January 18, 2019

ጎንደር !

ጎንደር

ጎንደር

January 18, 2019
የዐፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ (ታደሰ ጥበቡ)
“ጎንደር”ማለት “ጉንደ ሀገር”ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም “የሃገር ግንድ፣የሀገር መሰረት፣ርዕሰ ሃገር ወይም የሀገር ራስ ማለት ነው።
ይኸውም ኖህ ከጥፋት ውሐ በኋላ የተቀመጠበት በእንተላ፣በአይዋርካ፣በሽሌ፣በአይከል፣በኩል አድርጎ ጎንደር ላይ ብዙ ዘመን ፈጣሪውን እያመሰገነ እየቀደሰ የኖረባትና የተቀበረባት ቦታ በመሇኗ የሃገር መጀመሪያ ዋና ግንድ ተባለች።
እንዲያውም በ950 ዓ.ዓ ኖህ ሲሞት መቃብሩ ላይ ምንጭ ፈልቆ በርካታ ሰዎችን ይፈውስ ነበር።ከዚያም ለኖህ መታሠቢያ ይሆን ዘንድ አምላክ በቤተመንግስት አሳቦ የኖህ የመቃብር ሐውልት እንዲታነጽ ፈቀደ።ይህም በኋለኛው ዘመን በንጉሥ ፋሲለደስ የታነጸው የፋሲል ግንብ ነው።
አጼ ፋሲለደስም በ1629 ዓ.ም በመሀንዲስ አባ ገብረክርስቶስ መሪነት የእደ ጥበብ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ከኖህ መቃብር ላይ የቤተመንግሥቱን ታላቅ መሰረት ጥለውታል።ግንባታውም በ7 አመት ውስጥ ተጠናቀቀ።
ከዚህ በኋላ አጼ ፋሲል በቀሐ ወንዝ አጠገብ “ማንኪት”የሚባለውን ህንጻ በ17ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ግቢ መሀል ላይ 50 ሜትር በ25 ሜትር ስፋትና 2 ሜትር ጥልቀት ያለው መዋኛ ገንዳ አስገነቡ፡፡
አጼ ፋሲል መዋኛ ገንዳውን ከአሰሩት በኋላ ከቀሃ ወንዝ በተቆፈረ ቦይ ውሐ ተጠልፎ እንዲገባ አደረጉ።ልጆችም በአየር በተነፋ አቅማዳ እየተንሳፈፉ ዋና ይማሩበትና በጥምቀት በዓል ለመጠመቂያነት ያገለግል ነበር።ውሃው አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በተዘጋጀለት ቦይ ተመልሶ ይፈሳል።
ከመዋኛው በቅርብ ርቀት በስተምስራቅ በኩል በክብ ቅርጽ በግምብ በተሰራ የአጼ ፋሲለደስ ፈረስ የነበረው የዞብል መቃብር ጨምሮ 6 የእንቁላል ግንቦች እና የቤተ-ክርስቲያን ፍርስራሾች ይገኛሉ።
ዛሬ ላይ አጼ ፋሲል ባሰሩት አንድ ፎቅ ጥንታዊ ህንፃ ጥምቀት ሲመጣ የታቦታቱ ማደሪያ ሆኖ ያገለግላል።መዋኛ ገንዳው በባእሉ ሰሞን የባንዲራ መቀነት ይታጠቃል፡፡
በጎንደር ወደ ጥምቀተ ባሕሩ የሚወርዱ ታቦታት፡-
1.ቀሃ ኢየሱስ እና እልፍኝ ጊዮርጊስ
2.ቅዱስ ፋሲለደስ እና አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል
3.መጥምቁ ዮሐንስ እና ፊት ሚካኤል
4.መ/መ/መድኃኒዓለም እና አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት
5.በዓታ ለማርያም እና
6.ልደታ ለማርያም ከፀበል ቦታቸው ወርደው ይገባሉ፡፡
በተጨማሪም፦
7.አቡነ ሐራ ድንግል ወሩፋኤል ደግሞ ከቅጽሩ ተከብሮ ዙሮ ይገባል፡፡
አዘዞ ላይ ደግሞ
8.አባ ሳሙኤል ቅዱስ ሚካኤል
9.አዘዞ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል
10.አዘዞ ተክለ ሃይማኖት
11.አይራ ቅዱስ ሚካኤል ይወርዳሉ፡፡
አጼ ፋሲል የአጼ ሱስኒዮስ እና የወልደ ሰዓላ ልጅ ናቸው።በጣና ሐይቅ ደቅ ደሴት ዳጋ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ትምህርት እየተማሩ ያደጉ ሲሆን የአባታቸውን ዙፋን ተረክበው የነገሱት በ1624 ዓ.ም ነው።ስመ መንግሥታቸው “ሥልጣን ሰገድ”ይባላል።ትርጓሜው ዓለም የሰገደልህ ማለት ነው።
ማጣቃሻ ====
1.የጎንደር ታሪክ-ያሬድ ግርማ ሀይሌ 1999 ዓ.ም
2.መፅሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ-በአለቃ ኪ/ወልድ
3.የኢትዮጵያ የ5ሺህ ዓመት ታሪክ-ፍስሐ ያዜ 2003 ዓ.ም
4.የዓለም ታሪክ -አቶ ዮሐንስ ወልደ ማርያም 1936 ዓ.ም
5.ስለ ቅዱሳት መጻህፍትና ሳንስ ስምምነት-ዶ/ር ሄሪ ሪመር-ትርጉም በጎበዜ ጣፈጠ 1953 ዓ.ም


