January 13, 2019
“መካካድ እና የድብብቆሽ ጨዋታ” የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን የርስ በርስ ግንኙነት ማሻከሩን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሊቀ-መንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ። ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድሩ ኢትዮጵያ አሁንም የመፍረስ ዕድል አላት ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዶክተር ደብረጺዮን ይኸን ያሉት በዛሬው ዕለት ከተለያዩ የዕምነት ተቋማት ከተውጣጡ የኃይማኖት መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው። ዶክተር ደብረጺዮን የኃይማኖት መሪዎች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ በአገሪቱ የሚታየው በዘር ላይ ያተኮረ ጥቃት መፍትሔ ካልተበጀለት የከፋ መዘዝ ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት ለጠፉ ጥፋቶች አራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕኩል ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ በአፅንዖት ተናግረዋል። ፓርቲያቸው ሕወሓት የነበሩበትን ችግሮች መመርመሩን የገለጹት ደብረጺዮን በኢሕአዴግ ዘንድ ግን መካካድ እና የድብብቆሽ ጨዋታ ዕክል ፈጥረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
«ለምንድነው የማትስማሙት ብትሉን የድብብቆሽ ጨዋታ ተጀመረ። እንደ ሕወሓት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢሕአዴግ እንደለመድነው አይደለንም» ያሉት ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድሩ የግንባሩ «የውስጥ ባሕል ተሸርሽሯል» ብለዋል። የግንባሩ አባላት የተማመኑበት ጉዳይ በአደባባይ ተክዷል ሲሉም ተናግረዋል። ኢሕአዴግ በስልጣን የቆየባቸው ያለፉት 27 አመታት «የጭለማ ዘመን» መባሉ ስሕተት እንደሆነም ጠቁመዋል። «አብረን ያጠፋንው አብረን መጠየቅ ሲገባን» ትግራይ እና ሕወሓትን ለይቶ ተጠያቂ የማድረግ ዝንባሌ ታይቷል ሲሉም ወቅሰዋል። ዶክተር ደብረጺዮን በራያ እና በወልቃይት ጉዳይ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ ያሏቸውን ወገኖች አምርረው ወቅሰዋል። ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ ከአማራ ክልላዊ መንግሥት አቻቸው ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተገናኝተው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።