January 11, 2019

eotc htt university

የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳሱን ከፈራሚነት ከማግለል አንሥቶ በ9 የዩኒቨርሲቲው ሓላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የተላለፈው ከቦታቸው የማንሣትና የማስተካከል ውሳኔ፣ ከዛሬ ጀምሮ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ወጪ እየኾነ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው፤
ደቀ መዛሙርቱ፥ውሳኔው ተፈጻሚ እስኪኾንና በጊዜያዊነት ከተመደቡት ሓላፊዎች ጋራ በቀጣይ ኹኔታ ላይ ግልጽ ውይይት እስክናደርግ ድረስ ወደ ትምህርት አንመለስም፤ ብለዋል፤ ከአቋረጡ ወር አልፏቸዋል፤ በጸሎት ቤቱ እንዳይገለገሉ ታግደው በሜዳ ላይ እየጸለዩ ነው፤
ካናዳ ከሚገኙትና በቅርቡ ወደ አገር ቤት ከሚመለሱት ጊዜያዊ ዋና ዲን ቀሲስ ዶ/ር መብራህቱ ኪሮስ ጋራ እየመከሩ ነው፤ “ያለውን ችግር እንረዳለን፤ ግቢውን በጋራ እናስተካክላለን፤ አብረን እንሠራለን፤” ብለዋቸዋል፤


በገንዘብ ብክነትና ምዝበራ፣ በአካዳሚያዊ ነፃነት አፈናና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ በዕቅበተ እምነት ድክመትና የተቋሙን አጠቃላይ የመማር ማስተማር ተልእኮ የማዛባት አስተዳደራዊ ብልሽት ማጣራት በተካሔደባቸው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ 9 ሓላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ቋሚ ሲኖዶስ፣ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከፍተኛ የማጽዳትና የእርምት ውሳኔ አሳልፏል፤ በምትካቸው ኹለት ዲኖችን(ዋና ዲንና የአስተዳደር ምክትል ዲን) በጊዜያዊነት መድቧል፤ በሌሎቹም ቦታዎች ላይ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸው ባለሞያዎች በውድድር እንዲመደቡ መመሪያ ሰጥቷል፤የኑፋቄ መጽሐፍ እንደጻፈና እንደሚያስተምር ማስረጃ የቀረበበት መምህር ጌታቸው ተረፈ፣ ከሥራው ታግዶ በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር፤ በፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው፣ መናፍቅነቱ ተረጋግጦ ከዩኒቨርሲቲው ቢባረርም በስግብግብ ሓላፊዎች ትብብር ወደ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ተዛውሮ በመማር ላይ የሚገኘውን ሱራፌል ወልደ ዮሐንስን አግዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው በጀት ለተመደበለት ዓላማ ብቻ እንዲውልና አላግባብ ባክኗል የተባለውም በአስቸኳይ ተገቢ የሒሳብ ማጣራት እንዲካሔድበት ቋሚ ሲኖዶሱ አዟል፡፡ በተጨማሪም፣ ቤተ መጻሕፍቱ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኔኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠናክሮ ዘመኑን የዋጀ የሙሉ ፈረቃ አገልግሎት ለመስጠት በሚችልበት ኹኔታ እንዲሟላ፤ በደቀ መዛሙርት የቀለብ ግዥ ሒደት ላይ የመማክርቱ ተወካይ እንዲሳተፍ፤ የክረምት አበላቸውም ከሌሎች መንፈሳዊ ኮሌጆች እኩል በወጥነት እንዲከፈላቸውና በአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ በሚል በአጣሪ ኮሚቴው የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን አጽድቆ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እንዲተገበሩ ወስኗል፡፡
የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄና የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሁም አጣሪ ኮሚቴው ከሒደቱ የወሰደውን ባለ12 ነጥቦች ግንዛቤና ቋሚ ሲኖዶሱ ተቀብሎ ያጸደቀውን ባለ14 ነጥቦች የውሳኔ ሐሳብ የያዘው ሪፖርት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ በመደበኛ የአዳሪ ደቀ መዛሙርት እና በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ጽ/ቤት መካከል የተፈጠረውን አመለግባባት አስመልክቶ የቀረበ ዘገባ
መግቢያ
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አንጋፋው ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አካል ኾኖ የትምህርት አሰጣጡ ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር እንደ አንድ ፋኩልቲ ተካቶ በደርግ መንግሥት እስከ ተዘጋበት ጊዜ ድረስ በርካታ ሊቃውንትን አፍርቷል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ያላሰለሰ ጥረት በቀድሞው መንግሥት የተወረሰው ዩኒቨርስቲ በ1986 ዓ.ም. ተመልሶአል፡፡ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ተተኪ ትውልድን ማፍራት ዋና ተልእኮው በማድረግ በጀት ተበጅቶለት በተለያየ የትምህርት ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛል፤ብዙ ምሁራንም አፍርቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜም በዩኒቨርስቲው አስተዳደር እና በመደበኛ አዳሪ ደቀ መዛሙርት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ ከኹለት ሳምንት በላይ[ሪፖርቱ እስከ ቀረበበት ወቅት ድረስ] የትምህርት አገልግሎታቸው ተስተጓጉሏል፤ ችግሩ በአጭር ጊዜ ተፈትቶ ዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሥራውን መቀጠል እንዲችል በቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በታዘዘው መሠረት ከአጣሪ ልዑካኑ የቀረበ ዘገባ ነው፡፡
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ደቀ መዛሙርት፣ በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ጽ/ቤት በኩል የአስተዳደር በደል እየደረሰባቸው መኾኑን ገልጸው ችግሩን ለማስወገድ የዳኝነት ኹኔታ እንዲታይላቸው፣ ኅዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም በግንባር በመቅረብና በጽሑፍ አመልክተዋል፡፡ በዚሁ አንጻር ያለው ኹኔታ ሲታይ፣ በአጣሪ ኮሚቴው አማካይነት ተመርምሮና ተጣርቶ ለመፍትሔ እንዲበቃ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ በርዕሰ ደብር መሓሪ ኃይሉ ሰብሳቢነት፣ በማመልከቻው የሰፈረው ዝርዝር ጉዳይ ተመርምሮና ተጣርቶ ሊኾን የሚገባውን ከውሳኔ ሐሳብ ጋራ ሪፖርቱ በአስቸኳይ እንዲደርሰን ታደርጉ ዘንድ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ትእዛዝ፣ በቁጥር ል/ጽ/166/338/2011 ዓ.ም. በቀን 2/4/2011 ዓ.ም. ተጽፎ በታዘዘው መሠረት አጣርቶ እነኾ ከውሳኔ ሐሳብ ጋራ አቅርቧል፡፡
የአጣሪ ልዑካን አባላት፡
ርእሰ ደብር መሓሪ ኃይሉ፡- የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ – የልዑካኑ ሰብሳቢ
መልአከ መዊዕ ሳሙኤል እሸቱ፡- የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ – አባል
ርእሰ ደብር በሪሁን አርኣያ፡- በጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ምክትል ሓላፊ – አባል
መምህር ማሞ ከበደ፡- በአ/አበባ ሀ/ስብከት የቁጥጥር አገልግሎት ክፍል ሓላፊ – የልዑካን ቡድኑ ጸሐፊ ስንኾን፣ የማጣራት ሥራው እንደሚከተለው ተከናውኗል፡፡
ለማጣራት የተከተልነው ዘዴ:-
ማጣራቱን በግልጽና በተሳካ ኹኔታ ለማካሔድ ኹሉም ደቀ መዛሙርትና የተማሪ መማክርት አባላት በጸሎት አዳራሽ እንዲገቡ ተደርጎ፣ ከልዩ ጽ/ቤት የተጻፈው ደብዳቤና ተማሪዎች በጽሑፍ ያቀረቡት አቤቱታ በንባብ ተሰምቷል፡፡ በልዑካኑ ሰብሳቢ በርእሰ ደብር መሓሪ ኃይሉ አማካይነት ገለጻ ተደርጎ ውይይቱ በይፋ ተከፍቷል፤ ደቀ መዛሙርትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ካቀረቡት አንድ ገጽ በተጨማሪ፣ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሰጣቸው በአንክሮ የምንጠይቃቸው ጉዳዮች በሚል ዐሥር ርእሰ ጉዳዮችንና በውስጡም ንኡሳን ነጥቦችን የያዘና በተጨማሪ አምስት የመፍትሔ ሓሳቦችንና ሰባት ነጥቦችን የያዘ የደቀ መዛሙርት የአቋም መግለጫ የያዙ ስምንት ገጽ ማመልከቻ በደቀ መዛሙርቱ ተወካይ በንባብ ቀርቧል፡፡
የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ
የኮሌጁ አስተዳደር ም/ዲን
የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን
የኮሌጁ የሰው ኃይል ሓላፊ
የኮሌጁ ሬጅስትራር ክፍል ሓላፊ
የኮሌጁ ምግብ ቤት ሓላፊ
የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ጸሐፊን ጨምሮ በየደረጃቸው ላደረሱብን ችግር ይጠየቁልን፤ የሚል ስለነበር፣ ኮሚቴው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለሚመለከተው ክፍል አንድ በአንድ በማቅረብ ጠይቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ደቀ መዛሙርት፣ የአስተዳደር አካላቱ አደረሱብን ብለው ያቀረቡት አቤቱታና የቃል ማብራሪያ፤
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ደቀ መዛሙርት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እና ለቋሚ ሲኖዶስ ያቀረቡትና ደረሱብን ያሉት አስተዳደራዊ ችግሮች አንኳር ነጥቦች፡-
የውኃ ዕጦት፣ የላይብረሪ (ኮምፒዩተር፣ አይሲቲ አለመኖር)፤
የጽዳት ችግር(የግቢው ቆሻሻ አጠቃቀም)
የተማሪ መዝናኛ አለመኖር
የምግብ ጥራት አዘገጃጀት ችግር
የመብራት ችግር
የዩኒቨርስቲው መተዳደርያ ደንብ በተማሪዎች ገጽታ ላይ ብቻ የሚያተኩር መኾን
የመጸዳጃ ቤት አያያዝና ጽዳት ችግር
የግቢው ጸጥታ ጉዳይ ለደኅንነት ስጋት መኾን የሚሉ ናቸው፡፡
በስምንት ገጾች በዝርዝር ካቀረቡት ውስጥ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያስፈልጋቸውና በአንክሮ የምንጠይቃቸው ጉዳዮች ያሏቸው ዐሥር አንኳር ነጥቦች፡-
በዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ዓምባገነናዊነትና ማናለብኝነት፣ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች(የመናገር፣ የመጠየቅ…ወዘተ) ጥሰት ረገጣዎች በደቀ መዛሙርት ላይ እየተፈጸመብን መኾኑ፤
ተቋማዊ መዋቅሩ በኹለንተናዊ መንገድ ለአስተዳደር ሓላፊነት በማይመጥኑ አመራሮች መያዝና በአቅም ማነስ ምክንያት የአስተዳደር ሒደቱ መዛባቱ፤
ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ግብአቶች በበቂ ኹኔታ አለመሟላት፤ብቃት ያላቸው መምህራን እንዳሉ ኹሉ ለሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት የማይመጥኑ፣ ለክሬዲት አወር ክፍያ ብለው ከቢሮ ሓላፊነት ጋራ ደርበው የሚያስተማሩ መምህራን መኖር፤
የአካዳሚያዊ ነፃነት(የመጠየቅ መብት)ማጣት፤
በመመሪያ ያልተደገፉና አግባብነት የሌላቸው የዕረፍት ጊዜያት መብዛት፤ በተለይም በመግቢያ ጊዜ፣ አንደኛ ሲሚስተር ባለቀ ጊዜ እንዲሁም፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ እጅግ ጎልተው መታየታቸው፤
የተሟላ ብቁና በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ያለው፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ፣ የዘመኑን ኹኔታ የዋጁ የመጻሕፍት ክምችት በበቂ ኹኔታ ያሉት የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት አለመኖሩ፤ በሁሉም መልክ ማለትም በድርሳነ መዛግብት፣ በኅትመት፣ በኦዲዮ ቪዥዋልና በዲጅታል ቅርጽ በሚገባ አለማቅረብ እንዲሁም የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር፤
ዘግይተው የተከፈቱ ሌሎች መንፈሳውያን ኮሌጆች፣ የመደበኛ አዳሪ መርሐ ግብር በማስተርስ፣ በዲፕሎማና በትርጓሜ መጻሕፍት ቤት ሲከፍቱ የእኛ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ግን በአመራሩ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ታች እያሽቆለቆለ በመሔድ ላይ መገኘቱ ዐይነተኛ ምሳሌ ነው፤
ለመምህርነት የማይመጥኑ ለትምህርት ዓይነቱም ተገቢ ዝግጅት የሌላቸው አካላት በማስተማር ሥራ ላይ መሰማራታቸው የትምህርት ጥራቱ እንዲሞት አድርጓል፤ ለምሳሌ የስብከት ዘዴ የተባለው የትምህርት ዓይነት ተጠቃሽ ነው፤
በቀደመው ጊዜ ከአኀት እና ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡና ለተቋሙ ይሰጡ የነበሩ የተለያዩ የነፃ ትምህርት ዕድሎች መቋረጣቸውና የደቀ መዛሙርቱ ዓለም አቀፋዊ ዕውቀትና አገልግሎት እንዳይዳብር አድርጓል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሠለጠነና ዘመኑን በዋጀ መንገድ እንዳያገለግሉና እንዳይረከቡ ዕንቅፋት ኾኗል፤ በተለይም የደረጃ ደቀ መዛሙርትን አስመልክቶ በተቋሙም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንም ዓይነት የማበረታቻ ሥራዎች እየተሠሩ አይደለም፤
የደቀ መዛሙርት መሠረታዊ ፍላጎት በተገቢው ኹኔታ አለመሟላት፤
በግቢው ውስጥ የንጹሕ ውኃና የጥሩ ምግብ አቅርቦት በበቂ ኹኔታ አለመኖር፤
የንጽሕና መጠበቂያ ስፍራዎች በአቅራቢያው በተሟላ ኹኔታ አለመኖር፣
የደቀ መዛሙርት የመንቀሳቀሻና የጤንነት መጠበቂያ የኾነው ስፍራ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ መደረጉ፤
ደቀ መዛሙርቱ ቢታመሙ የመጓጓዣ አቅርቦትና ለሕክምና የሚከፈል የቅድመ ክፍያ ብር አለመኖር ወይም የተሻለ የጤና ተቋም ጋራ ውል አለመኖሩ፤
የግቢውን ኹኔታና ቦታው የሚጠይቀውን ችሎታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ የሠራተኛ ቅጥር መፈጸሙ፤ በግቢው ውስጥ አንድ የሐዲስ ኪዳንና አንድ የብሉይ ኪዳን መምህራን ተቀምጠው ነገር ግን በአንድ ሰው ሊፈጸሙ የሚችሉ ተግባራትን ተከፋፍለው ከኮሌጁ የመሸከም አቅም በላይ የተቀጠሩ ሠራተኞች በየቢሮው መገኘታቸው፤
በአራት ዓመት ቆይታ ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን የምንማርበት ክፍለ ጊዜ ከመቶ ቀናት የማይበልጡ ስለኾነ ከሐዲስ ኪዳን የማቴዎስ ወንጌል፣ የዮሐንስ ወንጌል እና ራእየ ዮሐንስ፤ከብሉይ ኪዳን ደግሞ ከሙሴ መጻሕፍት የተወሰኑትንና ትንቢተ ኢሳይያስን ብቻ የመምንማር ሲኾን በያንስ መናፍቃን ከፍተኛ ጥያቄና ክርክር የሚያነሡባቸውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት አንዳቸውንም ለመማር ፈጽሞ ዕድል አላገኘንም፤
የዩኒቨርሲቲው መተዳደርያ ደንብ በ1992 ዓ.ም. የወጣና ከደቀ መዛሙርት ሕይወት ጋራ የማይጣጣም ከሕገ ቤተ ክርስቲያንም ጋራ በከፍተኛ ደረጃ የሚያጋጭ በመኾኑ በደቀ መዛሙርት ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች እንዲፈጸሙ ሽፋን እየሰጠ መገኘቱ፤
ኮሌጁ የተቋቋመበትን የመማር ማስተማር ዓላማና ተግባር ወደ ጎን በመተው በግንባታ ሥራና የሕንፃ ኪራይ ላይ ብቻ መጠመዱ፤
ለአራት ዓመታት በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ አሳልፎ ዲግሪ ይዞ ለወጣ ደቀ መዝሙር የማይመጣጠንና ዘመኑን የማይዋጅ የ900 ብር ወርኃዊ ደመወዝ ክፍያ ብቻ መኖሩ፣ በደቀ መዛሙርቱ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቡናዊ ቀውስ መፍጠሩ፤ የሚሉት ለዩኒቨርስቲው የአስተዳደር አካላት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ የሚከተሉትን ጉዳዮች አጽንዖት በመስጠት በቃል አቅርበዋል፤
ለኮሌጁ አስተዳደር የምናቀርበው የመብት ጥያቄ መልስ አያገኝም፤ መልስ ያላገኘ ጥያቄም ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይዘን ስንሔድ፣ ተጠሪነቱ ለመንበረ ፓትርያርክ ነው እንባላለን፤ ወደ መንበረ ፓትርያርክም ስንሔድ አይፈጸምም፤ ስለዚህ ኮሌጁ ተጠሪነቱ ለማን ነው?
ኮሌጁ የተቋቋመበት የመማር ማስተማርና ትውልድን በዕውቀት የመገንባት ተልእኮ ወደ ጎን በመተው ሕንፃ መገንባት ላይ ተጠምዷል፤ ልማቱን ባንቃወምም ለመማር ማስተማሩ ትኩረት ይስጥልን፤
ቅዱስ ሲኖዶስ ለኮሌጁ በየዓመቱ በሚመድበው ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተማሪ ቅበላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚጨምር ቢጠበቅም፣ የዩኒቨርሲቲው ቅበላ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሔዷል፡፡ በ2010 ዓ.ም. 38 የዲግሪ ደቀ መዛሙርት አስመርቆ አሁን ቅዱስ ሲኖዶስ አዲስ ተጨማሪ በጀት አጽድቆለት እያለ በ2011 ዓ.ም. የተቀበለው ተማሪ ግን 28 ብቻ መኾኑ በየጊዜው ቅበላው ለማሽቆልቆሉ ማሳያ ነው፡፡ ተማሪን በመቀነስ በጀቱ እየባከነ ነው፡፡ የተማሪ ማደሪያ ዶርምም ሳይቀር ያለጨረታ ለነጋዴ እየተከራየ ነው፤
የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የቢሮ ሥራዎችን በመተው ከኮሌጁ በተከራዩት ሱቆች ላይ የግል ንግዳቸውን በማካሔድ ኮሌጁ ዘርፈ ብዙ ችግር እንዲያጋጥመው ኾኗል፤
ያለአግባብ እና ያለጨረታ የተከራየው ጥንታዊው የኮሌጁ ሕንፃ፣ የአቶ ግርማ ክትፎ ቤት እንዲኾን በማድረግ በዐቢይ ጾም ዓሣ፣ በፆመ ፍልሰታ ዓሣ በማቅረብ፣ በፆመ ነቢያትና በፆመ ሐዋርያት በኮሌጁ ግቢ ክትፎና ጥብስ ሥጋ እየተሸጠ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እየተጣሰ ይገኛል፤
እንደ ቀድሞው ጊዜ፣ የተማሪዎች ተወካይ በምግብ ቤት አስቤዛ ግዥ በኮሚቴ አባልነት በመወከል ደቀ መዛሙርቱ በጀታቸውን ይቆጣጠሩ እንደ ነበር ይታወቃል፤ በአሁኑ ጊዜ ግን የተማሪን በጀት ለማባከን ሲባል የደቀ መዛሙርት መማክርትም ኾነ ደቀ መዛሙርቱ በግዥ ሒደት እንዳይሳተፉ ተደርጓል፤
በፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተጠንቶ በእምነቱ ችግር እንዳለበት ተረጋግጦ የተባረረው ሱራፌል ወልደ ዮሐንስ የተባለ ግለሰብም፣ የሦስት ዓመት የተማረበት ውጤትና መሸኛ ተሰጥቶት ወደ ሌላ ኮሌጅ ተዛውሮ እንዲማር ተመቻችቶለታል፤ ይህም የኑፋቄ ትምህርቱን ለማስፋፋት የሚያግዘው በመኾኑ ተገቢና ትክክል አይደለም፤
ጌታቸው ተረፈ የተባለው የኮሌጁ መምህር፣ መልሕቅ አሊቴያም (እውነት) በሚል ርእስ የጻፈው መጽሐፍ፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው፤” የሚል መጽሐፍ ከመጻፉም በላይ ደቀ መዛሙርቱን እየበረዘ እያለ ምንም ዓይነት ርምጃ ኮሌጁ ሊወስድ አለመቻሉ፤
በደቀ መዛሙርት የመማሪያ ሕንፃ ላይ ያሉ ለተማሪዎች የሚበቁ መጸዳጃዎችና መታጠቢያ ቤቶች ምድር ቤት ለሚኖሩ የአስተዳደር ባለ ሥልጣናት ጥቅም ተብሎ ከሕንፃው ውጭ ሽንት ቤትና መታጠቢያ ቤት ሕግን ባልተከተለ መልኩ እንዲሠራ በማድረግ ኮሌጁን ለብክነት የዳረገ ከመኾኑም በላይ ተማሪዎችንም ለእንግልት እየዳረገ መኾኑ የሚሉ ናቸው፡፡
በደቀ መዛሙርቱ ለተነሡ ዋና ዋና ጥያቄዎችና በመስክ ምልከታ እንዲሁም ከአንዳንድ ሰነዶች በተገነዘብናቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና መልስ ይሰጡን ዘንድ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን ጨምሮ የኮሌጁን አመራር አካላት ለኹለት ቀናት በየደረጃው አነጋግረናል፡፡
በየደረጃው ያለው የኮሌጁ አመራርም ጉዳዩን ያስረዳልኛል ያለውን መልስ የሰጠ ሲኾን፤ አንዳንድ ጉዳዮችን በሰነድ ማስረጃ ለማስደገፍ ጥረት አድርጓል፡፡ ከኮሌጁ አመራሮች የተሰጠውን ምላሽ፣ ማብራራሪያና ማስረጃ በማገናዘብ አጣሪ ልኡኩ በ12 ነጥቦች የተዘረዘረ ግንዛቤ ለመውሰድ ችለናል፤ ከዚህም በመነሣት የኮሌጁን ችግር ይፈታል ብለን ያሰብነውን ባለ14 ነጥብ የመፍትሔ ሓሳብ ቤተ ክርስቲያንን ማዕከል በማድረግ አቅርበናል፡፡
የሚመለከታችሁ የሥራ ሓላፊዎች፣ የመማር ማስተማር ሒደቱን ጤናማ ለማድረግና ለሊቀ ጳጳሱ ድካምና ልፋት ፍሬያማነት የመፍትሔ ሐሳቡን በቅንነት በመገንዘብ እንዲተገበር ታስችሉ ዘንድ በአክብሮት እየጠየቅን የግንዛቤ ነጥቦቹንና የመፍትሔ ሐሳቦቹን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
በአጣሪ ልዑካኑ የተወሰዱ ግንዛቤዎች፤
ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በኮሌጁ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አሻራ ያላቸውንና ለትውልድ ተሻጋሪ የኾኑ ተግባራትን ያከናወኑ ቢኾንም፣ በአሁን ሰዓት ይህን አመርቂ ውጤት ለማስቀጠል የሚያስችል አስተዳደራዊ ቁመና በኮሌጁ አለመኖሩ ግንዛቤ ወስደናል፤
በመማር ማስተማሩ ሒደት፣ በተማሪዎች ቅበላና ቁጥር፣ በትምህርት ዝግጅት፣ በመምህራን ምደባና ቅጥር፣ በክፍለ ትምህርት ምደባ፣ በማስተማሪያ መጻሕፍትና ግብዓቶች ዝግጅት አጠቃላይ ክፍተት እንዳለ ግንዛቤ ወስደናል፤
ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርስቲ ያደገበት ሒደትና ለተከፈቱት የትምህርት ዘርፎች ተመድበዋል የተባሉት ሹማምንት ምርጫና ምደባ ግልጽነት የጎደለው እንደኾነ ተገንዝበናል፤
የኮሌጁ አስተዳደር ዲን ቢሮ፣ በሥሩ የሚመራቸውን ክፍሎች ተቆጣጥሮ በማሠራትና በሥራ ሒደቶችም በሕግ ያልተፈቀዱ ተግባራትን በመከላከልና በመገደብ ረገድ ተነሣሽነት የሌለው መኾኑንና ደቀ መዛሙርት ላነሧቸው የምግብ፣ የንጽሕናና ተጓዳኝ ጉዳዮች በቂ ዝግጅት ሳይደረግ የቅበላው ሒደት እንዲከናወን ማድረጉ በኮሌጁ አሁን ለተፈጠረው ችግር መንሥኤ እንደኾነ ለማወቅ ችለናል፤
ተደራራቢ ሥራ በመያዝ በተመደቡበት ዋነኛ ሥራ ላይ ጫና እየፈጠሩ ያሉ የሥራ ክፍሎች በኮሌጁ ውስጥ መኖራቸውንና ይህም አሠራር የኮሌጁ ዋነኛ ተልእኮ የኾነውን የመማር ማስተማር ሥራን በማስተጓጎል በንግድና መሰል ሥራዎች ላይ ብቻ የተሳተፈ እንዲመስል እንዳደረገውና ደቀ መዛሙርት፣ “ግቢው ትምህርት ትምህርት አይሸትም፤” በማለት ላነሡት አቤቱታ ማሳያ እንደኾነ ግንዛቤ ወስደናል፤
በበጀት አጠቃቀም ረገድም፣ ከደቀ መዛሙርት ቅበላ ጋራ ተቀምሮ የቀረበው የ204 ተማሪ በጀት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ቢፈቀድም ዓመታዊው የተማሪዎች መጠን ግን ከ128 እስከ 145 አለመብለጡንና እንዲሁም በሌሎች የበጀት ርእሶች ሥር የተቀመጡት ሥርዓተ ትምህርቱን ለማገዝ የተፈቀዱ ማለትም የላይብራሪ መጻሕፍት መግዣ፣ እንደ ምርምርና ጥናት መሰል በጀቶች ከአራት ዓመት በላይ ለተፈቀደለት ዓላማ አለመዋላቸውን ለመገንዘብ ችለናል፤
በኮሌጁ የሕንፃ ኪራይና መሰል ተግባራት፣ ከሥራው ጋራ ተያያዥነት የሌላቸው ግለሰቦች፣ ሕጋዊ ውክልና ከኮሌጁ ሳይሰጣቸው “በአለቃችን ታዘን ነው” በማለት የሕንጻ ኪራይ ላይ ሲያከራዩና ውል ሲያዋውሉ እንደ ነበርና አሁንም ይህን ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ግንዛቤ ወስደናል፤
ደቀ መዛሙርቱ በማደሪያ ሕንፃቸው ይጠቀሙበት የነበረው የንጽሕና መጠበቂያና መጸዳጃ ቤት በቂ ባልኾነ ምክንያትና ተገቢ የባለሞያ ጥናት ሳይደረግበት እንዲታሸግ መደረጉና ያለጨረታ 790ሺሕ ብር የሚያወጣ ሽንት ቤት ከካቴድራሉ አጥር ጋራ ተያይዞ መሠራቱ ያለበቂ ጥናት የተደረገ ተግባር እንደኾነ ግንዛቤ ተወስዷል፤
በመናፍቅነት የሚጠረጠሩ መምህራን ጉዳይም በአስቸኳይ አለመታየቱ፣ በመናፍቅነት የተባረረ ደቀ መዝሙርም የትምህርት ማስረጃው እንዲሰጠው መደረጉ፣ ኮሌጁ በዕቅበተ እምነት ላይ ተገቢውን ሥራ እየሠራ አይደለም ለሚሉ አካላት ማሳያ እንደኾነ በግልጽ ታውቋል፤
አንዳንድ የኮሌጁ ማኅበረ ሰብእ፣ በአዲሱ ሕንፃ ላይ በንግድ ተግባር መሳተፋቸው በመማር ማስተማር ተግባር ላይ ክፍተት እንዲፈጠር እንዳስቻለ የቀረበው አቤቱታ ማሳያዎች እንዳሉት ግንዛቤ ወስደናል፤
በኮሌጁ የአዲሱ ሕንፃ ግንባታ ወቅት፣ ለአይሲቲ ተግባር የሚውሉ የግንባታ ማቴሪያሎች ሳይካተቱ በመቅረታቸው ደቀ መዛሙርቱ በኮሌጁ ውስጥ ኢንተርኔት ለመጠቀም አለመቻላቸውንና ምንም ዓይነት የኮምፒዩተር አገልግሎት እንደማያገኙ በማጣራት ግንዛቤ ወስደናል፤
ብቃት የሌላቸውና ከትምህርቱ ጋራ ምንም ተዘምዶ የሌላቸው መምህራንም፣ ክፍል ለመሸፈን በሚል ሰበብና ከክፍያ ጋራ ተያይዞ ለሚገኝ ጥቅም ሲባል እንዲያስተምሩ እንደሚደረግ፤ ይህም አቤቱታ በተደጋጋሚ እንደሚቀርብ ከደቀ መዛሙርቱ የቀረበውን ጥያቄ እውነትነት በአካዳሚክ ዘርፍ ያሉ ሓላፊዎች ማረጋገጣቸው የችግሩን ጉልህነት እንደሚያሳይ ግንዛቤ ተወስዶበታል፡፡
በመኾኑም፣ ከላይ ከተገነዘብናቸው እውነታዎች በመነሣት የሚከተለውን የውሳኔ ሐሳብ አቅርበናል፡፡
የውሳኔ ሐሳብ፤
የበላይ ሓላፊ ብፅዕ ሊቀ ጳጳሱ፣ በኮሌጁ ኹለንተናዊ ዕድገት ላይ ያስቀመጡት አሻራ ትውልድ የማይረሳውና ቤተ ክርስቲያንም ዘወትር ስትዘክረው የምትኖረው ሐቅ በመኾኑ ይህ እውነት ተጠብቆ እንዲኖርና ሊቀ ጳጳሱ ያለባቸውን የዕድሜና የጤና ችግር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሊቀ ጳጳሱን በኹለንተናዊ መልኩ የሚያግዛቸው፣ ገንዘብን ከማንቀሳቀስ ጀምሮ ሙሉ ሓላፊነት የሚሰጠው፣ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያለው ዋና ዲን እንደ ሌሎች ዩኒቨርሰቲዎች በውድድር እንዲመደብ ቢደረግ፤
የአካዳሚ ምክትል ዲን፣ የተመደቡበትን የትምህርት ዘርፍ ዘንግተው በሕንፃ ኪራይና መሰል ተግባራት መሳተፋቸው ለሥርዓተ ትምህርቱ መዳከም በምክንያትነት የሚጠየቁ በመኾኑ ከቦታቸው ተነሥተው በምትካቸው ብቁ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያለው ሰው ቢመደብና እርሳቸው በማስተማር ሥራ ላይ ብቻ እንዲመደቡ ቢደረግ፤
የአስተዳደር ምክትል ዲን፣ በኮሌጁ ለተፈጠሩት አስተዳደራዊ ክፍተቶች በግንባር ቀደምነት ተጠያቂ በመኾናቸውና ችግሮችን ተከታትሎ ከመፍታት ይልቅ በመገፍተርና ምክንያት በመፍጠር ችግሮችን መፈታት ስላልቻሉ ከቦታቸው ተነሥተው በቂ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያለው ባለሞያ በቦታው እንዲመደብ ቢደረግ፤
የኮሌጁ ፐርሶኔል፣ በማጣራት ሒደቱ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግና እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት በማለት ከፍ ያለ እገዛ አድርገዋል፡፡ ኾኖም ከተመደቡበት የፐርሶኔል ሥራ ውጭ በሕንፃ ተቆጣጣሪነት ላይ መመደባቸው በሠራተኞች ቁጥጥርና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ክፍተት መፍጠሩንም ያረጋገጥን በመኾኑ በአንድ የሥራ መስክ ብቻ ተመድበው እንዲሠሩ መመሪያ ለኮሌጁ እንዲሰጥና ያለሕጋዊ ውክልና የኮሌጁን የተማሪዎች ዶርም ከሊቀ ጳጳሱ ጸሐፊ ጋራ በመኾን በማከራየታቸው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ቢደረግ፤
የኮሌጁ ጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊ፣ ከግቢ ጽዳትና ጥበቃ ጋራ ተያይዞ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ክፍተት ያለባቸው በመኾኑና ከውሳኔ ውጭ ከጨረታና ግዥ ሥርዓት ጋራም ተያይዞ ለሚከናወኑ ሥራዎች ተገቢ ውሳኔዎች መኖራቸውንና ውሳኔዎችንም በሚመለከተው ባለሥልጣን መታዘዛቸውን በማረጋገጥ ማስፈጸም ሲገባቸው ሕግን ያልጠበቀ አሠራር በመሥራታቸው ተጠያቂ ስለኾኑ ከቦታቸው ተነሥተው የሚመጥናቸው ሥራ እንዲሰጣቸውና በቦታቸው ብቃት ያለው የጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊ እንዲመደብ ቢደረግ፤
የኮሌጁ የቤተ መጻሕፍት ሓላፊ፣ በንግድ ሥራ ተሠማርተው በላይብረሪ አጠቃቀም ረገድ ለተፈጠረው ክፍተት ዋና ተጠያቂ በመኾናቸውና ሓላፊው በማስተማር ሥራቸው ችግር እንዳለባቸው ደቀ መዛሙርትና የአካዳሚክ ዲን ያረጋገጡት በመኾኑ ከላይብረሪ ሥራ ውጭ በማስተማር ሥራ እንዳይሳተፉ እንዲደረግና የሚሰጣቸውን ሥራ አክብረው እንዲሠሩ ጥብቅ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ቢደረግ፤
የብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ጸሐፊ፣ ከተመደቡበት የሥራ መስክ ውጭ ከአካዳሚክ ዲኑ ጋራ በመኾን ከኮሌጁ ቦርድም ኾነ የማኔጅመንት ኮሚቴ ሕጋዊ ውክልና ሳይሰጣቸው ሕንፃ በማከራየት ላይ መኾናቸውን በማጣራት ተግባሩ በመረጋገጡና በመናፍቅነት ለተባረሩት ሱራፌል ወልደ ዮሐንስም የሊቀ ጳጳሱን ቲተር አሳርፈው የመሸኛ ደብዳቤ በመስጠታቸው በአስቸኳይ ከቦታቸው ተነሥተው ሊቀ ጳጳሱን ሊጠብቅ የሚችል በሥነ ምግባርና በሃይማኖት የተመሰከረለት ጸሐፊ እንዲመደብ ቢደረግ፤
በደቀ መዛሙርት ቀለብ ግዥ ላይ የተማሪ መማክርቱ እንደሌሎች ኮሌጆች ምንም ዓይነት ተሳትፎ የሌለው በመኾኑ በግዥው ሥርዓት ላይ ደቀ መዛሙርቱ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥብቅ መመሪያ ለኮሌጁ እንዲሰጥ ቢደረግ፤
ለመማር ማስተማር ተግባር እንዲውል በዋና መሥሪያ ቤቱ የሚፈቀደው በጀት ለሌላ ተግባር እንዲውል መደረጉ አግባብነት የሌለው በመኾኑ በጀቱ ለተፈቀደለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ጥብቅ መመሪያ ለኮሌጁ እንዲሰጥ፤ በየዓመቱ ለ204 እና ከዚያ በላይ ለኾኑ ደቀ መዛሙርት የሚኾን በጀት ከዋናው መሥሪያ ቤት የሚፈቀድ ሲኾን ኮሌጁ ግን፣ከ128 እስከ 145 ብቻ ለሚኾኑ ደቀ መዛሙርት በጀቱን እንደሚጠቀም ስለተረዳን ቀሪውን በጀት አስመልክቶ ተገቢ የኾነ የሒሳብ ማጣራት በአስቸኳይ እንዲደረግ፤
በሒሳብ ባለሞያነት የተቀጠሩ ሠራተኛ፣ በኮሌጁ የውጭ ኦዲተርነት በሚያገለግሉት በአቶ መብራቱ ጥቆማ ያለውድድር የተቀጠሩ መኾናቸውን የአስተዳደር ምክትል ዲን ያረጋገጡ በመኾኑ ይህ ደግሞ በኮሌጁ የሒሳብ ሥራ ላይ ከፍተኛ አለመተማመንና ክፍተት ሊፈጥር ስለሚችል ግለሰቧንም ጨምሮ ተገቢ ማስታወቂያ ተዘጋጅቶ የሒሳብ ባለሞያዎች በውድድር እንዲመደቡ ቢደረግ፤
የደቀ መዛሙርት የክረምት አበል ከሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋራ ሲነጻጸር ማነሱ አግባብነት የሌለው በመኾኑ እንደ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንና ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት እንደሚከፈላቸው ወጥ እንዲኾን መመሪያ ለኮሌጁ እንዲሰጥ ቢደረግ፤
መምህር ጌታቸው ተረፈ የተባለው የኮሌጁ መምህር፣ ያዘጋጀው መጽሐፍ፣ “ኢየሱስ ያማልዳል የሚል አለበት” በማለት የቀረበበት ክሥ ስለአለ በሊቃውንት ጉባኤ ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ለጊዜው ከማስተማር ተግባሩ እንዲታገድ ቢደረግ፤
በመናፍቅነት የተባረረው ሱራፌል ወልደ ዮሐንስ የተባለ ደቀ መዝሙር፣ ከቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ዶክመንት ተሰጥቶት በመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ተዛውሮ እንዲማር ያመቻቸው የኮሌጁ ሪጅስትራር ስለኾነ በአፋጣኝ ተነሥቶ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታማኝ የኾነ ሬጅስትራር እንዲመደብ ቢደረግ፤
ደቀ መዛሙርቱ ሥርዓትንና ሕግን እንዲጠብቁ፣ ከትምህርት ሥርዓቱ ጋራ ተያይዞ የተፈጠሩ ክፍተቶች መነሻ ተደርገው፣ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርታቸውን በሥርዓት እንዲማሩና በምርምርና በጥናት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ቤተ መጻሕፍቱ በፈረቃ እንዲሠራ ቢደረግ፤ የአይሲቲና የኮምፒዩተር አገልግሎት በአፋጣኝ እንዲዘረጋ፤ በአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የማገልገል ዕድል ተሰጥቷቸው በተማሩበት ትምህርት ልምድ እንዲያገኙ ቢደረግ፤ በልምምዳቸው ወቅት ስላላቸው አፈጻጸም ኮሌጁ ግብረ መልስ ኮሌጁ እንዲያሰባስብና እንዲያበረታታ ቢደረግ ጠቃሚ ስለሚኾን ይኸው ምክረ ሐሳብ እንዲተገበር ለኮሌጁ መመሪያ ቢሰጠው በማለት የውሳኔ ሐሳባችንን ከአክብሮት ጋራ እናቀርባለን፡፡
ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር
አቅራቢዎች፡-
ርእሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ
መልአከ መዊዕ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ
ርእሰ ደብር በሪሁን አርኣያ
መምህር ማሞ ከበደ