አቶ ገብሩ አሥራት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ያደረጉትን ቃለመጠይቅ
December 29, 2018

የህወሓት መስራች፣ የመጀመሪያው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩትና የአረና አመራር ሆነው ያገለገሉት አቶ ገብሩ አሥራት ከአንድ ወር በፊት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቃለመጠይቅ አድርጎላቸው ነበር።በዚሁ ቃለመጠይቅ ብዙ ጠቃሚ እና መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን አንስተዋል። እስኪ በየብሄር ፖለቲካ እና የዜግነት ፖለቲካ፣ የማንነት ጥያቄዎች እና ግጭቶች፣ ብሄርተኝነት እና ፅንፈኝነት፣ ህወሓት እና በትግራይ ህዝብ ዙሪያ ከተናገሯቸው መካከል ላስነብባችሁ

ክፍል አንድ
የወቅቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰላለፍ፡ ብሄር ፖለቲካ VS የዜግነት ፖለቲካ
አዲስ አድማስ ጋዜጣ፦ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ቤት ከመመመለሳቸው አንጻር፣ በሀገሪቱ ምን አይነት የፖለቲካ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለው ያስባሉ?
አቶ ገብሩ አሥራት፦ አሁን ባለው ሁኔታ ፖለቲካችን ወዴት አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፣ አሰላለፉስ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለውን ለመገምገም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁለት የፖለቲካ አቅጣጫዎች ግን በፖለቲካ አውዱ ላይ ቀርበዋል፡፡ አንደኛው አሁን ያለውን የብሄር ብሄረሰቦች ፖለቲካ መሰረት አድርገን ወደፊት እንጓዝ የሚል ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሄ የብሄር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለኪሳራ ስለዳረጋት የሚያስፈልጋት የዜግነት ፖለቲካ ነው፤ ክልላዊ አከላለሉም ለዜግነት ፖለቲካ ችግር የፈጠረ ስለሆነ መፍረስ አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ሁለቱ የፖለቲካ አቅጣጫዎች አሁን በሀገሪቱ የተፋጠጡ ይመስለኛል፡፡ በኔ አስተያየት ሁለቱም ሳይጣረሱ መታረቅ አለባቸው፡፡ የብሄር ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካ እኩል ቦታ የሚያገኙበት አማራጭ መፈለግ አለበት፡፡ ምክንያታዊ ፖለቲካ፣ ሃሳባዊ ፖለቲካ እየተደፈጠጠ፣ ብሄር ላይ የተንጠለጠለ ያውም ፅንፍ የብሄር ፖለቲካ ኃይልና ተሰሚነት ያገኘበት ሁኔታ ነው አሁን የተፈጠረው፡፡ በሀገር አንድነት አምናለሁ ሲል የነበረ ሳይቀር ብሄሩን እየፈለገ የመሸገበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቀጣዩ ተግዳሮት፣ የፅንፈኛ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ነው፡፡ የብሄርና የዜግነት ፖለቲካ ሚዛን ጠብቀው የሚሄዱበት ሁኔታ እንዴት ይፈጠር የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ አሁን ሁሉም ሃይሉን የማሳየት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ያም ቢሆን እኔ እንደ ፖለቲከኛ እነዚህ ሁሉ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይረግባሉ በሚል ተስፋ ነው የምመለከተው፡፡ መፍትሄ ለማምጣት ግን ቁጭ ብሎ መነጋገር መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን ሃገሪቱ ወዳልሆነ አቅጣጫ ልታመራ ትችላለች፡፡