አየ ወ/ሮ መዓዛiii እርጅና ነው ወይስ ሙስና እንዲህ ሞያውን ያጠፋባት???
ጋዜጠኛ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ በራሷ የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) ጣቢያ የጨዋታ እንግዳ በተሰኘው ዝግጅቷ ትናንት ቅዳሜ ታሕሳስ 20,2011ዓ.ም. የተቋጨ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገ/ማርያምን ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት እንግዳ አድርጋ አቅርባ ነበረ፡፡
ወ/ሮ መዓዛ ይሄንን ሰውየ እንግዳ አድርጋ ስታቀርበው በአየር መንገዱ ስለሚፈጸሙና በሰፊው ስለሚወሩ የመብት ጥሰቶች፣ የወያኔ ባለሥልጣናት አየር መንገዱን የውጭ ምንዛሬ ማሸጋገሪያ አድረገው ስለመጠቀማቸው፣ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችና የሙስና ወይም የእምነት ማጉደል ተግባሮች ወይም ወንጀሎች የመሳሰሉ ጉዳዮች በአየር መንገዱ ስለመፈጸማቸው በለስላሳው እንደምታነሣ ጠብቄ ነበር፡፡
ልብ በሉ “አፋጥጣ እንደምትይዘው ጠብቄ ነበር!” አላልኩም፡፡ ምክንያቱም ወ/ሮ መዓዛ ይሄንን ዝግጅት ከጋዜጠኛ ደረጀ እጅ ወስዳ መሥራት ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ ስናያት ይሄንን ስታደርግ ዓይተናትና ሰምተናት አናውቅምና ነው፡፡ አቀራረቧ ሁሌም ተመሳሳይና ዘልማዳዊ ነው፡፡ ለስላሳ ጥያቄዎችን ታነሣለች እንግዳው በመሰለው መንገድ ይመልስና ዝግጅቱ ይጠናቀቃል፡፡ አበቃ ይሄው ነው፡፡
ጠንከር ጠንከር ያሉ ወይም አወዛጋቢ ጥያቄዎችን እያነሡ እውነቱን ማውጣጣት በደረጀ ጊዜ ቀርቷል፡፡ ደረጀ “አፋጥጦ ይይዛል ይሞግታል!” እያልኩ አይደለም፡፡ “አፋጦ አይይዝም አይሞትም!” እያልኩም አይደለም፡፡ ነገር ግን እንግዳ አድርጎ ያቀረበው ሰው የሚወራበት ወይም የሚታማበት ነገር ካለ ለዛ በተሞላ ጨዋታ እያሳሳቀ ፍርጥ አድርገው እንዲናገሩት የሚያደርግበት የራሱ መንገድ ነበረው፡፡ እንጅ እንደ አንዳንዶቹ ፍጥጫ የተሞላበት ለዛቢስ ጭቅጭቅ አድርጎ አይወዛገብም ነበር፡፡ ደረጀ እንዲህ እያደረገ የሚቀርቡ እንግዶች እውነቷን ሳያወጧት አይለቃቸውም ነበር፡፡
ደረጀ ይሄንን ሁሉ ሲያደርግ የተጋባዥ እንግዶቹን ምቾት አይነሳም፡፡ እያዝናና፣ እያሳሳቀ፣ እያዋዛ ነው ሥራውን የሚሠራው፡፡ በዚህ መንገድ መጠየቅ የሚገባቸውን ጥያቄዎች በሙሉ አንድም ሳያስቀር እያነሣ የአድማጩን ፍላጎት በማርካት ይሄንን ዝግጅት እጅግ ተወዳጅ አድርጎ ይዞት ነበር፡፡ ከመዓዛ ጋር በክፍያ ሳይስማሙ ቀሩና ጥሎ ወጣ፡፡ መዓዛም “ተወው! እኔ የማልሠራው መሰለህ?” ብላ በእልህ ገባችበትና ይሄው ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ይዛው ትገኛለች፡፡
ወ/ሮ መዓዛ ከጋዜጠኛ ደረጀ አኳያ ስትታይ በጣም ጎልቶ የሚታይ ሰፊ ልዩነት አላቸው፡፡ በእርግጥ መዓዛም ጠንካራ ጎን አላት፡፡ ይሁንና የደረጀ ያልነው ልዩ ብቃትና ችሎታ እንዳለ ሁሉ የመዓዛ የምንለው ልዩ ብቃትና ችሎታ ግን የላትም፡፡ እንደ ደረጀ አድርጎ ለመሥራት ድፍረት፣ በራስ መተማመን፣ ብልሃት ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ለጋዜጠኝነት የተሰጠንና ልዩ ችሎታ ያለውን ሰው ከሬዲዮ ማጣት በእውነት ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ እስከአሁን በዚህ ዝግጅት ላይ ቢኖር ኖሮ ስንቱን ቁምነገር በጨዋታ እያዋዛ ያስኮመኩመን ነበር፡፡
ወደ አቶ ተወልደ ዝግጅት እንመለስ፡፡ ከላይ እንዳልኳቹህ ወ/ሮ መዓዛ አቶ ተወልደን እንግዳዋ ስታደርገው ወ/ሮ መዓዛ የመሞገት ወይም እንደ ጋዜጠኛ ደረጀ እያሳሳቁ የማውጣጣት ችሎታና ፍላጎት የላትምና መረጃዎችን አጠናቅራ አቶ ተወልደን አፋጣ አትጠይቀው ይሆናል ወይም አሳስቃ አታውጣጣው ይሆናል አልኩ እንጅ ጭራሽ በአየር መንገዱ ላይ ከሠራተኞችና ከሕዝቡ “በማንነታችን ምክንያት ጥቃት ይሰነዘርብናል፣ የአየር መንገዱ የሥራ ቋንቋ ትግርኛ እስኪሆን ድረስ አየር መንገዱ በአንድ ክልል ተወላጆች ተሞልቷል፣ ትግርኛ ተናጋሪዎች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ይዘዋቸው ለሚገቡ ዕቃዎች ቀረጥ ሳይከፍሉ ይዘው እንዲያልፉ ወይም እንዲያስገቡ ይደረጋል፣ አየር መንገዱ የሌባ ባለሥልጣናት ገንዘብ ማሸሻ ሆኗል….!” ወዘተረፈ. እየተባሉ ስለሚነሡና በሰፊው ስለሚነገሩ ችግሮች ጨርሶ ላትጠይቀው ትችላለች ብየ ፈጽሞ አልጠበኩም ነበረ፡፡
እነኝህን ጥያቄዎች በራሷ ቁጥብነት የተሞላበት አኪያሔድ ቢሆን አለመጠየቋ በጣም ገርሞኛል ሆን ብላም ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው አቶ ተወልደ በተደጋጋሚ እነኝህን ጥያቄዎች እንድታነሣ ይገፋፋት ነበር፡፡
ከተደጋጋሚ ጉትጎታው በኋላ መሀል ላይ ወ/ሮ መዓዛ አቶ ተወልደን “ለሕዝቡ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ ዕድሉን ሰጥቸዎታለሁ!” ስትለው አቶ ተወልደ “በሶሻል ሚዲያ የሚረጭ ሰፊ ወሬ አለ፡፡ በሥራ ክንውን ብቃት ማነስ እርምጃ የተወሰደባቸው ግለሰቦች የሚያስወሩት ሐሰተኛ ወሬ ነው፡፡ የሚረጨው ነገር ሁሉ ውሸት ነው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፍጹም ከዘርና ከፖለቲካ ነጻ የሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ነው!” በማለት ጥቂት እንኳ ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ ካለውና ከተጨባጩ ሃቅ ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም፣ ነባራዊውን ሁኔታ የማያሳይ ወሬውን ለራሱ በሚመች መልኩ ተናገረ፡፡
ወ/ሮ መዓዛ “አንተው ካመጣኸውማ!” ብላ ጥያቄዎችን ታስከትላለች ብለን ስንጠብቅ ጨርሶ በሕዝብ ዘንድ የሚነሡ ቅሬታዎችን ልታነሣ ሳትችል ቀረች፡፡ የዝግጅቱ ዓላማ የሚመስለውና በግልጽም የታየው እውነቱ ያለበትን ቦታ ማሳየት ሳይሆን የሰውየውን የጠለሸ ኢሜጅ (ገጽታ) እና የተሠበረ ስም መጠገን ብቻ እንጅ ከሕዝብ በኩል ለሚነሡ ቅሬታዎች ቦታ ሰጥቶ ምላሽ ማሰጠት አልነበረም፡፡
ወ/ሮ መዓዛ ሕዝብ አጥብቆ የሚያነሣቸውንና እራሱ ሕዝቡ ምስክር የሆነባቸውን ቅሬታዎች፣ ከአብራሪ እስከ ቴክኒሺያን (አበጅ) ከሆስቴስ (አስተናጋጅ) እስከ የቢሮ (ጽ/ቤት) ሠራተኞች ከአሥተዳደር በደልና ብልሹነት የተነሣ በሰፊው የሚያነሧቸውን ጥያቄዎች አንሥታ የሕዝብን ድምፅ ወይም ጩኸት ቅሬታ ካላሰማች የእሷ ጋዜጠኝነት፣ የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) ጣቢያዋ የሕዝብ ሬዲዮነት ምኑ ላይ እንደሆነ ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡
ይሄ የሠራችው ሥራ ምን ማለት እንደሆነ ወ/ሮ መዓዛ መረዳት ባለመቻሏ እጅግ በጣም ገርሞኛል፡፡ ወይ ደግሞ ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅታ ከሆነም መልካም፡፡ እውነቴን ነው የምላቹህ እኔ መዓዛ የዚህን ያህል ማሰብ ማገናዘብ ይሳናታል ብየ አልገምትም ነበረ፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር ከሕዝብ ጋር ፊት ለፊት የሚያጋጫትን የሚያቀያይማትን ስሕተት ትፈጽማለች ብየ አልጠብቅም ነበረ፡፡
ከሰውየው ቅጥፈትና እብለት የተሞላበት ማስተባበያና ቅሬታ ያነሡ ሠራተኞችን ስም ያጎደፈ ዘለፋ በተጨማሪ ጭራሽ እሷም ተጨምራ ሐሰተኛ ማስተባበያውንና ስም ማጥፋቱን ብሎ እንደጨረሰ የጋሽ ጥላሁን ገሰሰን፦
“ኧረ ተውኝ ባትነኩኝ ምን አለበት፤
እባካቹህ ሰዎች ሥራየን ልሥራበት!”
የሚለውን ዘፈን አስከትላ በመጋበዝ በደል የተፈጸመባቸውን የግፍ ሰለባ ወገኖቻችንን ጥላሁን ገሰሰ የሥራ እንቅፋት የሆኑ ክፉ ሰዎችንና ክፉ ሥራቸውን እያነሣ ክፉ ሰዎችን በዘለፈበት ዘፈን ዘልፋ ተሳድባ አረፈችው፡፡
አቶ ተወልደ “ተራ ስም ማጥፋቶች ናቸው፣ ሐሰተኛ የሶሻል ሚዲያ ወሬዎች ናቸው፣ የሥራ ብቃትና ችሎታ ስለሌላቸው የተቀጡ የተሰናበቱ ሰዎች መሠረተቢስ የጥላቻ ወሬዎች ናቸው!” ብሎ የጥቃት ሰለባዎችን ክብር በሚነካ ተአማኒነትን በሚያሳጣ መልኩ እራሳቸውን መከላከል ባልቻሉበት ሁኔታና እንዲከላከሉም ዕድል ባልተሰጠበት ሁኔታ አሰድባቸዋለችና፣ ሲፈጸም የኖረውን ጥቃትና የብልሹ አሥተዳደር በደል አሌ ብሎ ሸምጥጦ ክዷልና እንግዲያውስ እነኝህ በአቶ ተወልደ ሐሰተኛና ስም አጥፊ ፍረጃ “ብቃት ችሎታ የሌላቸው!” የተባሉ ሰዎች እራሳቸውን የመከላከል መብት አላቸውና ከዓመታት በፊት በማንነቱ ምክንያት በሚፈጸምበት ጥቃት በመማረር በረዳት አብራሪነት የሚያበረውን ቦይንግ 767 አውሮፕላን (በረርት) አቅጣጫ ቀይሮ ስዊዘርላንድ የፖለቲካ ጥገኝነት በመጠየቅ ካሳረፈው ከኃይለመድኅን አበራ እስከ የበረራ ሥልጠናውን በማዕረግ ተመርቆ ሥራ በጀመረ በወሩ የተባረረውን አዲስዓለም መኮንንን፣ ከዐቢይ አበበ እስከ ዮሐንስ ተስፋዬ ድረስ እንዲሁም ሌሎችን ተቆጥረው የማያልቁ አማራ በመሆናቸው ብቻ የሥነ ልቡና ጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ እራሳቸውን እንዲከላከሉ ዕድል መስጠት ይኖርባታል!!!
የአየር መንገዱ የዘረኝነትና ብልሹ አሥተዳደር ጥቃት ሰለባ የሆናቹህ ወገኖቻችንም በዚህ ቃለምልልስ በአቶ ተወልደ ለተሰነዘረባቹህ የጅምላ ዘለፋና ስም ማጥፋት በዚሁ ዝግጅት ቀርባቹህ እራሳቹህን ከመከላከል ጀምሮ የሞራል ካሳ የመጠየቅ መብት አላቹህና ሸገር ራዲዮን እንድትጠይቁ ይሁን!!! ጣቢያው ወይም ወ/ሮ መዓዛ አሻፈረኝ ካለችም ለብሮድካስት (የስርጭት) ባለሥልጣን መሥሪያቤትና ለፍርድ ቤት ክሰሱ!!!
በመጨረሻም ሸገር ሬዲዮ የጠላቶቻችን ልሳን ሆኖ ተደርቦ ስለሰደበን፣ ጩኸታችንን ክሳችንን ዋጋ ለማሳጣት ስለተባበረብን እናመሰግናለን በሉት!!!
ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com
