January 22, 2019 t

- የግዛቲቱ ካህናትና ምእመናን፣ ከጥቅምቱ ምደባ በፊትና በኋላ አቤቱታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፤
- እመቤታችንን ከሚነቅፉና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከሚያቃልሉትጋ ግዴለሽና ተባባሪ ኾነዋል፤
- በቅዳሴ መካከል የጳጳሱንና የደጋፊዎቻቸውን ጭፈራ የሚያሳይ ቪዲዮ በማስረጃነት ተካቷል፤
- ከደጋፊቻቸው ጋራ ምእመኑን እየከፋፈሉ ባነፀው ቤተ ክርስቲያን እንዳይገለገል አውከውታል፤
***
- ችግሩ ከአትላንታ ጆርጂያ አልፎ በአምስት ግዛቶች አብያተ ክርስቲያንም ዘንድ ተስፋፍቷል፤
- ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በእውነት የሚጠብቅ ርቱዕ አባት እንዲመድብ ካህናቱና ምእመናኑ ጠይቀዋል፤
- በአ/አበባ የሚገኙት ሊቀ ጳጳሱ፣“በአንድ ወገን አቤቱታ የተላለፈ ነው፤” በሚል ተቃውመዋል፤
- በኑፋቄው አራማጅነት የሚጠረጠሩ ሌሎች ጳጳሳትም ጉዳይ ክትትልና እርምት ያስፈልገዋል፤
***
በሰሜን አሜሪካ የጆርጂያ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ የእምነት አቋማቸውን በተመለከተ ከካህናትና ምእመናን በተደጋጋሚ በቀረበባቸው አቤቱታ፣ ከአትላንታ ጆርጂያ ግዛት ከሚገኙ አድባራት እስከ መጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ድረስ ታግደው እንዲቆዩ ቋሚ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ የአትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ቦርድ አገልጋይ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን አስተባባሪ ግብረ ኃይል ተወካዮች በማስረጃ አስደግፈው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ በመወያየት፣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ በሌሎች የሀገረ ስብከቱ ግዛቶች(ቴነሲ፣ ሰሜንና ደቡብ ካሮላይና፣ አላባማ፣ ፍሎሪዳ እና ሚሲሲፒ) ብቻ ተወስነው አገልግሎት እየሰጡ እንዲቆዩ በማዘዝ ከአትላንት ጆርጂያ ግዛት አድባራት አግዷቸዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ያዕቆብ ከአትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ካህናትና ምእመናን ጋራ በእምነት አቋማቸውና በሌሎችም ምክንያቶች የፈጠሩት አለመግባባት ኹለት ዓመት ያህል እንዳስቆጠረ በአቤቱታው ተጠቅሷል፡፡ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሊቀ ጳጳሱን ከመመደቡ በፊት ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ከተመደቡም በኋላ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጽሑፍ እና በቃል በተደጋጋሚ ያቀረቡት አቤቱታ አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ አለመግባባቱ ተባብሶ ለካህናትና ምእመናን መከፋፈል ምክንያት ከመኾኑም በላይ፣ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት አምርቶ ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በፍ/ቤት የሚታወቀው የካቴድራሉ ቦርድ አገልጋይ ካህናትና የማኅበረ ምእመናን አስተባባሪ ግብረ ኃይል በተወካዮቹ አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶሱ ባቀረበው አቤቱታ እንዳስረዳው፣ ከኹለት ዓመታት በፊት ለካቴድራሉ አዲስ ሰበካ ጉባኤ ለመምረጥ በነበረው ጥቆማ አጋጣሚ አለመግባባቱ አስከፊ ገጽታ ይዟል፡፡ ይህንም ለመፍታት ጠቅላላ ጉባኤው ተጠርቶ በተሠየመ ኮሚቴ አማካይነት በተካሔደው ማጣራት፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ እና አቡነ ያዕቆብ የአለመግባባቱ ዋና ምክንያትና ጥፋተኞች መኾናቸው ተረጋግጧል፤ ሰበካ ጉባኤውም በሪፖርቱ ላይ ተመሥርቶ በአብላጫ ድምፅ ባሳለፈው ውሳኔ፣ አስተዳዳሪውም ሊቀ ጳጳሱም “ከአገልግሎቱ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡” ሰበካ ጉባኤው(ቦርዱ) በጠቅላላ 22 አባላት ያሉት ሲኾን፣ ከ16 የማያንሱት ብዙኀኑ አባላት እርሳቸውን የሚቃወሙ እንደኾኑ ተመልክቷል፡፡
ውሳኔው ግን ተግባራዊ እንዳይኾን የሊቀ ጳጳሱ ደጋፊዎች ሥርዐተ ቅዳሴን በማስተጓጎል ጭምር ሁከት እየፈጠሩ በፈጸሙት “ፀረ ሃይማኖት ድርጊት” ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት አምርቶ፣ “አባ ያዕቆብ እና ተከታዮቻቸው በየ15 ቀን ለ6 ሰዓት ብቻ ገብተው እንዲጸልዩ ሲፈቅድ፣ ምእመኑ በየ15 ቀኑ እየመጣ መገልገል ከጀመረ ኹለት ዓመታት ተቆጥሯል፤ ወጪያችንም ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፤” ይላል አቤቱታው፡፡
ይህም ሁሉ ኾኖ፣ ከሲኖዶሳዊው አንድነት መመለስ በኋላ በጥቅምት 2011 ዓ.ም. በተካሔደው የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ፣ አቡነ ያዕቆብ በሊቀ ጳጳስነት በመመደባቸው ምእመናን ብዙ ዋጋ ከፍለው ባሳነፁት ቤተ ክርስቲያን በየሳምንቱ ሥርዓተ እምነታቸውን በሰላም ለመፈጸም ከመቸገራቸውም በላይ የካቴድራሉ ወጪ ከተጠቀሰውም በላይ እየናረ መሔዱን አስረድቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ችግሩ፣ ከአትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል እና ከጆርጂያ ግዛት አብያተ ክርስቲያን አልፎ ወደ ሌሎች አምስት ግዛቶች መስፋፋቱን ጠቁሟል፡፡
ለተደጋጋሚ አቤቱታቸው ምላሽና መፍትሔ ባልተሰጠበት ኹኔታ፣ አቡነ ያዕቆብ በማይቀበሏቸው አድባራትና ምእመናን ላይ ሊቀ ጳጳስነት የተመደቡበት ምክንያት ግርታ እንደፈጠረባቸው ተወካዮቹ ለቋሚ ሲኖዶሱ የተናገሩት በከፍተኛ ምሬት ነው፡፡ አቡነ ያዕቆብ በተቀመጡበት፣ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን በመምህርነት ስም እየተጋበዙ ኑፋቄያቸውን እንዳስፋፉ የሚገልጹ የካህናትን፣ የምእመናንንና የሰበካ ጉባኤውን ማስረጃዎች አብራርተዋል፤ በተለይም በጸሎተ ቅዳሴ መካከል በሊቀ ጳጳሱ መሪነት የተደረገ ጭፈራን ያሳያል ያሉትን ቪዲዮ ባቀረቡበት ወቅት ቅዱስ ፓትርያርኩና የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በከፍተኛ ኀዘን ተውጠው ተስተውለዋል፤ ይህን ተከትሎም የእገዳውን ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙት ሊቀ ጳጳሱ፣ ከአንድ ወገን የቀረበን አቤቱታ ብቻ በመስማት የተላለፈ እገዳ ነው፤ በሚል የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተቃውመው ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለቅዱስ ፓትርያርኩ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ጆርጂያን እንደ መንበረ ጵጵስና የሚቀመጡበት በመኾኑ፣ “ከአትላንታ ከታገድኩ ምን ሀገረ ስብከት አለኝ፤” በሚል አቋም ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
“በእምነት ድርድር አያስፈልግም፤ ጉዳዩ ከአስተዳደርም በላይ ሃይማኖታዊ በመኾኑ ከመባባሱ በፊት ታግደው መቆየታቸው አግባብነት አለው፤” በማለት የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የደገፉት ካህናትና ምእመናን፣ አቡነ ያዕቆብ ከአባትነታቸው ጋራ የማይስማማ የግትርነት ጠባይዕ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፤ ከዕቅበተ እምነት አንጻር ስላለባቸው ድክመት ሲያስረዱም፣ በተቀመጡበት እመቤታችን ስትነቀፍ የሚከላከሉት ነገር የላቸውም፤ ቤተ ክርስቲያን አማናዊ የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም አድርጋ የምትፈተትበት የምሥጢረ ቁርባን አፈጻጸም በፕሮቴስታንታዊ ልማድ ሲቃለል ከማረም ይልቅ ተባባሪ በመኾን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ጥሰዋል፤ በማለት ይተቿቸዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ካህናቱንና ምእመናኑን በእውነት የሚመራ ኖላዊ አባት በአስቸኳይ እንዲመድብላቸው ያመለከቱት የካቴድራሉ ሕጋዊ አስተባባሪ ግብረ ኃይል ተወካዮች፣ “ይህም እስኪፈጸም ድረስ ምእመኑን ከመበተን እንዲጠብቅልን በጸሎት እንድታግዙን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፤” በማለት ተማፅነዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ የተዋሐደ ቁመና፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አንድነት በማረጋገጥ ለዓለም አቀፋዊ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ኦርቶዶክሳውያንን ኹሉ ያስደሰተ ሲኾን፣ ከቀድሞም ጀምሮ በእምነት አቋማቸው የሚጠረጠሩት መስለው/ሾልከው የገቡበትና መሣሪያቸውም ያደረጉት በመኾኑ፣ እንቅስቃሴያቸው፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጥብቅ ክትትልና ወቅታዊ እርምት እንደሚያስፈልገው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዕለት ዕለት በሚያሳስባቸው በርካታ ካህናትና ምእመናን እየተጠየቀ ይገኛል – “በአባቶች ዕርቀ ሰላም የተመለሰው ሲኖዶሳዊ አንድነት፣ የአንዳንድ አባላቱን ሃይማኖታዊ አቋም በመመርመርና በማጥራት ይበልጥ ሊረጋገጥና ሊጠናከር ያስፈልጋል፤” ይላሉ ወትዋቾቹ፡፡
