January 24, 2019
በአማራ ሚዲያ ምስረታ ጉዳይ በተፈጠረው አለመግባባት ላይ በተደረገ ውይይት የሽማግሌዎች ሪፖርት

በምሥረታ ላይ በሚገኘው የአማራ ሚዲያ ጉዳይ በመስራች ኮሚቴው እና በአቶ ሙሉቀን ተስፋው መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በተመለከተ ጥር 03/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ውይይት ተደርጓል፡፡ ውይይቱ ከቀኑ 8፡00-12፡00 የተደረገ ሲሆን፣ የውይይቱ አጠቃላይ ውጤት/ስምምነት በሽማግሌዎች በኩል እንዲገለጽ ሁለቱም ወገኖች በተስማሙት መሠረት ይህንኑ ለህዝብ ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
በውይይቱ የተገኙ ሰዎች፡-
- አቶ በሪሁን አዳነ ፡- ከመስራች ኮሚቴው
- አቶ ጌታቸው ሺፈራው ፡- ከመስራች ኮሚቴው
- አቶ ሙሉቀን ተስፋው ፡- በግል
ሽማግሌዎች፡- - አቶ ወንድይራድ ኃ/ገብርኤል (የሚዲያ ምስረታ ሂደቱን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩና እየተከታተሉ የሚገኙ)
- አቶ ማሙሸት አማረ (የሚዲያ ምስረታ ሂደቱን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩና እየተከታተሉ የሚገኙ)
- ወ/ት ወይንሸት ሞላ (በሚዲያ ምስረታው ሂደት ምንም አይነት ተሳትፎና ሚና እንዳልነበራት ቢታወቅም፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋው የሽማግሌዎች አባል እንድትሆን በጠየቀው መሠረት የተካተተች)
- አቶ አበበ ውቤ (የሚዲያ ምስረታ ሂደቱን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩና እየተከታተሉ የሚገኙ)
- አቶ በላይ ማናዬ (የሚዲያ ምስረታ ሂደቱን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩና እየተከታተሉ የሚገኙ)
የተነሱ አጀንዳዎች፡- - በሥራ ላይ ያለውን ኮሚቴ እውቅና አልሰጠውም በሚል በአቶ ሙሉቀን ተስፋው በኩል የተያዘ አጀንዳ
- በኮሚቴው ስም ከህዝብ የተሰበሰበውን ገንዘብ በኮሚቴው ስም በተከፈተው አካውንት አስገባለሁ ብሎ ቃል በገባው መሠረት አቶ ሙሉቀን ተስፋው ገቢ እንዲያደርግ በመሥራች ኮሚቴው (አቶ በሪሁን አዳነ እና አቶ ጌታቸው ሺፈራው) በኩል የተያዘ አጀንዳ
- ሥማችን ጠፍቷል፤ ስለሆነም ይቅርታ ልጠየቅ የሚል በሁለቱም ወገን የተያዘ አጀንዳ
- በሽማግሌዎች በኩል አቶ ሙሉቀን ተስፋው ወደ ኮሚቴው ተመልሶ በጋራ እንዲሰሩ በሚለው ውይይት ተደርጎ ስምምነት ቢደረስ የሚል ሀሳብ ቀርቧል፡፡
በተነሱ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጎ በሁለቱም ወገኖች የተደረሱ ስምምነቶች - አጀንዳ አንድ፡- ይህን አጀንዳ አቶ ሙሉቀን ተስፋው ባስያዘው መሠረት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ አቶ ሙሉቀን በሥራ ላይ የሚገኘውን ኮሚቴ እውቅና አልሰጠውም በሚል መነሻ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ በምስረታ ሂደት ላይ ቀደም ብሎ ባህር ዳር ኮሚቴ ተቋቁሞ የነበር መሆኑን ጠቅሶ፣ ያ ፈርሶ እንደገና አዲስ አበባ ላይ መቋቋሙ ላይ ቅሬታ አቅርቧል፡፡
አቶ በሪሁን እና አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ባህር ዳር ላይ ተመስርቶ የነበረው ኮሚቴ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮችና ፖለቲከኞች ተካትተውበት እንደነበር በማስታወስ፣ ኮሚቴው ከፖለቲካ ድርጅት ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ እንዲቋቋም በማስፈለጉ ፖለቲከኞቹ ወጥተው እንደአዲስ መቋቋሙ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በውይይት የሆነ እንደሆነ ጠቅሰው፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋውም በኮሚቴው ውስጥ ተስማምቶ አብሮ ሲሰራበት የቆየው ኮሚቴ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም፣ ኮሚቴውን እውቅና አልሰጠውም የሚለው የአቶ ሙሉቀን ተስፋው ቅሬታ ትክክል አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በውይይቱ አቶ ሙሉቀን ተስፋው ኮሚቴው ውስጥ ያለአግባብ የተካተቱ ግለሰቦች ስላሉ ሊቀየሩ ይገባል የሚል ሀሳብም አቅርቦ፣ ሽማግሌዎቹ የተነሳው ጉዳይ አቶ ሙሉቀን የኮሚቴው አባል ሆኖ አጀንዳ በማስያዝ በውይይት ሊፈታ እንደሚገባው ሀሳብ ቀርቦ፣ በሀሳቡ ስምምነት ተደርሷል፡፡ በሌላ በኩል፣ አቶ ሙሉቀን ‹‹በቀጣይ አጀንዳዎች ላይ የምንስማማ ከሆነ ኮሚቴውን እውቅና እሰጠዋለሁ›› በሚል ቅድመ ሁኔታ ለማስቀመጥ ሀሳብ አቅርቦ፣ በአቶ በሪሁን እና አቶ ጌታቸው በኩል ‹‹እውቅና አልሰጠውም የምትል ከሆነ ውይይቱን መቀጠሉ ተገቢነት የለውም›› በማለታቸው፣ ሽማግሌዎቹ አቶ ሙሉቀን እውቅና መስጠት ቢችል መልካም እንደሆነ፣ ነገር ግን ምንም ግፊት እንደተደረገበት ሳይሰማው በነጻ ፍቃዱ ውሳኔውን ካሳወቀ ብቻ ውይይቱ እንደሚቀጥል ተገልጾለት፣ ‹‹እውቅና እሰጠዋለሁ›› በሚል ተስማምቶ ወደቀጣዩ አጀንዳ ታልፏል፡፡ - አጀንዳ ሁለት፡- አቶ ሙሉቀን በኮሚቴው ስም ከህዝብ የተሰበሰበውን ገንዘብ ቃል በገባው መሠረት ለሚዲያ ምስረታው በተቋቋመው ኮሚቴ ስም በተከፈተው አካውንት ገቢ እንዲያደርግ በአቶ በሪሁን አዳነ እና አቶ ጌታቸው ሺፈራው የተያዘው አጀንዳ ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም፣ አቶ ሙሉቀን ‹‹የእኔ የምለው ገለልተኛ ሰው አካውንቱን አብሮ እንዲያንቀሰቅስ የሚደረግ ከሆነ፣ ወይም እኔ ራሴ የምካተት ከሆነ አስገባለሁ›› በሚል ሀሰብ አቅርቧል፡፡ አቶ በሪሁን እና አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ገንዘቡ ከህዝብ የተሰበሰበ ስለሆነ በቀጥታ ለዚሁ ዓላማ ለሚሰራው ኮሚቴ በስሙ በተከፈተው አካውንት ገቢ መደረግ አለበት የሚለውን አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ ሙሉቀን ተስፋው ‹‹የእኔ የምለው ገለልተኛ ሰው አካውንቱን አብሮ እንዲያንቀሰቅስ የሚደረግ ከሆነ፣ ወይም እኔ ራሴ የምካተት ከሆነ አስገባለሁ›› በሚለው አቶ በሪሁን እና አቶ ጌታቸው ተስማምተው፣ በዚሁ መሠረት ገንዘቡም ወደኮሚቴው አካውንት ገቢ እንዲያደርግ ስምምነት ተደርሷል፡፡ የኮሚቴው አካውንት በውጭም በሀገር ውስጥም የተከፈተ መሆኑ ተገልጾለት፣ የሙሉቀንን ጥያቄ ባስተናገደና ለአሰራር በሚያመች መልኩ ተግባራዊ እንዲደረግም ተስማምተዋል፡፡
- አጀንዳ ሦስት፡- ይህ አጀንዳ በሁለቱም ወገን ስማችን ጠፍቷል በሚል አንዱ ሌላውን ይቅርታ እንዲጠይቅ የቀረበ ሲሆን፣ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ሽማግሌዎች በሁለቱም ወገኖች የቀረቡ ቅሬታዎችን አዳምጠዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን ተስፋውም ሆነ በኮሚቴው በኩል የተገኙት በማህበራዊ ሚዲያ እና በተለያዩ መንገዶች አንዱ ሌላኛውን ስም አጥፍቷል የሚል ቅሬታ ነው ያላቸው፡፡ ሆኖም፣ ሽማግሌዎቹም እንደታዘቡት፣ በሁለቱም በኩል አደባባይ ባይገለጹ ይሻል የነበሩ ጉዳዮች መገለጻቸው አግባብ ባይሆንም፣ በዚህ ሁኔታ ይቅርታ ጠያቂም ተጠያቂም የሚኖርበት አግባብ ከመኖር ይልቅ ሁለቱም ወገኖች ከድርጊቶቻቸው ትምህርት ወስደው ሊያልፉት የሚገባ እንደሆነ ስምምነት ተደርሶ ታልፏል፡፡ ወደፊትም ስሜ ጠፍቷል የሚለውን ሰበብ እየተጠቀሙ የአማራን ህዝብ ትግል ሊጎዳ ከሚችል አካሄድ መውጣት እንደሚገባ የጋራ ስምምነት ተደርሷል፡፡
አጀንዳ አራት፡- ይህን አጀንዳ ሽማግሌዎቹ አቶ ሙሉቀን ተስፋው ወደኮሚቴው ተመልሶ በጋራ ቢሰራ መልካም ነው በሚል ያነሱት ሀሳብ ሲሆን፣ በሀሳቡ ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ አቶ ሙሉቀን ተስፋው ወደኮሚቴው ለመመለስ ሲስማማ፣ አቶ በሪሁን እና አቶ ጌታቸው በበኩላቸው የአቶ ሙሉቀን ወደኮሚቴው መመለስ የሌሎች የኮሚቴ አባላት ስምምነትንም እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ በእነሱ በኩል ቢመለስ ፍቃዳቸው እንደሆነና ሌሎች የኮሚቴ አባላትንም ሙሉቀን ቢመለስ ጥሩ ነው በሚል የተቻላቸውን አስረድተው ስምምነት ተደርሶ እንዲመለስ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን ተስፋው የኮሚቴው አባል እንደነበርና ኮሚቴውን በራሱ ጥሎ የወጣ በመሆኑ፣ አሁንም ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲመለስ አሰስበው፣ በኮሚቴው በኩል የሚደረሰውን ስምምነት እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡
ሽማግሌዎቹም የአቶ ሙሉቀን ተስፋው ወደኮሚቴው መመለስ እውን እንዲሆን የራሳቸውን በጎ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው ውይይቱ በተነሱ አጀንዳዎች ሁሉ ስምምነት ላይ ተደርሶ መጠናቀቁን ከታች ስማችን የተጠቀሱት ሽማግሌዎች በአንድ ድምጽ ማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ከውይይቱ በኋላ አቶ በሪሁን አዳነ እና አቶ ጌታቸው ሽፈራው ኮሚቴውን አነጋግረው የአቶ ሙሉቀን ወደኮሚቴው መመለስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት ማግኘቱን ለሽማግሌዎቹ አሳውቀዋል፤ ለህዝብም በይፋ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም፣ ይህን ስምምነት በተመለከተ ከሽማግሌዎች እውቅና ውጭ ቀድሞ በማናቸውም ወገን እንዳይገለጽ ስምምነት ቢኖርም፣ ይህን ስምምነት በተጻረረ መልኩ በኮሚቴው የወጣው መግለጫ በሀቅ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እያለ፣ የመግለጫ አወጣጥ ስምምነታችንን ግን የተጻረረ እንደነበር ታዝበናል፡፡
በመጨረሻም፣ በውይይት የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ እንዲሁም የአማራ ህዝብን ፍላጎት ከተጻረሩ አካሄዶች መቆጠብ እንደሚያስፈልግና ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ ከሚቱ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ ተገቢ መሆኑን በማመን፣ ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በዚሁ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ የሚዲያው ባለቤት የሆነው ህዝቡም ስምምነቱ ይህ መሆኑን ተገንዝቦ የሚዲያ ምስረታውን ሂደቱን በመደገፍ ላይ እንዲያተኩር እናሳስባለን፡፡ ይህን የሽማግሌዎች ሪፖርት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ወይንም የተለየ ሀሳብ አለን የሚል ካለ፣ ውይይቱ ሙሉው በድምጽ እየተቀረጸ የተደረገ መሆኑን በማስታወስ እንደአስፈላጊነቱ ሙሉውን ለህዝብ የምናደርስ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ - አቶ ወንድይራድ ኃ/ገብርኤል …………………………………………….
- አቶ ማሙሸት አማረ …………………………………………….
- አቶ አበበ ውቤ …………………………………………….
- አቶ በላይ ማናዬ …………………………………………….
(ከሽማግሌዎች መካከል የሆነችውና በአቶ ሙሉቀን ተስፋው ጥያቄ የተካተተችው እህታችን ወ/ት ወይንሸት ሞላ ይህን መግለጫ ለማዘጋጀት በነበረን የመጀመሪያ ቀን ግንኙነት ተገኝታ የነበር ቢሆንም፣ መግለጫውን ለመጻፍ በነበረን ቀጠሮ ግን አልተገኘችም፡፡ በተደጋጋሚ ስልክ ሲደወልላትም ልትመልስ አልቻለችም፡፡)
ጥር 16/2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ
