January 3, 2019

ኢትዮጲስ

ከሁሉም አስቀድሞ፣ ኦነግ ወደ ህጋዊ መድረኩ የተመለሰበት ሁኔታ መሰረታዊ የአካሄድ ስህተት ነበረበት፡፡ በመንግስት በኩል ሆኖ የሰምምነት ሰነዱን የፈረመው የፌደራል መንግስት ወኪል ሳይሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ለማ መገርሳ ነበሩ፡፡ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ድርጅቶች የሰላም ስምምነት መፈፀም የሚችሉት፣ ከህግም ሆነ ከመርህ አኳያ፣ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ብቻ ነው፡፡

“በኦነግና በኢህአዴግ /ኦዴፓ መካከል የተከሰተው አለመግባባት፣ ብልጭ ያለውን የዲሞክራሲ ተስፋ ሊያጠፋ በሚችል አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ውጥንቅጥ ድርጅታዊ አቅምን ብቻ እንደ መለኪያ የምንወስድ ከሆነ፣ የእነ ዐቢይ አህመድ መንግስት፣ ኦነግን በኃይል ለመጨፍለቅ ብዙም የሚቸገር አይሆንም፡፡ ወደዚህ አማራጭ በፍጥነት አለመግባቱ፣ ብልህነት የተሞላበት አካሄድ ነው፡፡ ገመዷ ሙሉ በሙሉ እስክትበጠስ ድረስ፣ ለሁለቱም ወገኖች ሰላም ዋነኛው አማራጭ ሊሆን ይገባል፡፡

ኦነግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ህጋዊ ህልውናቸውን የሚያገኙት ከክልል መስተዳድሮች ሳይሆን፣ በፌዴራል ህገ መንግስቱ በኩል ከፌዴራል መንግስቱ ነው፡፡ የክልሎች ህገ – መንግስቶችና መስተዳድሮች፣ በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የህግ መብትና ሥልጣን (ከአፈፃፀም ባሻገር) የላቸውም፡፡ የኦነግ ጉዳይ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ጉዳይ አይደለም፤ የፌዴራል መንግስት ነው፡፡

የአካሄድ ስህተቱ አልበቃ ብሎ፣ የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ለህዝብ ይፋ አልተደረገም፡፡ ይህ መሆኑ፣ ህዝብ ጥፋተኛውን በቀላሉ ለመለየት እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ጥፋተኛው ወገንም፣ ከህዝብ እይታ ውጭ ሆኖ የህዝብን ሰላም የሚያውክበት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡ ደግነቱ፣ ይህ ስህተት በቀላሉ ሊስተካከል ይችላል፡፡ ስምምነቱ፣ “ዛሬ ነገ” ሳይባል፣ በቅፅበት ለህዝብ ይፋ ሊደረግ የሚችል ነው፡፡ ቅንነቱ ካለ ደግሞ፣ ሁለቱ ወገኖች ተስማምተው ይፋ ሊያደርጉት ይችላሉ፤ ይገባልም፡፡

ኦነግ፣ እንደማንኛውም ድርጅት ደካማና ጠንካራ ጎኖች አለው፡፡ ከደካማው ብንነሳ፣ ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅርና ሰራዊት የለውም ፡፡ ይሄ እውነታ፣ የመላው ታሪኩ መገለጫ ነው፡፡ በአንፃራዊነት፣ የድርጅቱ ጥንካሬ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው ከደርግ ውድቀት አንስቶ የሽግግር መንግስቱን እስከለቀቀበት የአንድ ዓመት ጊዜ ነበር፡፡ የሽግግር መንግስቱን ለቆ የወጣው በአግባቡ ሳይዘጋጅና ሳይጠናከር፣ ህዝብን ሳያማክርና በአፍሪቃ ቀንድ የተከሰተውን አዲስ የኃይል አሰላለፍ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ስለነበር፣ ያለፉትን ሶስት አስርት ዓመታት በከንቱ እዲያባክን አድርጎታል፡፡ ይህን ስህተት አሁንም ደግሞ፣ ከኢህአዴግ ጋር ወደ ፍልሚያ ቢገባ፣ ከዚህ በኋላ ሶስተኛ ዕድል (የመጀመሪውን ዕድል 1983፣ ሁለተኛውን አሁን) የግማኘቱ አጋጣሚ በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡

የኦነግ ዋነኛ ጠንካራ ጎን፣ በህዝብ ዘንድ ያለው የፖለቲካ ድጋፍ ነው፡፡ ድጋፉ ተገባውም አልተገባውም፣ “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ተብሎ ክርክር ካልተደረገ በስተቀር፣ እውነታነቱን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ህዝባዊ ድጋፍ (የሚሊዮኖች ድጋፍ፣) ለሁለተኛ ጊዜ እንዳይባክን በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ያስፈልገዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ቢጠብ እንኳን፣ ፈፁም የማይቻልበት ደረጃ እስኪደርስ ታግሶ፣ ህጋዊ መድረኩን መጠቀም የተሻለው አማራጩ ነው፡፡ ከአመራር አባላቱ መካከል አንዳንዶቹ፣ ሻዕቢያ ኤርትራን በኃይል እንደገነጠለው ሁሉ፤ ኦነግም ኦሮሚያን በኃይል እንዲገነጠል ከሰነቁት ምኞታቸው ጋር ሊፋቱ ይገባል፡፡ ከጊዜው ጋር አብረው መለወጥ ካልቻሉ፣ ድርጅቱን ይዘው ከመጥፋት ያለፈ አንደምታ እንደማይኖራቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡

በኦህዴድ/አዴፓ በኩል፣ የድርጅቱ መሰረታዊ ድክመት የሎሌነት ታሪኩ ነው፡፡ ይህ አሳፋሪ ታሪክ፣ ድርጅቱን ሁሌም ቢሆን እንደጥላ እንደሚከተለው ማንም ብዥታ ሊኖረው አይገባም፡፡ የኦህዴድ አመሰራረት ለኦሮሞ ህዝብ ቁመት (ለማንኛቸውም ህዝብ ቁመት) የሚመጥን አይደለም፡፡ እንዲያውም፣ ይኸው ታሪክ የኦሮሞ ህዝብ መዳከም አንድ መገለጫ ነው፡፡ ወደ ኋላ ተሄዶ መለወጥ የሚቻል ነገር ቢሆን፣ መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ መፋቅ የሚገባው ነወ፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ በዐቢይና ለማ የሚመራው ኦህዴድ/አዴፓ አመራር አዲስ ታሪክ ለመስራት ተግቶ በመስራት ውጤታማ ሆኗል፡፡ ህዝቡ አሁንም ቢሆን ኦህዴድን በጥርጣሬ ቢመለከተውም፣ በአዲሱ አመራሩ ግን ኮርቷል፤ የልቡም ደርሶለታል፡፡ ቀን እንዳወጡለት ልጆቹም ተቀብሏቸዋል፡፡ እነ ዐቢይ አህመድ የኦሮሞን ህዝብ ካስደሰቱበት እርምጃዎቻቸው መካከል፣ ኦነግን ወደ ህጋዊ መድረኩ ማስገባታቸው በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ኦነግ ላይ የተቻኮለ የኃይል እርምጃ በውስድ፣ ይህን የህዝብ አመኔታና ፍቅር ጥያቄ ውስጥ ማስገባት የብልህ አካሄድ አይሆንም፡፡ 
በጥቅሉ፣ ሁለቱም ወገኖች የሚጠቀሙት ችግሮቻቸውን በሰላም በመፍታት ብቻ ነው፡፡ አንዱ ሌላኛውን ጥሎ ለማለፍ የሚያደረገው ሩጫ፣ ለራሳቸውም ሆነ ዲሞክራሲ ለተጠማው ለሰፊው ሀገርም አይበጅም፡፡” 745