January 2, 2019

ፎቶ፡ ከግራ ወደ ቀኝ፤ አቶ መርእድ ዓለማየሁ፤ ወ/ሮ የሴም ደበበ፤ አቶ ተፈራወርቅ አሰፋ፤ ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ፤ ኪዳኔ ዓለማየሁ።
በመጀመሪያ፤ ስለ ሽልማቱ “አድዋ የባሕል እና የታሪክ ሕብረት”ን በተለይም የድርጅቱን መሪ፤ ዲያቆን ፍሬው ሰይፉን በትሕትና አመሰግናለሁ።
በተጨማሪም፤ ሽልማቱ በተከናወነበት ጊዜ በአቶ ተፈራወርቅ በኋላም ዲን. ፍሬው በቪኦኤው ቃለመጠይቅ በጊዜ ውሱንነት ምክንያት ስለ እኔ ተግባሮች ያቀረቧቸው መግለጫዎች በኔ ጥረት ብቻ ላይ በማተኮሩ ነገር ግን የብዙ ሰዎችም ሕብረትና ድጋፍ የተከናወነበት ስለ ነበር ይኸንኑ በግልጽ ማስታወቅ ተገቢ መስሎኛል። ባሁኑ ጊዜ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ረጅሙ እድሜዬም ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ በመሆኑ፤ ከዚህ በታች ስማቸውን ለምጠቅሰው ሰዎች በሙሉ ልባዊ ምሥጋናዬን በትሕትና አቀርባለሁ። በተጨማሪም፤ የሽልማት ባሕልን ለማጠናከርና የበለጠ ብቃት ያላቸው ብዙ ሌሎች ሰዎች ስላሉ ለማበረታታት ነው።
በመጠኑም ቢሆን ሽልማቱን ስቀበል በገለጽኩት መሠረት እኔ ሽልማቱን ብቀበልም ሌሎች ምሥጋናው ሊደርሳቸው የሚገባቸው ሰዎች፤ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የቴሎኮሚዩኒኬሽን ቦርድ የአስተዳደር ዋና ክፍል ሥራ አስኪያጅ በነበርኩበት ጊዜ ከፍተኛ ድጋፍ ያከናወኑልኝ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ በትሩ አድማሴን፤ አንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት የለሶቶ መንግሥት የፖስታና የቴሌኮሚዩኒኬሽንና የሲቪል ኤቪዬሽን ዲሬክተር በኋላም የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በነበርኩበት ጊዜ የሐገሩ እቅድ ኃላፊ የነበሩት ሚር. ቲም ታሃኒ፤ በኋላም ዱባይ በአማካሪነት አገለግል በነበርኩበት ጊዜ የከተማው ከንቲባ የነበሩት ሚር. ቃስም ሡልጣን፤ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአጠቃላይ ለ28 ዓመት በ10 ሐገሮች ባገለገልኩበት ጊዜ ብዙ ሌሎች ምሥጋና የሚገባቸው ሰዎች ነበሩ።
ጡረታ ከገባሁም በኋላ ባተኮርኩባቸው ልዩ ልዩ ዓላማዎች፤
1ኛ/ የዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (www.globalallianceforethiopia.net) ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው የጦር ወንጀል ስለሚያስፈልገው ፍትሕና ቫቲካንም ለኢጣልያኖቹ ባከናወነችው ድጋፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ስለሚያስፈልጋት ጉዳይ በሊቀመንበርነት የሚያገለግሉት፤ ልዑል ኤርምያስ ሣህለ ሥላሴ፤ እና የቦርድ አባላት ዶር. አክሊሉ ሀብቴ፤ ዶር. ጌታቸው ኃይሌ፤ ዶር. ግርማ አበበ፤ ዶር. አስቴር መንገሻ፤ ዶር. ሚካኤል ወሰን፤ ዶር. ጆን ሌቪ(Dr. Jon Levi)፤ ዶር. ስቲቭ ደላማርተር (Dr. Steve Delamarter) እና ሚር. ኒኮላ ዲማርኮ (Mr. Nicola DeMarco) ሊመሰገኑ ይገባል።
2
በተከናወነው ጥረት እስካሁን የተገኘው ውጤት፤
(ሀ) የየካቲት 12 የሰማእታት ቀን ዝክረ በዓል በየዓመቱ እስከ 30 በሚደርሱ የዓለም አቀፍ ከተሞች እየተከናወነ ነው። በዚህ አጋጣሚ፤ አንዳንድ የኢትዮጵያውያን ማሕበር ድርጅቶች በዓሉን በመዘከራቸው ልዩ ምሥጋና ይገባቸዋል። ባሁኑ ጊዜ፤ ዳላስ ከተማ ለሚቀጥለው የየካቲት 12 ዝክረ በዓል እያዘጋጁ ያሉትን ዲን. ፍሬው ሰይፉን፤ አቶ ሔኖክ አሰፋን፤ አቶ ፍቅረማርያም ደረሰን፤ ቀሲስ አብነት አሰፋን፤ ዲን/ ሔኖክ ተዘራንና አቶ ከድር ሰይድን፤ ላመሰግን እወዳለሁ። በሌሎች አካባቢዎችና ሐገሮች ዝክረ በዓሉን የሚያከናውኑ ጥልቅ ምሥጋና የሚገባቸው ብዙ ሰዎችም አሉ።
(ለ) ኢጣልያኖችና ጥቂት ኢትዮጵያውያን ኢጣልያ በምትገኘው ሮም (Rome) ከተማ የየካቲት 12ን ዝክረ በዓል በዚህ ዓመት እንደሚያከናውኑ ወዳጄ፤ ካርሜሎ ክሪሸንቲ (Carmelo Crescenti) አስታውቆኛል።)
(ሐ) ቫቲካን የኢጣልያንን የጦር ወንጀል በመደገፏ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ከዚህ በላይ በቀረበው ድረ-ገጽ የተካተተ አቤቱታ እስካሁን 6400 ደጋፊ ፈርሞታል። በድርጅታችን በኩል የሚፈለገው የፊርማ ቁጥር መቶ ሺ በመሆኑ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ተጨማሪ ፊርማ በማግኘቱ ረገድ እንደሚረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። መመስገን ከሚገባቸው ውስጥ አቶ ከባዱ በላቸውና አቶ ገብረሕይወት ልብሰ ቃል ሊጠቀሱ ይገባል።
(መ) ኢትዮጵያ በኢጣልያ አማካኝነት ለደረሰባት የጦር ወንጀል ጉዳዩን እንደሚያጠኑት የአውሮፓ አንድነት ምክር ቤት እንደሚመለከተው በጽሑፍ ገልጾልናል።
(ሠ) ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊነት ጉዳይ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ለደረሳቸው የድርጅታችን ደብዳቤ ቅንነት የሰፈነበት መልስ ሰጥተውናል። ነገር ግን በቫቲካን በኩል እስካሁን ተገቢ መልስ አላገኘንም። ቫቲካን አይሑዶችን፤ የላቲን አሜሪካን ሕዝብና ሩዋንዳን ይቅርታ ጠይቃ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተመሳሳይ የክርስቲያናዊ ይቅርታ አለመጠየቋ የሚያጠያይቅ ነው። በዚህ ጉዳይ እየረዱ ያሉት አቶ ጨፍቄ ደሠላኝና ዶር. ያዕቆብ ኃይለማርያም ናቸው።
(ረ) አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ ከንቲባውና ተባባሪዎቹ ኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው የጦር ወንጀል ዋናው ተጠያቂ ለሆነው ለግራዚያኒ መታሰቢያ በማቋቋማቸው ማሕበራችን በኢጣልያኖችና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ባከናወነው ተቃውሞ እንዲሁም በኢጣልያው በላዚዮ አውራጃ ገዢ፤ በሲኞር ኒኮላ ዚንጋሬቲ (Nicola Zingaretti) እና በአውራጃው ምክር ቤት መታሰቢያው እንዲወገድ ተወስኖ በተጨማሪም የኢጣልያው ፍርድ ቤት በከተማው ከንቲባና በሁለት የምክር ቤቱ አባላት ላይ የገንዘብ፤ የእስራትና ከመንግሥት ሥራ የመወገድ ፍርድ መሰጠቱ ሲሆን ጉዳዩ በይግባኝ ላይ ይገኛል። ቫሌሪያ ቺሪያቼ (Valerio Ciriaci) ግሩም የሆነ ፊልም አሰራጭቷል።
(ሰ) በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው የፋሺሽት ኢጣልያ ጭፍጨፋ ዋና ተጠያቂ የነበረው የሙሶሊኒ የልጅ ልጅ፤ አሌሳንድራ ሙሶሊኒ (Alessandra Mussolini) አያቷን በተቃወመ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል በማለት የማስፈራሪያ መልእክት በማስተላለፏ ከዚህ በታች ያለውን በመጠቆም የሚታየውን ለኢጣልያ ፕሬዚዳንትና ለአውሮፓ አንድነት ምክር ቤት ግልባጭ የተደረገ የማሕበራችን ደብዳቤ ተልኮላታል።
(ሸ) በኢትይጵያ ላይ ስለ ደረሰው ከፍተኛ የጦር ወንጀልና ስለሚያስፈልገው የካሣ መጠን ጥልቅ ጥናት እንዲከናወን በማሕበራችን ከተወሰነ በኋላ ተግባሩን እንዲያከናውን ዶር. ቴዎድሮስ ኃይለማርያም ተዋውሎ ቅድመ ክፍያም ከተደረገለት በኋላ ውጤቱ እየተጠበቀ ነው። በዚህ ጉዳይ ቅድመ ዝግጅት የረዱት ዶር. ያዕቆብ ኃይለማርያም፤ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፤ ቀሲስ/ዶር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል (ነፍሳቸውን ይማር)፤ ሚር. ኢያን ካምፕቤል (Ian Campbell)፤ ኢንጂ. ታደለ ብጡል፤ አቶ ሺመልስ አዱኛ፤ ዶር. ግርማ ዓለማየሁ እና ፕሮፌሰር ረዳ ተክለሃይማኖት ናቸው።
ኢጣልያ በሊቢያ ላይ ባከናወነችው የጦር ወንጀል ለፈጸመችው የ30000 ሰው ጭፍጨፋ $5 ቢሊዮን ካሣ ስትከፍል በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው የአንድ ሚሊዮን ሰው ጭፍጨፋ እንዲሁም የ525000 ቤቶች፤ የ2000 ቤተክርስቲያኖችና የ14 ሚሊዮን እንስሶች ውድመትና የመጠነ ሰፊ ንብረት ዘረፋ ተገቢ የሆነ ካሣ አለመክፈሏ የሚያሳዝን ነው። አርሚኒያም በቱርኮች አማካኝነት ክ115 ዓመት በፊት ለተፈጸመባት የአንድ ሚሊዮን ሕዝብ ጭፍጨፋ እየጠየቀች ያለችው ካሳ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ነው።
በዚህ ጉዳይ በተለይ የሚጠበቀው ልዩ እርምጃ በኢትዮጵያ መንግሥት ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው እጅግ ከባድ ወንጀል ከዚህ ውስጥም 2000 ቤተ ክርስቲያኖች በወደሙባት፤ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል በተጨማሪም በደብረ ሊባኖስ ገዳም 2000 መነኩሴዎችና ምእመናን በተጨፈጨፉባት እንዲሁም እጅግ ብዙ ንብረት በተዘረፉባት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ተገቢው የፍትሕ እርምጃ እንዲወሰድ እየተጠበቀ ነው።
3
በዚህ አጋጣሚ መገለጽ ያለበት፤ የኢትዮጵያ የፍትሕ ትግል ውጤታማ ሆኖ ካሣው ሲገኝ የሚከናወነው በሙስና ሊጠቃ ቢሚችል በገንዘብ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ ሊጠቅም በሚችል ተግባር (ፕሮጀክቶች) መሆን አለበት።
ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው ፍትሕ ከተጻፉት ሰነዶች አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ይገኛሉ፤
ለበለጠ ዝርዝር ግንዛቤ በ(www.globalallianceforethiopia..net) ድረ-ገጽ መመልከት ይቻላል።
2ኛ/ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም፤ ሕብረትና ልማት እንዲገኝ በተከናወነው ጥረት (www.eotcipc.org) አቶ ፋሲል ገብረማርያምን፤ አቶ ሐሩን ሙሳን፤ ወ/ት ሊሊ ገብሩን፤ አቶ ሰመረ ሀብተማርያምን፤ ሚር ዩሱፍ ካሌብን፤ ሚር ኢስማኢል ማሕሙድን ማመስገን ተገቢ ነው። ድርጅቱን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሊቀመንበርነት ስመራው ቆይቼ በኋላ ሚር. ዩሱፍ ካሌብ ተረክቦ ቀጥሎም አቶ ሰመረ አመራሩን ይዘው ነበር፡፡ በኔ በኩል ስለ ጉዳዩ ከጻፍኳቸው ውስጥ ከዚህ በታች ያለውን በመጠቆም መመልከት ይቻላል፤
በተጨማሪ፤ ስለአፍሪካ ቀንድና ስለ ሌሎች ጉዳዮች የደረስኩት መጽሐፍ፡ “My Journey with the United Nations and Quest for the Horn of African Unity and Justice for Ethiopia” ነው።
ባሁኑ ጊዜ ደግሞ ልዩ ምሥጋና የሚገባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ክቡር ዶር. አቢይ አሕመድ ናቸው። ምክንያቱም እኛ ለብዙ ዓመት የለፋንበትን ጉዳይ እርሳቸው በአጭር ጊዜ ከኤርትራ፤ ከሶማሊያና ከጅቡቲ መንግሥታት ጋር ቀና የሆነ ግንኙነት በመፍጠር የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና ሕብረት ራእይ አጠናክረውታል። የእርሳቸው
እጅግ የሚያበረታታ ሒደት ወደ አንድነት እንደሚዘልቅ ከፍ ያለ ተስፋ አለኝ። ስላስገኙት እጅግ ከፍ ያለ ውጤት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረብኩትን የምሥጋናና የአቤቱታ ግልጽ ደብዳቤ በሚከተለው ላይ መመልከት ይቻላል፤
3ኛ/ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተከስቶ ስለ ነበረው መከፋፈልና ሌሎችም ችግሮች ዓለም አቀፍ የምእመናን ማሕበር በማቋቋም በተከናወነው ጥረት ዶር. አክሊሉ ሀብቴ፤ አቶ ኢዮኤል ነጋ፤ ቀኛዝማች/ዶር. ሰሎሞን አበበ፤ አቶ ሔኖክ አሰፋ፤ አቶ ምናሴ በየነ፤ አቶ ሞላ ጋሻው፤ አቶ ሰይፈ ታደሰ፤ ወዘተ ምስጋና ይገባቸዋል።
የምእመናን ከፍተኛ ጥረታቸውና ጸሎታቸው ያስገኘው ውጤት፤ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክቡር ዶር. አቢይ አሕመድ አማካኝነት የተከሰተው አስደናቂ ውጤት ነው። ይኸውም ተከፋፍለውና ተወጋግዘው የነበሩት አባቶች አንድነት ማስገኘታቸው ነው።
በኔ በኩል በተጨማሪ የሚያሳስቡኝ ጉዳዮች ስላሉ ለብፁዓን ወቅዱሳን ፓትሪያርኮች ለአቡነ መርቆሬዎስና ለአቡነ ማትያስ የጻፍኩትን ደብዳቤ ለእግዚአብሔር፤ ለቅድስት ማርያምና ለመላእክት፤ ለአባቶች ካሕናትና ለምእመናን ግልባጭ በማድረግ አቤቱታዬን አቅርቤ ነበር። መልስ እየጠበቅኩ ነው። ካነሳሁዋቸው ጉዳዮች ውስጥ ከ90% በላይ ምእመናን ከንስሐናና ከቅዱስ ቁርባን ርቀው በቅዳሴውና በመጽሐፈ ቅዳሴው መሠረት የሕገ እግዚአብሔር አፍራሾች ሆነው ስለ መገኘታቸው፤ የቤተ ክርስቲያኑ ስብከት በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች እንዲቀርብ ስለ ማስፈለጉ፤ ስለሚያስፈልገው
4
የአስተዳደርና ቁጥጥር መሻሻል፤ ኢየሩሳሌም ስለሚገኘው ገዳማችን ባለቤትነት ስለሚያስፈልገው ጥረት፤ እንዲሁም ሰለ ሌሎች ጉዳዮች ይገኙበታል። ማሕበረ ቅዱሳንም በማከናወን ላይ ስላለው ድጋፍ በትሕትና አመሰናለሁ፡፡
4ኛ/ በኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው ዲሞክራሲ፤ የሰብአዊ መብት መከበር፤ ዶር. እርቁ ይመር፤ አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር፤ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ፤ አቶ ከባዱ በላቸው፤ አቶ መርድ ዓለማየሁ፤ አቶ ይልማ ዘሪሁን፤ አቶ ደጀኔ አሳየ፤ አቶ ዳንኤል ላቀው፤ ወ/ት ኮከብ ኃይሌ፤ አቶ መስፍን በቀለ፤ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ከተገኙት ውጤቶች ውስጥ በአሜሪካ ኮንግሬስ ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው የሰብአዊ መብት መከበር የጸደቀው ሒደት በኤች አር 128 (HR128) የተገኘው ውሳኔ ሲሆን ሌሎች ተጨባጭ ውጤቶችም የ”ኢትዮጵያዊነት” እና የ”ትብብር” ድርጅቶች መቋቋም ነው። በዚህ ከባድ ጉዳይ ከኔ ጋር ተባባሪ የነበሩ ከቴክሳስ፤ ክካንሳስ፤ ከኦክላሆማ፤ ከኮላሮዶና ከጂኦርጂያ የአሜሪካ ከፍለ ሐገሮች (states) የተሳተፉ ምሥጋና የሚገባቸው ኢትዮጵያውያን አሉ።
5ኛ/ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምርጫ መብታቸው ስለ መጠቀም የተከናወነው ሌላው ጥረት ነው። ኢትዮጵያውያን/አሜሪካውያን በምርጫ መብታቸው በመጠቀም ለራሳቸው፤ ለማሕበራቸው፤ ለኢትዮጵያና ለአሜሪካም ፍሬያማ የሆነ ተግባር እንዲያከናውኑ ተሞክሮ ነገር ግን የሚፈለገው ውጤት ተጨማሪ ጥረት የሚያስፈልገው ነው። ስለ ጉዳዩ ያቀረብኩዋቸው ሰነዶች ከዚህ በታች ባሉት ይገኛሉ፤
WAKE UP ETHIOPIAN AMERICANS! USE YOUR VOTING RIGHTS!
ኮሎራዶና በሌሎች ጥቂት አካባቢዎች እንዳሉ ኢትዮጵያውያን/አሜሪካውያን እንደሚከናወነው በሌሎች የአሜሪካ አካባቢዎችና የሌሎች ሐገሮች ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመብታቸው በመጠቀም በምርጫ ብቻ ሳይሆን በመመረጥም ቢሳተፉ ለኢትዮጵያ ጭምር ብዙ ጥቅም ሊያስገኙ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ነው።
6ኛ/ ተገቢ ጥረት የተከናወነበት ሌላው ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ ላይ እስከ 500 000 ሰው ለመጨፍጨፉና ለሌላም ብዙ የሰብአዊ መብት መጣስ ዋናው ተጠያቂ የሆነውን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለፍትሕ የማቅረቡ ትግል ነው። ለዚህም ጥረት ልዩ ምሥጋና የሚገባቸው ሰዎች፤ አቶ ነሲቡ ስብሀት፤ ዶር. ጌታቸው ኃይሌ፤ አምባሳደር እምሩ ዘለቀ፤ አቶ ፀሀይ ደመቀ፤ እና አቶ ተስፋሚካኤል መኮንን፤ ሲሆኑ “ፍትሕ ለኢትዮጵያ ግብረ-ሃይል” በተሰኘ ድርጅት ስር ትግላችንን እያኪያሔድን ነው። አንደኛውን የአቤቱታ ደብዳቤያችንንና ሌላው ኮ/ል መንግሥቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትን ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እንዲገደሉ በማዘዝ የፈረመበትን ጽሑፍ በሚከተሉት መመልከት ይቻላል፤
7ኛ/ ብዙ ትኩረት የሰጠሁት ሌላው ጉዳይ የግብረ ሠናይ ጥረቶችን የመደገፍ ሔደት ነው። ከነዚህም ተግባሮች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ለቤተ ክርስቲያን ነክ እርዳታዎች፤ በዓይን ሕመም እንዲሁም በውሀ እጥረት ለተጠቁ ኢትዮጵያውያን ስለሚያስፍልጉ እርዳታዎች፤ 10ኛ ክፍል ጨርሰው ከትምሕርት ቤት የሚወገዱ ወጣቶች ስለሚያስፈልጋቸው እርዳታ፤ ወዘተ ይገኙበታል። በተጨማሪም ለዳላስ/ፎርት ወርዝ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማሕበር ያተኮርኩባቸው ጉዳዮች ስለ እድር ማቋቋም፤ ለሕንጻ መግዣ እርዳታ፤ የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል፤ ወዘተ. ነበሩ። በግብረ ሠናይ ተግባሮች እርዳታዎቹንም በማመቻቸት የደገፉ ወገኖች ነበሩ። ከነዚሁ ውስጥ የምጠቅሳቸው አቶ ተፈራወርቅ አሰፋን፤ አቶ ብርሃን መኮንንን፤ ወ/ሮ በለጥሻቸውን፤ አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔርን፤ አቶ ይርጋለም ጎበዜን፤ አቶ ሚደቅሳን፤ ዶር. ወንዱ ዓለማየሁን፤ አቶ ዘውገ ቃኘውን፤ ቀሲስ መስፍን ደምሴንና፤ ሌሎች በዙ ተባባሪዎችን አመሰግናለሁ።
8ኛ/ ጠቀም ያለ ጊዜ ያሳለፈብኝ ሌላው ተግባር “My Journey with the United Nations and Quest for the Horn of Africa’s Unity and Justice for Ethiopia” የተሰኘው መጽሐፌ ዝግጅት ነበር። ለዚህም ከፍ ያለ እርዳታዋን ላበረከተችልኝ ለባለቤቴ ለአምሳለ ኃይሉ ምሥጋናዬን እያቀረብኩ ስለ መጽሐፉ ከዚህ በታች ባለው ሊታይ የሚችለውን በጣም ጠቃሚ የሆነ ሐተታ ያቀረበልኝን ዶር. ጌታቸው ኃይሌንም ከልብ በትሕትና አመሰግናለሁ።
5
ማጠቃለያ፤
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ “አድዋ የባሕል እና የታሪክ ሕብረት”ንና በድርጅቱ መሪ በዲያቆን ፍሬው ሰይፉ ስለ ተበረከተልኝ ሽልማት ለማመስገንና ለተሸለምኩባቸው ተግባሮች አስተዋጽኦዎች ያበረከቱትን ሌሎች ሰዎችን በመጥቀስ ለማመስገን እንዲሁም የሽልማት ባሕሉ እንዲዳብር እና ሽልማት የሚገባቸው ሌሎች ሰዎችንም ለማበረታታት ነው። በልዩ ልዩ ተግባሮች የተሳተፉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክቱ ሌሎች ስማቸው ያልጠተቀሱ ሰዎች እንዳሉ እገነዘባለሁ። የነሱንም ስሞች ባለመጥቀሴ ይቅርታ እየጠየቅኩ ልባዊ ምሥጋናዬን በትሕትና አቀርባለሁ።
በዚህ አጋጣሚም፤ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ሰፊ ግንዛቤ በማስገኘት ለተባበሩልኝ ለመገናኛ ብዙኃን በተለይ ለአሜሪካ (ቪኦኤ)፤ ለጀርመን (ዶቼቬሌ)፤ ለኢሳት፤ ለዳላስ የኢትዮጵያ ማሕበር ሬዲዮ፤ ለሸገር፤ ለርዕዮት (Reyot) እንዲሁም ለአባይ ሚዲያ (Abbaymedia)፤ ለሳተናው (Satenaw)፤ ለዘሀበሻ (Zehabesha)፤ ለኢካድፎረም (Ecadforum)፤ ለኢትዮጵያ ዛሬ (Ethiopia Zare) ወዘተ. ድረገጾች ጥልቅ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
እዚህ ላይ ማንሳት ያለብኝ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ፤ በበኩሌ ያስገኘሁት ውጤት በባለቤቴ በአምሳለ ኃይሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ የነበረ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።
እግዚአብሔር ሁላችንንም ያበርታን።
