ሐራ ዘተዋሕዶ
January 17, 2019t

- በሁከት ፈጣሪነት በተሰናበቱ አራት መነኰሳት ላይ የተወሰደውን ርምጃ ያጣራል፤
- የተባረሩት መነኰሳት ውሳኔውን በመቃወም ለቅ/ፓትርያርኩ አቤቱታ አቅርበዋል፤
- “በፖለቲከኞች ምክርና በሊቀ ጳጳሱ ወገንተኝነት የተላለፈ ውሳኔ ነው፤”/የተባረሩት/
- “ከኮፕቶች ፈተና ለይተን በማናየው ዐመፀኝነት ገጽታችንን አበላሽተዋል፤”/ገዳሙ/
***
በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን በአድማና በፀብ እያወኩ ሊቀ ጳጳሱንና አበው መነኰሳትን በመደብደብ ጉዳት ባደረሱ አራት መነኰሳት ላይ የተወሰደውን ከአገልግሎትና ከአንድነት የማሰናበት ርምጃ የሚመረምር የቋሚ ሲኖዶስ ልኡክ ዛሬ ማምሻውን ወደ እስራኤል ያመራል፡፡
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ረዳት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ መልአከ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስ በአባልነት የሚገኙበት የቋሚ ሲኖዶሱ አጣሪ ልኡክ፣ የገዳሙን ውሳኔና አራቱ መነኰሳት ያቀረቡትን አቤቱታ በጋራ በመመርመር ለማኅበሩ አንድነትና ለገዳማቱ አገልግሎት መቃናት የሚበጅ ዘላቂ መፍትሔ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ባለፈው ታኅሣሥ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ቄሰ ገበዝ ለመምረጥ በተደረገው የገዳማቱ አጠቃላይ ስብሰባ ላይ፣ እኛ ያልነው ካልኾነ በማለት ፀብና ሁከት አነሣስተው በአንድ መነኰስ ላይ በፈጸሙት ድብደባ ጉዳት ያደረሱትና ሊቀ ጳጳሱን ያንገላቱት ቄሰ ገበዙ አባ ወልደ ሩፋኤል ገብረ ጻድቅ እና አባ ገብረ እግዚአብሔር ተስፋይ ከአበሮቻቸው አባ ተስፋ ማርያም ይኅደጎ እና አባ ኀይለ ገብርኤል ሞላልኝ ጋራ ከገዳሙ አገልጋይነትና ከማኅበረ መነኰሳቱ አንድነት እንዲሰናበቱ፣ ምልዓተ ማኅበሩ፣ በማግሥቱ ታኅሣሥ 10 ቀን ባካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
አራቱ መነኰሳት በበኩላቸው፣ ርምጃውን ተቃውመው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፉት አቤቱታ፣ ውሳኔው፣ በውጭ ፖሊቲከኞች ጣልቃ ገብነትና በጎሠኝነት አድልዎ(በወገንተኝነት) የተላለፈ ነው፤ በሚል ድርጊቱን መፈጸማቸውን ክደዋል፡፡ “ሊቀ ጳጳሱ የውጭ ፖሊቲከኞችን ምክር እየሰሙ ማኅበሩ ሰላም እንዲያጣ እርስ በርስ እያደባደቡት ነው፤ በቀዬአቸው ከተወለዱ መነኰሳት ጋራ በመኾን ማኅበር በሌለበት እየሾሙና እየሻሩ ሕግና ደንብ ያፈርሳሉ፤ ዘመዶቻቸውን ብቻ በማቅረብ የገዳሙን ንብረት ለመቆጣጠር ይሞክራሉ፤” በማለት ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምን ከሠዋል፡፡ በማኅበሩ የተፈጠረው መከፋፈል ወደ ሕዝብ እንደወረደና ይህም እርስ በርስ እንዳያበጣብጥ ስለሚያሰጋ በቅዱስነታቸው እና በቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ተሰጥቶት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ታኅሣሥ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥር 111/2011 በገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ተፈርሞ በየስማቸው የተጻፈላቸው የአጠቃላይ ስብሰባው ውሳኔ እንደሚያመለክተው፣ከአራቱ መነኰሳት መካከል ፀብና ሁከት በመቀስቀስ በቀዳሚነት የተጠቀሰው አባ ተስፋ ማርያም ይኅደጎ፣ ታኅሣሥ 9 ቀን በተደረገው የምልዓተ ማኅበር ስብሰባ፣ ገና በአጀንዳው መጀመሪያ እኔ ቀድሜ ካልተናገርኩ በማለት ስብሰባውን ረግጦ ወጥቷል፡፡ በጉባኤው ሰብሳቢና በአዛውንት አባቶች ተለምኖ ተመልሶ ቢቀመጥም ይብሱኑ በፀብ አጫሪነት ከባድ ብጥብጥ በመፍጠር በአባቶች ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ አጀንዳውም እንዳይቋጭ ምክንያት ኾኗል፡፡ በስብሰባው ዕለት ብቻ ሳይኾን በየጊዜው ለገዳሙ ሥርዐት ባለመገዛት በሚፈጥረው ልዩ ልዩ ችግር መላ ማኅበሩን ሲያውክ እንደቆየ በገዳሙ መዝገብ ቤት የሚገኘው የግል ማኅደሩ ስለሚያሳይ ከአገልጋይነትና አባልነት እንዲሰናበት ተወስኖበታል፡፡

አባ ገብረ እግዚአብሔር ተስፋይን በተመለከተ፣ አበ ማኅበሩን(ሊቀ ጳጳሱን) በማኅበረ መነኰሳቱ ፊት፣ መነኰሳቱን በሊቀ ጳጳሱ(አበ ማኅበሩ) ፊት በመደብደብ፣ መነኩሴ ነኝ ከሚል አባት የማይጠበቅ፣ የሲናይ በረሓን አቋርጦ ወደ እስራኤል በስደት ቢመጣም ገዳሙ በፍቅር ሲቀበለው የገባውን ቃል ኪዳን የሻረ፣ ማኅበሩ በወንድምነት የዋለለትን ውለታ የዘነጋ፣ አባቶችንና መላውን ምእመን ያሳዘነ፣ የገዳሙንም ታሪክ ያጨለመ አሳፋሪ ድርጊት መፈጸሙን የአጠቃላይ ስብሰባው ውሳኔ አትቷል፡፡ ይህ ድርጊቱ በቀላሉ ቢታለፍ ነገ በገዳሙ ላይ የከፋ ጉዳት ሊፈጸም ስለሚችል በእጁ የሚገኘውን የገዳሙን ንብረትና የቤቱን ቁልፍ አስረክቦ እንዲወጣ ተወስኖበታል፡፡

አባ ወልደ ሩፋኤል ገብረ ጻድቅም፣ ከአባ ገብረ እግዚአብሔር ተስፋይ ጋራ በመኾን በአንድ መነኰስ ላይ ኢሰብአዊ የኾነ የድብደባ ተግባር እንደ ፈጸመ የአጠቃላይ ስብሰባው ውሳኔ አስታውቋል፡፡ ከዚህም በላይ፣ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በኢያሪኮ ገዳም ቅዳሴ ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ባለመቀበል ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ንቋል፤ አቃሏል፡፡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ለገዳማቱ ሕግና ሥርዐት አልታዘዝም፤ የበላይ አካል መመሪያን አልቀበልም፤ እያለ በራሱ ፈቃድና ሐሳብ ብቻ እየተሰማራ ፀብና ሁከት እያስነሣ የቆየ በመኾኑ በእጁ የሚገኘውን የገዳሙን ንብረት አስረክቦ እንዲወጣ ተወስኖበታል፡፡

ቄሰ ገበዝ ለመምረጥ ታኅሣሥ 9 ቀን በተካሔደው የምልዓተ ማኅበር ስብሰባ በመጀመሪያ በአድመኝነት በመሳተፍና ለበላይ አካል ታዛዥ ባለመኾን ጭምር በዋናነት ከተጠቀሱት ውስጥ አባ ኀይለ ገብርኤል ሞላልኝ ይገኝበታል፡፡ በፀቡ ወቅት አንድ አረጋዊ መነኰስን ለመደብደብ ከመጋበዙም በላይ ችግሩን ለማብረድ በመጣው ፖሊስም ሲናደድ መስተዋሉን ውሳኔው አስፍሯል፡፡ ወደ ገዳሙ የተላከበትን ዓላማ በመዘንጋት በአሳፋሪ ተግባር ላይ ተሳታፊ በመኾኑ፣ ታኅሣሥ 10 ቀን የተደረገው ጠቅላላ ስብሰባ፣ ከገዳሙ እንዲሰናበት ተወስኖበታል፡፡

የተፈጠረውን ችግር፣ “በገዳማችን ላይ ያንዣበበ የዘመኑ አደገኛ ፈተና” በማለት የገለጸው የማኅበሩ ጠቅላላ ስብሰባ፣ ኮፕቶች ከሚያመጡብን ፈተና ተለይቶ የማይታይና የገዳሙንም ገጽታ የሚያበላሽ እንደኾነ ገልጾ፣ በስም ተጠቃሾቹ የድርጊቱ መሪና ፈጻሚ መነኰሳት ላይ የወሰደውን ርምጃ አስፈላጊነትና አግባብነት አስረድቷል፡፡
