በፎቶው (በምሥለ አካሉ) ላይ የምትመለከቷቸው ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ (መካነ ትምህርት) ግፍ ሲፈጸምባቸው የሰነበቱ በወያኔ አጠራር የአማራ ክልል ተማሪዎች ናቸው፡፡
ለቀጣዩ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ቆይታቸው ዋስትና የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ “ክልላቹህ ነው!” በተባሉት የሀገሪቱ ክፍል ተመድበው ትምሕርታቸውን መማር እንዲችሉና “የአማራ ክልል መንግሥት ነኝ!” የሚለው በድኑ ብአዴን ይሄንን እንዲያስፈጽም ለመጠየቅ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡
በሰልፉ ላይ የተማው ነዋሪም ለምን አብሮ እንዳልወጣ ግን ሊገባኝ አልቻለም!!! ልጆቹ አይደሉም ወይ??? በዚህ ሰልፍ መፍትሔ የማይገኝ ከሆነ በቀጣዩ ጊዜ ግን የከተማው ሕዝብም አብሮ እንዲወጣ ማስተባበር ይኖርባቸዋል!!!
“አልበላሽንም ምን አመጣው?” አለች አሉ ጦጣ፡፡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወይም የዐቢይ አሥተዳደር አስቀድሞ አንዳችም የሚፈጠር ችግር እንደማይኖርና በቂ ዝግጅት እንደተደረገ እየለፈፈ ወላጆች “ልጆጃችሁን ወደየተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ላኩ!” ሲለፍፍ ሊፈጥሩት ያሰቡት አንዳች ችግር እንዳለ ታውቆኝ ነበር፡፡
የሁሉም ተማሪ የመጀመሪያ ምርጫ በቅርቡ ያለው ዩኒቨርሲቲ (መካነ ትምህርት) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሊያጠናው የፈለገው ዲፓርትመንት (ክፍለ ጥናት) በቅርቡ ካለው ዩኒቨርሲቲ የማይሰጥ ካልሆነ በስተቀር፡፡
አገዛዙ ግን ይሄንን የተማሪዎች ምርጫ ይጥልና የአማራውን ተማሪ አርቆ ወደሌላ ቦታ ይመድባል የሌላውንም ወደ ሌላ፡፡ አገዛዙ ይሄንን የሚያደርገው ሕዝቡ ርቀው ላሉ ልጆቹ ደኅንነት ሲል ከተቃውሞ እንዲሰበሰብ ለማድረግ እንደመያዣ መጠቀሙ ነው፡፡ ይሄ የአገዛዙ ቁማር እዚህ ላይ መብቃት አለበት!!!
ይሄ የአንዱን አካባቢ ተማሪ ወደሌላ የሌላውን ደግሞ ወደሌላ የማዘዋወር አሠራር ፋይዳ አለው ከተባለ የእርስበርስ ትውውቅ ለመፍጠር፣ የሕዝብ ለሕዝብን ትስስር ለማጠናከር የሚበጅ መሆኑ ነው፡፡ አገዛዙ ግን በግልባጩ ነበር ሲጠቀምበት የኖረው፡፡
እስከዛሬ እንደተመለከታቹህት በየዩኒቨርስቲው ግጭት በተነሣ ቁጥር የመጀመሪያ ተጠቂ የአማራ ተማሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በርካታ የሚያሳሱ እኅት ወንድሞቻችንንም አጥተናል፡፡ በርካታ የአማራ ወላጆች ለልጆቻቸው ደኅንነት በመሥጋት ልጆቻቸውን ከተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ በማስቀረት በግል ለማስተማር በመገደድ ለአላስፈላጊ ወጪ በመዳረግ ለኢኮኖሚና (ለምጣኔ ሀብትና) ተያያዥ ጉዳዮች ኪሳራና ጉዳት ሲዳረግ ቆይቷል፡፡ አቅሙ የሌላቸውና ልጆቻቸውን ለመላክ መጨከን ያልቻሉት ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው መማሩ እንዲቀርባቸው ያደረጉም ጥቂቶች አይደሉም፡፡
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በአማራ ተማሪዎች ላይ መሰንበቻውን ከተፈጸመው አረመኔያዊ ግፍ ለመረዳት እንደቻላቹህት ይሄ ዓመት ለአማራ ተማሪዎች በእጅጉ አሥጊ ነው፡፡ እመኑኝ አንድ ነገር ካልተደረገ በስተቀር ይሄ ዓመት የአማራ ወላጆች የደም እንባ የሚያነቡበት ዓመት ይሆናል፡፡
ይሄንን አደጋ ማስቀረት የምንችለው አንድ ነገር ያደረግን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ የገና እረፍት ዩኒቨርሲቲዎች ይዘጋሉ፡፡ ተማሪዎቹ ከእረፍት ከመመለሳቸው በፊት ድልደላው እንደገና ተደርጎ ከመጀመሪያ ዓመት እስከ መጨረሻ ዓመት ያሉ ሁሉም ተማሪዎች ወያኔ ክልልህ ነው ባላቸው በየክልል ክልላቸው እንዲመደቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መጠየቅና ማስፈጸም አለበት!!!
ሰላም ሲሆን፣ ሀገር ጫታ ሲሆን፣ ፍቅርና መተሳሰብ ሲሰፍን ለእርስ በርስ ትውውቅም ሆነ ለሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የኛ ልጆች ወደሌላ የሌሎቹም ወደእኛ እየሔዱና እየመጡ የሚማሩ ይሆናል!!!
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድልደላው በአስቸኳይ እንዲፈጸም ይረባረብ!!! ይሄንን ማድረግ ካልተቻለ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በዋናነትም አማራው ልጆችህ የወያኔ/ኢሕአዴግ ቁማር የመጫወቻ ካርድ እንዲሆኑ ወይም እንዲያልቁ እንደፈቀድክ እወቀው!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com
