December 29, 2018
Posted by: Zehabesha
ከ33 አመታት ስደት የስደት ህይወት በኋላ በቅርቡ ወደአገራቸው የተመለሱት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ዛሬ በአዲስ አበባ ለንባብ ከበቃው ኢትዮጲስ ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡:
የደርግን ስርአት ተቃውመው በ1979 ወደውጭ ለስራ በተላኩበት ወቅት በዚያው የቀሩት ሻለቃ ዳዊት በስደት ቆይታቸው የህወሀትን አገዛዝ አጥብቀው ሲቃወሙ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ወደአገር ቤት የተመለሱበትን ሁኔታ ሲያስረዱ በእነዶክተር አብይ የተካሄደው ለውጥ ለስፋ ስለሰጣቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሲናገሩ ‹‹ይህን የtጀመረውን ለውጥ መደገፍ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው በማለት፣ ይህ ለውጥ ወደፊት እንዲጓዝ፣ እንዲጠናከርና ለአገር እንዲበጅ በማድረግ ሃላፊነትን መወጣት እንደሚያስፈልገን በመገንዘብ ተመልሻለሁ›› ብለዋል፡፡ የተመለሱት ግን ጠቅልለው ለመኖር ሳይሆን ይህን ለውጥ የሚያግዙበትን መንገድ ለማጥናትና ከመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ተወያይተው ለመወሰን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የተለያዩ ወገኖች ከትቅ ትግል ወደሰላማዊ ትግል ሲገቡ መከወን ስላለባቸው ተግባራትና መከተል ስለሚያስፈልገው ስርአት በተባበሩት መንግስታት ስር የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉ ሻለቃ ዳዊት የሰላም ስምምነት ማለት ጦርነትና ግጭትን አስወግዶ ሰላም ማስፈን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆዩ ሀይሎች ወደሰላማዊ ትግል እንገባለን ብለው ሲወስኑና ይህም ተቀባይነት ሲያገኝ የመጀመሪያው ተግባር ትጥቅ መፍታት መሆኑን ያስረዱ ሻለቃ ዳዊት በእኛ አገር አሁን የሚታየው ግን ትንሽ ስርአቱን ያልተከተለ እንደሆ ገልፀዋል፡፡ ‹‹በኦነግ በኩል ትጥቃቸውን ሳይፈቱ የገቡ ካሉ ስህተት ተፈፅሟል ማለት ነው›› ያሉት ሻለቃው በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብሎ የኦነግ ሰራዊት የሚባል ነገር እንደማይኖርም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ውጭ ‹ትጥቅ ትፈታለህ፣ አልፈታም› የሚለው ነገር ትክክል እንዳልሆነና ይህ ነገር መጀመሪያ ማለቅ እንደነበረበት፣ ሳያልቅ ከቀረም አሁን መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

