January 16, 2019
ከእውነቱ ይታያል (15.01.2019)
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት ዋነኛ ግብ አድርጎ የያዘው ጉዳይ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ መገንባት ነው። ይህ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ሲጠበቅ ብቻ ነው። ከዚህ አልፎ ያንድን ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ ወይም ቡድን ያልተገባ ጥቅምና የበላይነት ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ የህገመንግስቱን መሰረታዊ መነሻ ይደረምሳል ብቻ ሳይሆን በማንኛውም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊም ፍትሃዊም ሊሆን አይችልም።
ያለመታደል ሆኖ ግን ብዙዎቻችን እንደምንገነዘበው ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በአንድ ቡድን ብልጣብልጥነት፣ አልጠግብ ባይነት፣ ጀብደኝነት እንዲሁም አምባገነንነት በሌላው ወገን ሞኛሞኝነት፣ የዋህነት፣ ፍርሃት ወይም ችልተኝነት ሊባል በሚችል ሁኔታ ህገመንግስት ተጥሶ የዚህን ቡድን የበላይነትና ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት ሲደረግ እንደነበረ ተስተውሏል። ይህ ያንድን ቡድን የበላይነትና ጥቅም የማስከበር እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ምንጭ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኢህአዴግም ይህን የችግሮች ሁሉ መነሻ የሆነ አደገኛ እንቅስቃሴ አምኖ እንዲታረም ከማድረግ ይልቅ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው በሚል ቅርንጫፍ ላይ በመንጠልጠል በክህደት የመከላከል አቅጣጫን በመምረጡ ምክንያት ራሱን መቀመቅ አስገብቶ ሃገሪቷንና ህዝቦቿን ሊበታትን ቋፍ ላይ ደርሶ ነበር።
ለህዝቡ ምስጋና ይግባውና ባደረገው ብርቱ ትግልና በከፈለው መስዋዕትነት የኢህአዴግን እጅ ጠምዝዞ ራሱንና ሃገሩን ለጊዜውም ቢሆን ገብተውበት ከነበረው አረንቋ ለማውጣት በቅቷል። ይህን ተከትሎም ኢህአዴግ ውስጥ አጋጣሚውን በመጠቀም የተፈጠረ ሃይል ህዝቡን በደጀንነት በመያዝ ወደስልጣን ለመምጣት ችሏል። በርግጥ ይህ ሃይል ወደስልጣን የመጣበት ሂደት ዴሞክራሲያዊ ነበር ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ዘገባ እንደሰማነው ከሆነ በኢህአዴግ ሊቀመንበር የምርጫ ሂደት ወቅት ባንድ ወገን ተራው የዚህ ወይም የዚያ ብሄር መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ በሌላ ወገን ደግሞ የቡድነኝነት ዝንባሌዎች እና እንቅስቃሴዎች ይታዩ እንደበረ ለመገንዘብ ከባድ አልነበረም። ከዚህ ባለፈ ከምርጫው በፊትም ቢሆን ቡድነኝነት የተስተዋሉባቸው እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ መካድ አይቻልም። በግልፅ ሲነገር እንደሰማነውም ቢሆን የምርጫውን ሂደት ከእግር ኳስ ጨዋታ አሰላለፍ ጋ በማመሳሰል አሸንፎ የመውጣት ብርቱ ጥረት እንደነበረ ተገንዝበናል።
ከዚህ ሁሉ ይልቅ የምርጫ ሂደቱ ምሉዕና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችል የነበረው ያሉት 180 የሚሆኑ የኢህአዴግ ም/ቤት አባላት እያንዳንዳቸው ሉዓላዊ ሆነው በነፃና በፍላጎት ከቀረቡ ተጠቋሚዎች መካከል ብቃት አለው ብለው ያመኑበትን ሰው ቢምርጡ ኖሮ ነበር። ይህ እዛው ሳለ በአራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል መተማመንና የአብሮነት ስሜት ሊያጎለብት የሚችል አጋጣሚ ነበር። በነገራችን ላይ በዚህ መንገድ ተሂዶም ቢሆን ዉጤቱን ላይቀይረው ይችል እንደነበረ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ በዚህ ምርጫ ወቅት የለውጥ ሃይል ነኝ የሚለው አካል ያመለጠው ታሪካዊ እድል እጂግ በጣም ፈታኝ በሆነ ጊዜም ቢሆን በምርጫ ዉጤቱ ብቻ ሳይሆን በሂደቱም ደሞክራሲያዊነት ላይ የማይደራደርና የፀና አቋም ያለው መሆኑን ማሳየት አለመቻሉን ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲ የሚለካው በውጤቱ ብቻ ሳይሆን በሂደቱም ነው። እንዲያውም በዴሞክራሲ እይታ ከውጤት ይልቅ ሂደት በጣም ወሳኝ ቦታ አለው። ሂደቱ ምንም ይሁን ምን በሚል እሳቤ ውጤቱ ላይ የሚያተኩር መንግስት የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው በሚል ማኪያቬሊያዊ ፍልስፍና የሚመራ አምባገነናዊ መንግስት መሆኑ አይቀርም።
ወጣም ወረደ የዚህ ምርጫ ውጤት የሆኑት የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ በሚመሩት ድርጅታቸው ውሳኔ መሰረት ምናልባትም ከዛ ባለፈ ሁኔታ የተለያዩ አወንታዊ ተግባራትን አከናውነዋል። ከዚህ ጋ ተያይዞ ሊገለፅ የሚገባው አብይ ነገር ጠቅላይ ሚ/ሩ ያከናወኗቸው ተግባራት አወንታዊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የፈፀሙበት ጊዜም ቢሆን ከኢህአዴግ ዘገምተኛ ባህል በእጅጉ በወጣና ፈጣን በሆነ መንገድ ነው። እኝህ ጠቅላይ ሚ/ር ከፈጸሟቸው አወንታዊ ተግብራት ውስጥ የእስረኞች መፈታት ትልቁን ቦታ የሚይዝ ነው። የተፈቱት እስረኞች አገር ቤት ያሉት ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ የውጭ ሃገራት የነበሩትንም ያካትታል። ሌላው ወሳኝ የሆነው አወንታዊ ተግባራቸው ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የወሰዱት እርምጃ ነው። በዚህ ረገድ ሊነሳ የሚገባው ትልቅ ጉዳይ ከሃገር ውጭ የነበሩት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች/ድርጅቶች ወደሃገር ውስጥ እንዲገቡና አገር ውስጥ ያሉትም ጭምር በነፃና በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንዲችሉ መግለፃቸው ብቻ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ የሚያበረታታ መንገድን መከተላቸው ነው። ከዚሁ ሳንርቅ ከሃገር ውጭም ይሁን በሃገር ውስጥ ያሉ የሚድያ ተቋማት (ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ) በነጻ እንዲንቀሳቀሱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም። የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትም ቢሆን በአልጄርሱ ስምምነት መሰረት እንዲፈታ አቋም መያዛቸውና ይህንኑ አቁማቸውን ለማስፈፀም እያደረጉ ያለው ጥረትም አንዱ የጠቅላይ ሚ/ሩ አወንታዊ ተግባር ተደርጎ ሊገለጽ የሚችል ነው። ሌሎች አወንታዊ የሆኑ ተግባራትንም መዘርዘር ይቻላል። የዚህ ፅሁፍ አላማ እሱ ባለመሆኑ ግን በዚህ ረገድ ያለውን ሃሳቤን እዚህ ላይ መግታት መረጥኩ። የጠቅላይ ሚ/ሩን አወንታዊ ተግባራት በዚህ መልክ እንደማሳያ ካነሳሁ አይቀር አሉታዊ ናቸው የምላቸውን ደግሞ እንዲሁ ለማሳያ ያህል አጠር አድርጌ እንደሚከተለው ለመግለፅ እሞክራለሁ።
የመጀመሪያውና ዋናው አሉታዊ ጉዳይ የተቋማት ግንባታና ገለልተኝነትን የተመለከተ ነው። በዚህ ዙሪያ ዶ/ር አብይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ ስህተት ሊማሩ ይገባል። ነብሳቸውን ይማርና አቶ መለስ እንደ ግለሰብ አንድም ሶስትም ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከማንም ሰው በላይ ምን አልባትም ደግሞ ከፈጣሪ ጋ እንደ እኩያ እየታዩ ሃይ ባይ ሳይኖራቸው ፖለቲካውን አመሰቃቅለውት እንዳለፉ የሚታወቅ ነው፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ተቋማት ቀጭጨው፣ ተዳክመውና ተልፈስፍሰው የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ይቅርና የራሳቸውን ስልጣንና ተግባራት እንኳን በሚገባ የተረዱ የማይመስሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ከዚህ አንፃር የህግ አውጭው አካል ስራ አስፈፃሚውን የመቆጣጠር ህገመንግስታዊ ስልጣን ያለው ቢሆንም የተገላቢጦሽ በስራ አስፈፃሚው ቁጥጥር ዉስጥ ገብቶ የቆየ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይገነዘባል። የፍትህ አካላቱም ቢሆኑ ህገ-መንግስቱ ያጎናፀፋቸውን ገለልተኝነት ዘንግተው ባብዛኛው የስራ አስፈጻሚው ጉዳይ አስፈፃሚ የሆኑበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑም ሌላው ግልፅ የሆነ ነገር ነው።
አሁን ባለንበት ወቅት ላይም ቢሆን ዶ/ር አብይ የሚመሯቸው የመንግስትም ይሁን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አካላት የነዚህን ሁለት ተቋማት በተለይም የህግ አውጭውን ሉዓላዊ ስልጣን የመጋፋት አዝማሚያወች እየፈፀሙ እንደሆነ የሚያመላክቱ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ማሳያዎች አንዱ ከኢትዮ-ኤርትራ የአልጀርስ ስምምነት ጋ የተያያዘው ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ይህን ስምምነት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት በ1993 አ.ም የወሰደው አቋምና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንዲፀድቅ የተደረገው አዋጅ አምስት የሚሆኑ የሰላም ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ይህን አዋጅ የሻረ ሌላ በተወካዮች ም/ቤት የወጣ አዋጅ መኖሩን አልታዘብኩም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ዶ/ር አብይ በሚመሩት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ ብቻ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደተቀበለች ለህዝብ ተገልፆ ወደተግባር ተገባ። ይህ ሂደት በውጤቱ ሲለካ አወንታዊ ቢሆንም በሂደቱ ሲመዘን ግን ዶ/ር አብይ የሚመሩት የኢህአዴግ ስራ ስፈፃሚ ኮሚቴ የተወካዮች ም/ቤትን ሉዓላዊ ስልጣን የተጋፋ መሆኑን መረዳት አይከብድም። ይህ ደግሞ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ለህገመንግስታዊ ደሞክራሲ ግንባታ ያለውን የተዛነፈ አቋም ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ህግመነግስታዊ ሊሆን ይችል ዘንድ በ1993 የወጣው የተወካዮች ም/ቤት አዋጅ እንዲሻር ወይም እዲሻሻል በማድርገ በምትኩም አሁን ዶ/ር አብይ በሚመሩት የኢህአዴግ ስራ አስፍፃሚ ኮሚቴ የተያዘው አቋም በተወካዮች ም/ቤ ተቀባይነት አግኝቶ አዋጅ እንዲወጣለት መደረግ ነበረበት።
ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ ዶ/ር አብይ ወደሃላፊነት ሲመጡ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የተደረገበት አግባብ ነበር። በርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ በማንኛውም መመዘኛ ሲታይ የሚደገፍ ነው። በተለይም የሰብዊ መብቶች እንዳይጣሱ ለማድረግና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መደረጉ ከአስፈላጊም በላይ አንገብጋቢ ነበር። ይሁንና የተወካዮች ም/ቤት ገና ሳያፅድቀው ጠቅላይ ሚ/ሩ የካቢኔያቸውን ውሳኔ መሰረት አድርገው አዋጁ እንደተነሳ ለህዝብ መግልጫ መስጠታቸው አሁንም በተወካዮች ም/ቤት የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነትና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ላይ ያላቸውን የተዛነፈ እይታ ያሳያል።
ከተቋማት ገለልተኛነትና ከህግ የበላይነት አንጻር የዶ/ር አብይ አስተዳደር የፈፀመው ሌላው ዝንፈት ደግም ከአዲስ አበባ ወጥቶች ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሁኔታ ላይ ነው። እነዚህ ከአንድ ሽህ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ የታጎሩት ህጋዊ በሆነ መንገድ ክስ ቀርቦባቸውና በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ሳይሆን ለፌዴራል መንግስቱ ተጠሪ በሆነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውሳኔ ነው። ይህ የሚያሳየው የመንግስት የስራ አስፈፃሚ አካል በህገመንግስቱ የተቀመጠውን የስልጣን ክፍፍል በመጋፋት የፍትህ (የፍርድ ቤትን) ስራ እየሰራ ያለ መሆኑን ነው። በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት ሰውን ሰብስቦ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝና ውሳኔ እንደ እንስሳት ካምፕ ውስጥ ማጎር እንደባህል የተወሰደው ኢትዮጵያ ውስጥ ካልህነ በስተቀር ሌሎች አገሮች ውስጥ ጭራሽ የሚታወቅ አይመስለኝም። አንድ የመንግስት የስራ አስፈፃሚ ዘርፍ ይህን አይነትና መሰል ተግባራትን ለመፈፀም ስልጣኑ ከየት እንደሚመነጭ እስካሁን የተወቀ ነገር የለም፤ ጉልበትና ማን አለብኝነት ካልሆነ በስተቀር።
ሌላው ከህግ የበላይነት ጋ ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት አሉታዊ ድርጊት የጠቅላይ ሚ/ር ፅ/ቤት ፕሬስ ሃላፊ (አሁን ምድባቸው የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ዴስክ ሃላፊ ሆነዋል ተብሏል) ሹመት የሚመለከተው ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የውጭ ሃገር ዜጋ የመንግስት መስሪያ ቤት ላይ ሊሾም የሚችለው ቦታውን ለመያዝ የሚያስችል ብቃት ያለው ኢትዮጵያዊ ማግኘት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ቦታውን ሊሸፍን የሚችል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጠፍቶ ነው የውጭ ሃገር ዜጋ እንዲሾም የተደረገው? ብሎ መጠየቅ አግባብነት ይኖረዋል። መልሱ ደግሞ በፍፁም ሊሆን አይችልም የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ ቦታውን ሊሸፍን የሚችል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሰው ይጠፋል ተብሎ ስለማይገመት ነው። ይልቁንም ዋናው ምክንያት መንግስት ለጡንቻ እንጅ ለህግ የበላይነት ያለው ግንዛቤ አሁንም የተዛነፈ መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ሃላፊዋ ለቦታው ያላቸውን የብቃት ማነስ በመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ከጋዜጠኖች ይቀርቡ ለነበሩ ጥያቄዎች ይሰጧቸው የነበሩትን ቁንፅልና ግልብ ምላሾች በማየት መረዳት የሚቻል ይመስለኛል። እነዚያ ይሰጡ የነበሩ ምላሾች የሚያሳዩት ትልቅ ቁምነገር ቢኖር ሃላፊዋ ምን ያህል ለመንግስት ፖሊሲዎች፣ ህጎችና ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እንግዳ እንደነበሩ ነው።
ከዚሁ ከህግ የበላይነት ጉዳይ ሳልወጣ ማንሳት የምፈልገው ነጥብ በመንግስት መሪ ደረጃ ፀጉረ ልውጥ በሚል ህገመንግስታዊ የሆነን የዜጎች በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ለመገደብ ጥረት የተደረገበትን ሁኔታ ነው። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ለዜጎች ከሚሰጣቸው መብቶች ውስጥ አንዱ በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ነው። የዜጎች በነፃ የመንቀሳቀስ ብቻም ሳይሆን በመረጡት ቦታ የመኖርና ሰርቶ የማደር መብቶችም ህገመንግስታዊ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ አንፃር ሳየው ፀጉረ ልውጦችን ነቅታችሁ ጠብቁ ብሎ መልዕክት በማስተላለፍ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሰርቶ የማደር መብቶችን ለመጣስ መሞከር ለህግ የበላይነት መከበር ካለ የተዛባ ግንዛቤ ካልሆነ በስተቀር ሌላ መነሻ ሊኖረው አይችልም።
በዚህም አለ በዚያ ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አወንታዊ ጎኖች የበለጠ እየተጠናከሩ፤ አሉታዊ ጎኖች ደግሞ በሂደት እየታረሙ ሊሄዱ ይችላሉ በሚል እሳቤ ወደተነሳሁበት የዚህ ፅሁፍ አላማ ልግባ። ይህን ፅሁፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ስለታየችኝ ነው። በአንድ በኩል ብሩህ የዴሞክራሲና የብልፅግና ተስፋ ይታየኛል። ይህን ተስፋ እንድሰንቅ ያደረገኝ ዋናው ምክንያት የህዝቡ በተለይም የወጣቱ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሃዊነትና ለእድገት ያለው ግንዛቤ ኣያደገ መምጣቱ ነው። በሌላ አነጋገር ህዝቡ የስልጣኑ ባለቤት ራሱ መሆኑን የተረዳበት ወቅት ላይ መድረሱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ተስፋ የሚያጨልሙ የአካሄድ ስህተቶች እየተመለከትኩ ነው። በተለይም የቅንነት መጓደልና የጋራ እሴቶቻችንና ጥቅሞቻችን ላይ ያለመግባባት ችግሮች ጎልተው እየታዩ ነው። በዚህ ላይ በምክንያት ሳይሆን በመንጋ የማሰብ፣ አለመደማመጥ፣ አለመተማመን፣ የአብሮነት መጓደልና እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚሉ ነገሮች እየገነኑ መጥተዋል። ይህ አለመተማመን፣ ሽኩቻና አለመደማመጥ ሌላው ይቅርና በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለይ ደግሞ ኢህአዴግን በመሰረቱት ህወሃትና ብአዴን (አዴፓ) ጎልቶ እየታየ ነው። በእኔ እምነት ለዚህ ሁሉ ምክንያት ይሆናሉ ብየ የማስባቸው በኢህአዴግ በእራሱ በተለይም ደግሞ በህወሃት ሰዎች የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ ችግሮችና መፍትሄ ይሆናሉ ብየ የማስባቸውን ፍሬ ነገሮች ከዚህ በታች ለማሳየት እሞክራለሁ።
አንደኛው መሰረታዊ ችግር ከማንነት ጋ ተያይዞ እየተነሳ ያለው ውዝግብ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት የወሰን ስሪት የተከወነው ቁንቋን፣ ባህልን/ልምድን፣ ስነልቦናዊ ትሥስርን እና የቦታ አቀማመጥን መሰረት አድርጎ ነው። ይህ የወሰን ስሪት ሲከወን በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበረ ግልፅ ነው። ጥያቄዎቹ ሲነሱ የተፈቱበት መንገዶች ደግሞ ተመሳሳይነት የሚጎድላቸው ነበሩ። ይህም ማለት ባንዳንድ አከባቢዎች ተነስተው የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ የተደረገው በህዝብ ውሳኔ ነው። ይህ መንገድ ተመራጩና ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ቦታ የሰጠ ምላሽ ነበር። ባንድንዶቹ አከባቢዎች ደግሞ የተመረጠው የችግር አፍተታ ዘዴ አስተዳደራዊ ነበር። የዚህ መንገድ ዋና ገፊ ሃሳብ ደግሞ ስግብግብነት ላይ የተመሰረተ የግዛት መስፋፋት ስለነበር አሁን ላይ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መነሻ መሆኑ አልቀረም። በተለይ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልላዊ መንግስታት መካከል ባሉ አንዳንድ አከባቢዎች ለምሳሌ በወልቃይት፣ በራያና በመሳሰሉ አከባቢዎች በነበረው የወሰን ስሪት ምክንያት የተፈጠረው ቁርሾ እያስከተለው ያለው ውጣ ውረድ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነዚህ አከባቢዎች ወደትግራይ ክልል የተካለሉበት መንገድ በህወሃት ሰዎች እጀ እረጅምነትና በመሳሪያ የተደገፈ ጡንቻ ምክንያት የነሱን የቆየ ፍልጎት ለማሟላት እንጅ በአከባቢው ይኖር የነበረውን ህዝብ ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ ባለመሆኑ በተለያየ ጊዜ በሚከሰት ግጭት የሰው ህይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ እንዲሁም በሁለቱ ክልሎች መካከል የእሰጥ አገባ መነሻ እየሆነ መጥቷል። ምናልባትም በነዚህ አከባቢዎች ያሉ ችግሮች ሚዛናዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ባስቸኳይ የማይፈቱ ከሆነ በአማራና በትግራይ ክልላዊ መንግስታት መካከል የጦርነት መነሻ ምክንያት ሆነው የሃገሪቱን አንድነት ሊያናጉ የሚችሉ ችግሮች መሆናቸው የማይቀር ነው። ስለዚህ በነዚህ አከባቢዎች ያሉ ችግሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ባስቸኳይ የመፈታት ያለመፈታት ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነት የማስቀጠል ያለማስቀጠል ጉዳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።
ጥያቄው ያለው በምን መንገድ ቢፈታ ዘላቂ ይሆናል የሚለው ላይ ነው። በእኔ እምነት ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታው ይችላል ብዬ የማስበው ርምጃ የህዝብ ውሳኔ ብቻ ነው። በህዝበ ውሳኔው ተሳታፊ ሊሆን የሚገባው ህዝብ ደግሞ የወሰን ስሪቱ በተከወነበት ወቅት በቦታው ይኖር የነበረው ህዝብ እንጅ ከዛ በኋላ ታስቦበትም ይሁን በሌላ መንገድ የሰፈረውን ህዝብ ሊጨምር አይገባም። በወቅቱ በቦታው ይኖር የነበረውን ህዝብ ለመለየት ደግሞ የተካሄዱ የህዝብና ቤት ቆጠራዎች፣ ግብር የተከፈለባቸውንና ሌሎች ሰነዶችን መመርመር ይቻላል። ይህ መሆን አለበት ብዬ ሃሳብ እያቀረብኩ ያለሁት ኢህአዴግ በፈፀመው ድርጊት ምክንያት ጉዳት ደርሶብኛል ያለ አካል በራሱ በኢህአዴግ መታከሙ/መጠገኑ የተጓደለው ፍትህ የተመለሰበትን ሂደት ፈረንጆቹ እንደሚሉት (Restorative Justice Process) ከቂምና ከቁርሾ የፀዳ ያደርገዋል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። የህዝብ ውሳኔው ከተካሄደ በኋላ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳ ክልል ካለ ታሪካዊ፣ ህጋዊና ሌሎች ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ጥያቄውን ለፍትህ ስርዓቱና ከዛም ለፌደሬሽን ምክርቤት አቅርቦ እንዲፈታ ማድረግ ህገመንግስታዊ መብት ነው። በዚህም አለ በዚያ ኢህአዴግ ሃገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ቦታዎቹ ላይ የሰፈሩ ሰዎች ካሉ የህዝብ ውሳኔው አካል መሆን ባይችሉም በየሚኖሩበት አከባቢ የተለመደ ኑሯቸውን ለመቀጠል እስከፈለጉ ድረስ ህገመንግስታዊ መብታቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ሁለተኛው ትልቅ ችግር ከሰንደቅ አላማ ጋ ተያይዞ እየተነሳ ያለው ውጥንቅጥ ነው። እስካሁን ባለ ልምድ የሚታወቀው ሰንደቅ አላማ አንድ አገር በውስጥም ሆነ በውጭ የሚመሰልበት ገኡዝ ነገር ነው። ለዚህም ነው የማንኛውም ሃገር ሰንደቅ አላማ በየመንግስት ቢሮዎች፣ ክብረ በአላት፣ የስፖርታዊ ውድድሮች፣ ሁሉም አይነት ሰልፎች፣ እና አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የሚታየው። ይህ በመሆኑም ሰንደቅ አላማ ቢቻል በሁሉም ካልሆነም ባብዛኛው በአገሩ ዜጎች ተቀባይነት ሊያገኝ መቻል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ስናይ ግን ውጥንቅጡ የወጣ የህዝብ እይታ ነው ያለው። አንዳንዱ ሰንደቅ አላማየ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ሆኖ መሃሉ ላይ ኮከብ ያለበት ነው ይላል። ሌላው አይ የኔ ሰንደቅ አላማ ኮከብ የሌለው ምን አልባትም የአንበሳ አርማ ያለበት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ነው ይላል። ከኒዚህ ውጭ ያለ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሰንደቅ አላማየ ፖለቲክ ድርጅት እንደ አርማ እየተጠቀመበት ያለ ምስል ነው ይላል። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ግጭቶች እየተከሰቱ የሰው ህይወት ሲቀጠፍና ንብረት ሲወድም ይታያል። አሁንም ቢሆን በሰንደቅ አላማ ጉዳይ ላይ ሃገራዊ መግባባት እስካልተፈጠረ ድረስ የግጭትና የብጥብጥ መነሻ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ስለሆነም ችግሩን ለመፍታት ህዝቡ የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለት በግልፅ፣ በነፃና በቅንነት ውይይትና ክርክር አድርጎ የሚፈልገውን በአብላጫ ድምፅ እንዲወስን ሊደርገ ይገባል።
ሶስተኛው ጉዳይ የፌደራል መንግስትን የስራ ቋንቋ በሚመለከት እየተነሳ ያለው አተካሮ ነው። እንደሚታወቀው የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አማርኛ ባብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለሚነገር የፌዴራል የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል ህገመንግስታዊ እውቅና አግኝቷል። አንዳንዶቹ ይህ ሁኔታ ባይዋጥላቸውም ከእውነታ ጋ መጋጨት ሆኖ ስለሚታያቸው ተቃውሟቸው ያን ያህል የከረረ አይደለም። ይልቁንም በዚህ ረገድ እየተነሳ ያለው ዋናው ጉዳይ ተጨማሪ የፌዴራል መንግስት ቋንቋ እንዲኖር የማድረግ ፍላጎት ነው። በኔ እይታ መነሻው ምንም ይሁን ምን አንድን ቋንቋ ተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን የሚቀርብ ጥያቄ በራሱ ችግር የለውም። ምን አልባት የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋዎች መብዛት የህዝብ ለህዝብ መቀራረብን የማጎልበት አስተዋፅዖ ሊኖራቸው ይሆን እንደሆነ እንጅ ጉዳት ሊኖረው አይችልም። ከዚህ አንፃር ሲታይ ኢኮኖሚያዊና ነባራዊ ሁኔታው እስከፈቀደ ድረስ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፌዴራል የስራ ቋንቋዎች ቢኖሩ ምናልባትም ተመራጭ ሊሆን ይችላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እጅግ በጣም አፅንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ግን አለ። ይህም ሊጨመር የታሰበው ቋንቋ በህግ ሊጫን የማይገባው መሆኑ ነው። “ዘመኑ የኛ ነው” ከሚል የተዛባ ግንዛቤ ተነስቶ ቋንቋን በህግ ብቻ ሌላው ላይ ለመጫን መሞከር በማንኛውም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊ አይሆንም ብቻ ሳይሆን የሃገርን ህልውና ጭምር አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አምባገነናዊ አካሄድ ነው። ይልቁንም መሆን ያለበት ልክ እንደሰንደቅ አላማው ሁሉ የሚቀርቡ የፌደራል የስራ ቋንቋ ልሁን ጥያቄዎች ወደህዝቡ ቀርበው ነጻና ግልፅ ውይይት/ክርክር ተደርጎባቸው በአብላጫ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ እልባት እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
አራተኛው መሰረታዊ ቁምነገር የመገንጠል መብትን ጨምሮ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀሩን በተመለከተ የሚነሳው ክርክር ነው። በዚህ ዙሪያ ሁለት ፅንፍ ላይ ያሉ ጎራዎች አሉ። አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ወደ አሃዳዊ የመንግስት ስርዓት መመለስ አለባት የሚል ክርክር ያነሳሉ። ይህን ሃሳብ የሚያቀነቅኑ ሃይሎች መገንጠል የሚል መብትን በፍፁም አይቀበሉም። በዚህ ጎራ የሚካተቱ ሃይሎች የኢትዮጵያ የወሰን አከላለል መልክዓ ምድርን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን አለበት ይላሉ። በሌላኛው ጎራ ያሉት ደግሞ አሁን ያለው አወቃቀር የመገንጠል መብትን ጨምሮ እንዳለ መቀጠል አለበት የሚሉ ናቸው። ችግሩ ያለው እነዚህ የተለያዩ ሃሳቦችና ፍላጎቶች መንፀባረቃቸው ላይ አይደለም። እንዲያውም ሰው የሚሰማውን መግለፁ የሚበረታታና ዴሞክራሲን የሚያጠናክር ሂደት ነው። ይህ ሂደት ችግር መሆን የሚጀምረው አንዱ ወይም ሌላው የኔ ፍላጎትና ሃሳብ ብቻ ነው እንከን የሌለበት ብሎ ይህንኑ ፍላጎትና ሃሳብ በሌላው ላይ በሃይል ለመጫን እንቅስቃሴ የሚጀምር ከሆነ ነው። በዚህም አለ በዚያ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀሩ የመገንጠል መብትን ጨምሮ በዚህ ደረጃ የሚያከራኪር ከሆነ መፍትሄ የሚሆነው አሁንም ከላይ እንደተገለፀው ሁሉ ህዝቡ ያልተገደበ ነፃና ግልፅ የሆነ ውይይት እንዲያደርግባቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ለነገ የማይባል ስራ ተደርጎ መወሰድ አለበት። ውይይቱና ክርክሩ በነፃና በግልፅ ከተካሄደ በኋላ የትኛው አወቃቀር እና በምን አኳኋን የሚለውን ጉዳይ ህዝቡ ደሞክራሲያዊ በሆነ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በአብላጫ ድምፅ እንዲወስን ማድረግ ይጠይቃል።
ይሁንና ከላይ የተነሱትን አራት መሰረታዊ ችግሮች በሚገባ ለመፈተሽና በተጓዳኝ የተቀመጡትን መፍትሄዎችም በትክለኛ መንገድ ገቢራዊ ለማድረግ የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት ይኖርባቸዋል። አንደኛው ቅድመ ሁኔታ ኢህአዴግ በውስጡ ያለውን በግልፅ የሚታይ መሻኮት፣ ትርምስ፣ አለመተማመንና ግልፀኝነት መጓደል አስወግዶ አንድነቱን አጠናክሮ መገኘት ይኖርበታል። ምክንያቱም የራሱን አባል ድርጅቶች ማቀራረብና መተማመን እንዲችሉ ያላደረገ ኢህአዴግ ህዝቡን ከዳር እስከዳር አቀራርቦ ከላይ በተነሱ መሰረታዊ ችግሮች ዙሪያ ቅን የሆነ ውይይት እንዲኖርና እንዲሁም የተቅመጡት የመፍትሄ ሃሳቦች በሚገባ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው።
ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ በህዝቡ ውስጥ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ነፃ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃሳብ የማራመድና የመሰለውን አቋም የመያዝ መብቱ ሊከበርለትና ሊጠበቅለት ይገባል ማለት ነው። ማንም ሰው ሃሳብ በማራመዱና አቋም በመውሰዱ ምክንያት ሊሸማቀቅ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ሊደርስበትና ሊታሰርም አይገባውም። በተጨማሪም ማንም ሰው የህዝብ ውሳኔ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊትም ይሁን ድምፅ በሚሰጥጥበት ጊዜ ወይም ከዚያ በኋላ ምንም አይነት ትፅዕኖ እንዳያርፈበት አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ የነፃ ሃሳብ ዝውውርን ለማጎልበት እጅግ በጣም ጠቃሚ ርምጃ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ ደግሞ ስርዓት እንዲበጅላቸው ማድረግ ያስፈልጋል።
ሶስተኛው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ረፖርቶችና ግብረ መልሶች እውነተኛ መሆን የሚኖርባቸው መሆኑ ነው። ከአሁን ቀደም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኢህአዴግ ሰዎች የሚታወቁት የውሸት ረፖርትና ግብረ መልስ በመፈብረክ ነው። ይህ ደግሞ ኢህአዴግንም ሆነ እመራዋለሁ የሚለውን ቀና ህዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ስለዚህ በማንኛውም ውይይትና ክርክር ላይ የሚነሱ ሃሳቦችና የሚያዙ አቋሞችን የተመለከቱ ረፖርቶችና ግብረ መልሶች ወደሚመለከተው አካል ሲተላለፉ ምንም አይነት ውሸት ሳይጨመር ሳይቀነስ መሆኑ መረግገጥ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከልና ለማረም ይረዳ ዘንድ የሪፖርቶችንና ግብረመልሶችን እውነተኛነት እውን ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ይሆናል።
በሌላ በኩል ከላይ በተገለፀው መሰረት ህዝባዊ ውይይቶች፣ ክርክሮችና የድምፅ አሰጣጥ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜ የሚከተሉት ነጥቦች ተግባራዊ ቢሆኑ ሂደቱን የበለጠ ዴሞክራሲያዊና ታማኝ ሊያደርጉት ይችላሉ። እነዚህም፦
ሁሉም ህዝብ በጉዳዮቹ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉ መረጋገጥ ይኖርበታል። ውይይቱ ደግሞ እንደተለመደው ለይስሙላ ሳይሆን ጥልቅና ነፃ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፤
ሁሉም መገናኛ ብዙሃን ህዝቡ በውይይቱና ክርክሩ ላይ እንዲሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንዲችሉ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል፤ ዘገባዎቻቸውና ትንታኔዎቻቸውም ህዝቡ ሁኔታውን በተገቢው መንገድ እንዲረዳው የሚያደርግ አቅጣጫን ቢከተሉ ሂደቱን ውጤታማ እንደሚያደርገው ተገንዝበው ለዚሁ ቀና የሆነ እገዛ ቢያደርጉ ይመረጣል፤
የፖለቲካ ፓርቲዎችም አንዱን ወይም ሌላውን ሃሳብ ደግፈው ወይም ተቃውመው የመሰላቸውን ሃሳብ እንዲያራምዱና ለህዝቡም ይህን ሃሳባቸውን ያለምንም ገደብ በነፃ እንዲገልፁ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል።
በተጨማሪም ገለልተኛ የሆኑ ታዛቢዎች እንዲኖሩ ማድረግም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ መፍትሄ ያልተሰጠውና እግረ መንገዴን ላነሳው የፈለኩት መሰረታዊ ችግር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋ እየተቆራኙ የሚነሱ የንግድ ድርጅቶችን (Endowments) የሚመለከተው ጉዳይ ነው። እነዚህ ድርጅቶች በተለይም ኤፈርት አብዛኛው የመነሻ ካፒታሉ የተገኘው የህወሓት አመራሮች እንደሚሉት ውጭ አገራት ከነበሩ የህወሓት ንብረቶች ሽያጭና ከአባላት መዋጮ አልነበረም። በወቅቱ የሆነው ነገር አንድ ከተማ ወይም ቦታ ከደርግ ይዞታ ነፃ ሲወጣ በአካባቢው ከሚገኙ ባንኮች፣ የህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎች ህዝባዊ ተቋማት የሚዘረፍ ንብረትና ገንዘብ በጆንያ እየተሞላ ለኢህአዴግ ፋይናንስ ገቢ ይደረጋል። በየቦታው የነበሩ የኢህአዴግ ፋይናንስ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ደግሞ በአብዛኛው የህወሓት አባላት ነበሩ። እነዚህ የህወሓት ሰዎች ገንዘቡን ይሰበስቡና የሚልኩት ትግራይ ውስጥ ወደሚገኘው ማዕከላቸው ነበር። ይህ ገንዘብና ንብረት ነው እንግዲህ ተጠራቅሞ የኤፈርት ማቋቋሚያ መነሻ ካፒታል የሆነው። ከዚህ ስንነሳ ኤፈርት እንደመነሻ የተጠቀመበት ጠርቀም ያለ ገንዘብና ንብረት የተገኘው ከመላው ኢትዮጵያ ኪስ ውስጥ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም።
የዚህ ከኢትዮጵያ ህዝብ ኪስ በተዘረፈ ገንዘብ የተቋቋመ ድርጅት አላማ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሞኖፖል መቆጣጠር ነበር። ይህን ለማስፈፀም በየቦታው ተሰግስገው የነበሩ የህወሓት አመራሮችና አባላት ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። በዚህም መሰረት በኤፈርት ስር ያሉ ድርጅቶች ንግዱን ያለምንም ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዳሻቸው ሲፈነጩበት እንደነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሰወረ ምስጢር አይደለም። አንዳንድ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ሊኖሩ ቢችሉም እንኳን የነበረው አሰራር ለኤፈርት ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ስለነበር እነዚህ ድርጅቶች የሚፈልጉት የንግድ እንቅስቃሴ ከሆነ ለሌላ አሳልፎ መስጠት አይታሰብም። በሌላ በኩል የኤፈርት ድርጅቶችን የሚጠቀምባቸው ቡድን ሌላ የነዚህ ድርጅቶች ሸቀጥ ማራገፊያ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሌላ ሆኖ መቆየቱ ገሃድ የወጣ ምስጢር እንደነበር መካድ አይቻልም። ይህ በመሆኑ ምክንያት በሃገሪቱ የነበረው የተጠቃሚነት ሚዛን ወደ አንድ ቡድን ያጋደለ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ ሆኖ የሚታየኝ ሁሉንም ድርጅቶች (Endowmments) አፍርሶ አንድ ላይ በማምጣት በፌዴራል ደረጃ አንድ የልማት ድርጅት እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው። የዚህ በፌዴራል ደረጃ የሚቋቋም የልማት ድርጅት አላማ ደግሞ ፍትሃዊ የሆነ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የፌዴራል አወቃቀሩን ሂደት ሊያጠናክር በሚችል መንገድ መሆን ይኖርበታል።
ቸር እንሰንብት!!!
