January 3, 2019
«እኛ ከእኛ ሕገ መንግስት የተረፈን፤ ጠንከር ያለ ንጥሻ የሚያሰጋት ድንጉጥ ሀገር ነው። በአፈና ውስጥ፤ ነጻነትን አጥቶ መኖር አንድ ነገር ነው፤ የሀገር ህልውና፤ በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ግን፤ እዚህ የደረስነው እንዴት ነው ብሎ የመጣንበትን መንገድ የመፈተሹ አስፈላጊነት የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ይሆናል።»
ባለፈው ዶ/ር ዐቢይ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ወይይት ላይ፤ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የተወከሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህዝቦች የኔ ብለው የሚቀበሉት ሕገ መንግስት እንዲኖረን፤ ከምርጫ በፊት ሕገ መንግስቱ ላይ መወያይት ያስፈልጋል፤ በእኛ እምነት አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት፤ የአማራን ህዝብ ይሁንታ፣ ፈቃድ እና ተሳትፎ ያረጋገጠ አይደለም” የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል። ወይይቱን ለመጀመር ትክክለኛው ግዜ መቸ ነው የሚለው ሌላ አጀንዳ ሁኖ፤ ሕገ መንግስቱ ሀገራዊ ሰነድ ለማድረግ፤ ብዙ ውይይት እና ክለሳ እንደሚያስፈልገው የምጋራው ሀሳብ ነው። ነገር ግን፤ ከግዜ ወዲህ ተደጋግሞ የሚሰማው “የአማራ ህዝብ ያልተወከለበት ሕገ መንግስት” የሚለው አገላለጽ፤ የሕገ መንግስቱን ህጸጽ በተሞላ ገጽታ የሚያሳይ ነው ብየ አላምንም። ሕገ መንግስቱ የጸደቀበት መንገድ ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊነት የጎደለው በሆነበት ሁኔታ፤ የተሳርፎ ጉድለት ግንባር ቀደም ችግር ሆኖ መቅረቡ እይታችንን ከመሰረታዊ ችግሩ ያርቃል የሚል ስጋትም አለኝ። በሌላ በኩል፤ የአማራን ህዝብ ነጥለን በሂደቱ አልተወከለም የምንል ከሆነ፤ አንድምታው የተቀረው ኢትዮጵያዊ ተወክሎል ይሆናል። በእኔ እይታ፤ አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት ሲጸድቅ የትኝውም ህዝብ ውክልና አግኝቶል የሚያስብል ሁኔታ አልበረም።
የሕወሐት/ኢሕአዴግ የፖለቲካ ትርክት፤ አማራን በመክሰስ ዙርያ የተቃኘ እንደነበር የሚካድ ነገር አይደለም። ሥርዓቱ ለብሔር መብት ከሰጠው ሰፊ እውቅና አንጻር፤ ብሔር ዘለል ለሆኑ የጋራ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና አስተዳደራዊ ሁነቶች የነበረው አተያይ በጣም የቀጨጨ እና የተዛባ መሆን፤ ብሔር ተኮር ጥያቄዎች ያልነበረውን የአማራ ህዝብ ከፖለቲካው ስሌት ውጭ ሆኖ እንዲንሳፈፍ አድርጎታል። ከዛም ባለፈ፤ “የድሮ ሥርዓት ናፋቂ” ፣ “ትምህክተኛ” ከሚሉ ተለጣፊ ስሞች ጀምሮ፤ በዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊ አብሮነትን እና ዘርፈ ብዙ ትስስር ሸምጥጦ በካደ መልኩ የተቀነቀነው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት፤ ለአማራ፤ በተለይም ለልሂቁ ክፍል ፖለቲካዊ ተሳትፎን ፈታኝ የሚያደርግ ሁኔታ ነበር። ሕገ መንግስቱ በዚህ መንፈስ ውስጥ የተጻፈ እንደመሆኑ፤ ከዚህ አሉታዊ ገጽታ የጸዳ አይሆንም። ያ ማለት ግን፤ ያገዛዙ ፖለቲካዊ እሳቤ፤ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ገጾች ያላገናዘበ፤ ፍላጎቶችን አጣጥሞ ለመሄድ ፈቃደኝ ያልሆነ፤ አግላይ እና ከፋፋይ ነበር ማለት እንጅ፤ ሕገ መንግስቱ፤ የአማራ ህዝብ ብቻ ሲገለል የተቀረው ኢትዮጵያዊ መክሮበት ዘክሮበት ያጸደቀው ነው ማለት አይደለም።
የሕዝብ ተሳትፎ አለ የሚባለው በመጀመርያ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ሲኖር ነው። ሕገ መንግስቱ ሲጸድቅ ደግሞ የአንድ ቡድን የበላይነት እንጅ የሀሳብ የበላነት አልነበረም። እርገጥ ነው፤ ሕገ መንግስቱን በማጽደቁ ሂደት ውስጥ “የተሳተፉ” የተለያዩ የብሄር የፖለቲካ ሃይሎች ነበሩ። ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች ተካፈሉበት የተባለ ጉባኤም ተካሂዶል። የሂደቱ አድራጊ ፈጣሪ ማን እንደነበር ግን ከማንም የተደበቀ አይደለም። በወቅቱ ጆሮ ያገኘ ሀሳብም ሆነ የተመለሰ ጥያቄ ካለ፤ የሕወሐትን ሥልጣን ከማጽናት አንጻር ያለው ጥቅም እየተሰላ የተስተናገደ እንጅ፤ በየትኛውም አካል የድርድር ውጤት የተገኘ አይደለም። የሆነውም ያልሆነውም ሕወሐት የፈቀደው እና የወደደው ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው ግርግር ሂደቱን ህጋዊነት ከማላበስ ውጭ ሌላ እርባና አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ በወቅቱ በአንጻራዊነት ሕወሐትን የመገዳድር ፖለቲካዊ ቁመና ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰበው ኦነግ፤ አገልግሎቱን እንደጨረሰ በግዜ ተገፍትሮ ወጥቷል።
ሕገ መንግስቱ፤ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ በተለየ መልኩ የአማራን ህዝብ ተሳትፎን አላረጋገጠም የምንለው፤ ሕገ መንግስቱን በማርቀቁ ድራማ፤ በአማራነት የተሰባሰበ ኃይል እንደ ሌሎቹ የብሄር ድርጅቶች ባለመካተቱ ከሆነ፤ በወቅቱ በዚህ መልኩ የተደራጅ አካል የነበረም አይመስለኝም። ያልበነረን ድርጅት ተገለለ ማለቱ ብዙም አያስኬድም። ከሂደቱ የተገፉት ከሕወሐት ልዩነት ተኮር ፖለቲካ የማይገጥም አስተሳሰብ የነበራቸው ሀገራዊ ተቋማት እና የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው። የተገፋው ያልተፈለገ አስተሳሰብ ነው። በሌላ በኩል፤ ህዝብ በነጻነት አማራጮችን መዝኖ፤ ወኪሎቹን የሚመርጥበት፤ የመረጠው ሳይስማማው ሲቀር መልሶ የሚያወርድበት ሥርዓት አጠቃላይ ሀገሪቱ ውስጥ ባልነበረበት ሁኔታ ስለ ማንኛውም ህዝብ ውክልና ማውራት አይቻልም። ሕወሐት የወከለው ራሱን እንጅ የትግራይን ህዝብ አይደለም። ኦነግ ስብስባ ላይ ስለተሳተፈ፤ የኦሮሞ ህዝብ ተወከለ ማለት አይደለም። በተመሳሳይ፤ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጡ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ፤ በአማራነት የተሰባሰበ የፖለቲካ ድርጅት በሄደቱ ተሳትፎ ቢሆን ኖሮ የአማራ ህዝብ ተወከለ የሚያስብል ጉዳይ አይሆንም።
ይህን ስል፤ በቅርጽም ደራጃ ቢሆን የነበረው መገለል በአማራ ህዝብ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተጽኖ በመዘንጋት አይደለም። አጠቃላይ፤ ስርአቱ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ተቆርቆሪ መስሎ፤ አማራ ላይ ለማሳደም የተንቀሳቀሰበት መንገድ፤ በህዝቡ ላይ ቀላል ያልሆነ ስነ ልቦናዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫና አሳርፎል። ያም ሆኖ፤ ሀገር አቀፍ አፈና በሰፈነበት፤ ህግ እና ሥርዓት እየተጣሰ፤ ፍጹም ዲሞክራሲያዊነት በጎደለው ሁኔታ ጸደቀ የተባለን ሕገ መንግስት መሰረታዊ ህጸጽ፤ ወደ ተሳትፎ ጎድለት ማውረድ፤ ነገሩን የምንረዳበትን እይታ በጣም ያዛባዋል። ዞሮ ዞሮ፤ በሕወሐት/ኢሕአዴግ ከፋፋይ ፖለቲካ የከሰርነው እንደ ሀገር ነው። ይህን መዘንጋት አያስፈልግም። ስህተቱም ሊታረም የሚችለው ችግሩ የጋራ መሆኑ ላይ መግባባት ስንፈጥር ብቻ ነው።
ባለፉት ግዚያት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ የብሄር ጥያቄ ብቻውን ተነጥሎ እና ከርሮ የተተረከበት ሁኔታ፤ ሁሉንም ዓይነት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን ጨፍልቆ በብሄር መነጽር ብቻ የማየቱ ዝንባሌ፤ የአማራ ህዝብ፤ በአጼዎቹ ዘመን፤ እግሩን ሰቅሎ ዓለሙን ሲቀጭ የነበር አስመስሎት ቆይቶል። በግልባጩ ደግሞ አሁን፤ የአማራ ብሄርተኝነት አካባቢ የምንሰማው ትርክት፤ በሕወሐት አገዛዝ የደረሰውን ጥፋት፤ በአማራ ላይ ብቻ የደረሰ ጥቃት አድርጎ ጠርዝ የማስያዝ አዝማምያ በሰፊው ይታይበታል።
በየማህበረሰቡ የሚነሱ ቅሪታውችን ትክክለኛ እና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ማቅረብ ክፋት የለውም። ይልቁኑ እርስ በርሳችን እንድንተያይ እና እንድንገናዘብ ይረዳል። ነገር ግን፤ የወጡበትን ብሄር በደል ነጥሎ ለማግዘፍ ሲባል፤ ነገሮችን ከልክ በላይ መለጠጥ፤ እውነታን ከማዛባቱም በላይ እንደ ሀገር የሚስተሳስሩንን ገመዶች እያቀጨጨ ከዕይታችን ያርቃቸዋል። ሰፊ እና እርስ በርሱ ተጠላላፊ የሆነን የሕብረተሰብ ሁነት፤ በሙሉ ገጹ አገላብጦ ከማየት ይልቅ፤ ከመኃከሉ አንድን ነገር ገንጥሎ ከልክ በላይ የማጦዝ ፖለቲካ፤ ሞቱ እና ሽረቱ አንድ ላይ በተገመደ ህዝብ መኃከል፤ የልዩነት ግድግዳ እየሰራ፤ የጋራ ራእይ ሰንቆ ወደፊት መጓዝን አዳጋች ያደርገዋል። አቶ ክርስቲያን ታደለ እንዳነሳው፤ ሁላችንም የኔ ብለን የምንቀበለው ሕገ መንግስት ያስፈልግናል። ያ የሚሆነው ግን፤ ልዩነትን ከሚያጎላ ትንተና እየተቆጠብን፤ አብሮነትን የሚያጎለብት አስተሳሰብ ስንመርጥ ነው። በአንድ ቡድን ተጽፎ በመላው ኢትዮጵያ ላይ የተጫነን ሕገ መንግስት፤ የአማራ ችግር ብቻ አድርጎ ማጥበብ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ አጀንዳ አላግባብ መከፋፈል ይሆናል። የጉዳዩንም ክብደት ያሳንሰዋል።
በእኔ እይታ፤ ሕገ መንግስቱን ለውይይት እና ክለሳ ክፍት እንዲሆን ግድ የሚሉን፤ ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። የመጀመርያው የሕገ መንግስቱ ችግር፤ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ወደመሆን የመጣበት አጠቃላይ ሂደት፤ ነጻ እና አሳታፊ ካለመሆኑ ጋር የሚያያዝ ነው። ሕገ መንግስት የጋራ ሰነድ እንደመሆኑ፤ ሂደቱ ያገባኛል ለሚል ዜጋ ሁሉ ክፍት መሆነ ነበረበት። በወቅቱ ይህን ዓይነት አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር አልነበረም። ሕገ መንግስቱ የጸደቀው፤ ሕወሐቶች የሀገሪቱን መዋቅር ሙሉ በሙሉ በመዳፋቸው ባስገቡበት፤ እነሱ ያልወደዱትን ሀሳብ ማንጸባረቅ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ወንጀል በሆነበት ዘመን ነው። አፈና ባለበት የታፈነ ሀሳብ አለ። ሀሳብ በውይይት የሚዳብርበት መንገድ ዝግ በሆነበት ሁኔታ የተዘጋጀ ሰነድ፤ በነጻ መድረክ እንደገና እንዲመረመር እስካልሆነ ድረስ፤ የሀገሪቱን ፈተናዎች በትክክል አጣጥሞ ለመፍታት እና ሀገርን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመምራት በቂ አቅም አለው ብሎ በደፈናው ይዘነው እንቀጥል ማለቱ የሚያስኬድ አይሆንም።
ሁለተኛው የሕገ መንግስቱ ችግር፤ ከጸሃፊው ከሕወሐት ማንነት የሚነሳ ነው። አፈና የየትኛውም አምባገነን አገዛዝ መገለጫ ባህሪ ነው። ሆኖም፤ አብዛኛዎቹ የዓአለማችን አምባገነኖች፤ እኔ አውቅልሀለሁ የማለት አባዜአቸው እንዳለ ሆኖ፤ ለሀገር አንድነት ባላቸው ታማኝነት አይታሙም። እንዲያውም ለብዙዎቹ፤ ሀገር ወዳድነት፤ ቅቡልነትን የሚገዙበት ዋነኛ መንገድ ነው። ሕወሐት ግን አፋኝ አምባገነን ብቻ አልነበረም። ስልጣን ላይ ለመውጣትም ሆነ፤ የበላይነቱን አስጠብቆ ለመቆየት፤ የሀገር ህልውና ምሶሶ በሆነው የህዝብ አንድነት ላይ ለመቆመር ዓይኑን ያላሽ ከፋፋይ ቡድን ነው። በሀገሪቱ ህልውና እና በራሱ ህልውና መካከል ሰፊ ተቃርኖ በፈጠረ ቡድን ፊታውራሪነት የተዘጋጀ ሰነድ፤ ከአዘጋጁ አጀንዳ የጸዳ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም።
ፍሬው ያማረ ቢሆን፤ በምን መልኩ ተጻፈ፤ በማን ተጻፈ የሚለው እምብዛም አከራካሪ ላይሆን ይችል ይሆናል። ሕገ መንግስቱ እንዲከለስ የሚያስገድደው ዋናው ምክንያት፤ ስራ ላይ ከዋለ ሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ፤ ራሳችን ያገኘነው ከፍተኛ አለመረጋጋት፤ ግራመጋባት እና አለመተማመን ውስጥ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ችግር ከዚህ ሕገ መንግስት በኋላ የተፈጠረ አይደለም። ነገር ግን፤ የቀደሙ ችግሮችን ባስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ነው ተብሎ የተነገረለት ሕገ መንግስት፤ ሌላ አደጋ አስከትሎ ከመጣ፤ መፍትሄ ተብሎ የተቀመጠውን አቅጣጭ እንደገና መፈተሹ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ ሰፊ ታሪክ፤ ብዙ መልክ ያለው ማህበረሰብ፤ ውስብስብ ችግሮች ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ፤ የሕገ መንግስት ረቂቅ የማዘጋጀቱ ስራ ይህን እውነታ የሚመጥን ሰፊ እና ጥልቅ የባለሙያ ጥናት ይጠይቅ ነበር። አሁን ስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት፤ ስልጣን ለጨበጠው አካል ፍላጎት ታዛዥ ከሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ቴክኒካል እገዛ በቀር፤ ይሄ ነው የሚባል የባለሞያ ጥናት እና ምርምር አላየውም። በመሆኑም፤ ለስሕተት ተጋላጭነቱ የሰፋ ነው።
ሕገ መንግስት ሀገራዊ ቃልኪዳን ነው። በትንሹም በትልቁም የሚደለዝ የሚሰረዝ መሆን የለበትም። ነገር ግን፤ የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሚል ማዕረግ ስለተለጠፈለት ብቻ አይነኬ አይሆንም። እንደ ማንኛውም ነገር ክብርን የሚያገኝው ከውጤቱ ነው። የአሜሪካ ሕገ መንግስት እንደ ታቦት የሚከበረው፤ የአሜሪካ ግዛቶች ከእንግሊዝ ነጻ ከወጡ በኋላ፤ አንድ ሀገር ሆኖ ለመቀጠል የገጠሟቸውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መሰናክሎች በብቃት አሻግሮ፤ መሰረቷ የማይናጋ ኃያል ሀገር ማቆም ስላስቻለ ነው። በአንጻሩ እኛ ከእኛ ሕገ መንግስት የተረፈን፤ ጠንከር ያለ ንጥሻ የሚያሰጋት ድንጉጥ ሀገር ነው። በአፈና ውስጥ፤ ነጻነትን አጥቶ መኖር አንድ ነገር ነው፤ የሀገር ህልውና፤ በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ግን፤ እዚህ የደረስነው እንዴት ነው ብሎ የመጣንበትን መንገድ የመፈተሹ አስፈላጊነት የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ይሆናል።
ከናፍቆት ገላው
