራዝሞ “ነገሮች አሁን እየሔዱ ባለበት ሁኔታ ቀጥለው ለተራዘመው የምርጫ ቀን እንድረስ!” ማለት ሳይሆን የዐቢይ አሥተዳደር “የለውጥ አሥተዳደር ነኝ!” ብሏልና፣ “ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ!” ብሏልና ከምርጫው በፊት ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ እንዳይደረግ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን በሙሉ ለማስወገድ ለመፍታት ከዚህች ሰዓት
ጀምሮ በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትጋት በመሥራት ቢያንስ የተራዘመው ምርጫ ከመኪያሔዱ ከሁለት ዓመት በፊት የቤት ሥራዎቹን በሙሉ ጥንቅቅ አድርጎ በመፈጸም ሁሉንም ነገር ምቹና ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
እነኝህ ችግሮች ባልተቀረፉበትና ለመቅረፍም ባልተፈለገበት ሁኔታ ምርጫ እንዲደረግ ከተፈለገ ግን ትጠራጠሩ የዐቢይ አሥተዳደር ወይም ወያኔ/ኢሕአዴግ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ የማድረግ ፍላጎቱና
ቁርጠኝነቱ ጨርሶ የለውም፡፡ ከዚህ ቀደም እንደተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ አጭበርብሮ ማለፍ አስቧል ማለት ነው፡፡ አብን እነኝህ የቤት ሥራዎች ተጠናቀው ሳይሠሩ ምርጫ እንዲደረግ የፈለገበት ምክንያት ማንን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ ግልጽ የሆነላቹህ ይመስለኛል፡፡
የአማራ ሕዝብ ሆይ! ባለጋራህ ወያኔ/ኢሕአዴግ ምስለኔውን መቀየር እንጅ እንዲያው በፍጹም ነጻ ወጥተህ በራስህ እየወሰንክ እንድትኖር አልፈቀደልህም፡፡ ለነገሩ ዘርህን ከዚህች ሀገር ለማጥፋት በርትቶ ሲሠራ የኖረው
ወያኔ/ኢሕአዴግ እስካለ ጊዜ ድረስ “ነጻ ወጥቸ በራሴ ጉዳይ እራሴ እየወሰንኩ እራሴን አሥተዳድራለሁ!” ብለህ ካሰብክ ሲበዛ የዋህ ሆነሃል ማለት ነው፡፡
ወገኔ ሆይ! የነጻነት ጉዞህ ረጅምና መረር ያለ መሥዋዕትነት እንደሚያስከፍልህ አውቀህ ቆርጠህ ጨክነህ
ተነሥ!!! ልዑል እግዚአብሔር በረድኤቱ ረጅሙን፣ ከባዱንና ውስብስቡን የነጻነት ጉዞህን አጭር ያርግልህ!!!
አሜን!!!
ድል ለአማራ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com