ከመንግስቱ ሙሴ ፌስ ቡክ የተወሰደ


January 22 at 7:53 PM ·

የሀገራችን ፖለቲከኖች ዘረኞችም ሆነው ስለዴሞክራሲ ያወራሉ። አንዳንዶች ደግሞ የዴሞክራሲ ምንነት እና ማንነት ባልተገለጠባት ሀገራችን ከወዲሁ እኔ ሊብራል ዴሞክራሲ ነኝ፣ ወይንም እኔ ሶሻል ሲሉ እናያለን። ይህ አባባል ትክክል ቢሆንም ዋናው ለሊብራልም ሆነ ልሌላ አይነቱ ስርአት መሰረቱ ዋናውን የዴሞክራሲን መሰረተ ሀሳብ መቀበል እና መተግበር ነበር። ዴሞክራሲ በሌለበት ሊብራል ወይንም ሶሻል ሊኖር አይችልም እና ማለት ነው። ዴሞክራሲ ማለት ደግሞ የብዙሀን ገዥነት (አስተዳደርም ሊሆን ይችላል) እና የአናሳ መብት የተከበረበት ስርአት ማለት ነው። ወይንም የብዙሀን ስርአተ አስተዳደር እና የግለሰብ ነጻነት የተከበረበት ማለት ነው።
አሜሪካኖች እጅግ ከሚኮሩበት አንዱ ስርአታቸው ህገመንግስታቸው ሲረቀቅ ያሰፈረው እና እያደገ የመጣው የምርጫ ስርአታቸው እና የግለሰብ ነጻነት ክብራቸው ነው። እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ይህን የግለሰብ ሙሉ ነጻነትን አከብራለሁ የሚለውን የሊብራል ዴሞክራሲ ስርአታቸውን የሚጋፋ አስተሳሰብ ተከስቶ አያውቅም ነበር። የ2016 ፕሬዜዳንታዊ የምርጫ ውድድር ግን ከሁሉም ቃሉን ለመጥራት እንኳን የሚፈሩትን የሶሻል ዴሞክራሲን ሀሳብ ይዞ የተነሳው የዴሞክራቲኩ ፓርቲን ዋነኛ ተመራጭ የነበረችውን ሒለሪ ክልንተንን ያስጨነቀበት መሰረታዊ አላማ የሶሻል ዴሞክራሲን መሰረታዊ አላማወች በመግፋት እና ብሎም በህልም ያልገመቱት አዲሱ የ21ኛው ዘመን ወጣት ደግፎት መነሳቱ ነበር። በእርግጥም በርኒ ሁለቱንም ፓርቲወች ያስደነገጠ እንደነበር ግልጽ ሲሆን። የዴሞክራቲክ ፓርቲው እድሉን ለሱ ቢሰጥ እና ሙሉ ትብብር ቢያደርግ ኖሮ ሚስተር ሳንደርስ የሪፓብሊካኑን ተመራጭ ዶናልድ ትራንፕን ሊያሸንፍ የሚችልበት እድል እንደነበር ይገመታል።
ባጭሩ ለማሳየት የሞከርሁት ሁሉም ሀገራት አሜሪካንን ጨምሮ የመጨረሻ እድገታቸው ወደ የሶሻል ዴሞክራሲ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ለምሳሌ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዜዳንት ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ውድድሩ ከማሳቸስተሩ አስተዳዳሪ ሚት ራምኒ ጋር በነበረው ውድድር ዋናው የዴሞክራቲኩ ፓርቲ እና የፕሬዜዳንቱ መሪ መፈክር ከአሜሪካን ህብረተሰብ 1% የሆኑት 99% የአሜሪካንን የንዋይ ጸጋ የተቆጣጠሩት ተወካይ ነው ለድሀ አያስብም ምክንያቱም ድህነትን አያውቅም በሚል በእርግጥም ሕዝብን ያሳመነ ዘመቻ በማድረግ ለሁለተኛ ግዜ ፕሬዜዳንሲውን ለመውሰድ ችለዋል። ይህ ማለት የሕዝቡ ድጋፍ እያጋደለ ያለው ወደማህበራዊ ፍትህ እና ተመጣጣኝ የሀብት ሽግሽግ መሆኑን ሲሆን። ለዚህ ደግሞ ከሊብራል ዴሞክራሲ ይልቅ ሶሻል ዴሞክራሲ የቀረበ ስርአት እንደሆነ ዛሬ የኖርዲክ ሀገራት የሆኑት የአውሮፓ ሕብረት አባላቱ ጥሩ ሞዴሎች ናቸው። እንዴውም በብዙሀን የአውሮፓ ሀገራት በአለም የዜጎች ኑሮ የአንደኝነት ቦታውን ለረጅም ግዜ የያዘችው ኖርዌይ ለሶሻል ዴሞክራሲ ጥሩ ሞዴል እንደሆነች ይታወቃል።
ሊብራል ዴሞክራሲ ምንድን ነው
ሊብራል ዴሞክራሲ የግለሰብ ነጻነትን አጥብቆ የሚደግፍ ስርአት ነው። ግለሰብ ያሻውን የማድረግ እድሉ ክፍት ነው። በነጻነት የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀትም የዴሞክራሲ መሰረታዊ እሴቶች ከግለሰብ ነጻነት ጋር ያቆራኛቸዋል። ሊብራል ዴሞክራሲ ትልቁ ጥንካሬው የጠነከረ ወይንም እጅግ ታታሪ የሆነ ግለሰብ ወይንም ጭንቅላቱን ተጠቅሞ ለፈጠራ የበቃ ግለሰብ ገደቡ ይህ ተብሎ የሚመዘን አይደለም። ለምሳሌ የማይክሮሶፍት ፈጣሪ ቢል ጌትን እና የማካንታሽ ፈጣሪ ሟቹን እስቲቭ ጆብ በፈጠራ ችሎታወቻቸው እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አለምን ለመለወጥ ያስቻለ እና ባለሀብት ያደረገ ችሎታቸው ትልቁ የስነልቦናዊ መሰረቱ የግለሰብ ነጻነት ገድብ አልባ የሆነው ባህል እና ስርአት ሲሆን፣ በአንጻሩ የአለማችን ብልጹግ የሆነችው አሜሪካ ውስጥ ለአይን የሚዘገንን ኑሮ ያላቸው ከሰውነት የወጡ ዜጎችንም የምታስተናግድ እንዲሆን ይኸው የግለሰብ መብት እና ተያያዥ አስተሳሰብ መሆኑ ግልጽ ነው። በሊብራል ዴሞክራሲ ማንም ሰው ሕግ እስካከበረ ድረስ ግለሰብ ሀብት የማግኘም ሆነ የመደህየት ልክ እና ገደብ የለውም። ይህ ማለት ስርአቱ ልክ በጫካ የሚኖሩት የዱር እንሣት የእለት ጉርስ ለማግኘት ጠንካራው ደካማውን ለራት እና ለቁርስ እንደሚያደርግ ሁሉ የሊብራል ዴሞክራሲ ፍልስፍናም በኤኮኖሚው ዘርፍ ያሸነፈ ሁሉን መጠቅለል መብቱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስርአት ነው። ሰው የየግሉን እምነት ቢያመልክ ይህን አታድርግ ከእኛ ባህል እና አሰራር ውጭ ነው ብሎ የሚያወግዘው የለም። የተለያዩ እምነቶች በተለያየ ስርአት ይከበራሉ፣ ዜጎች ያሻቸውን የማምለክ መብታቸው ክቡር ነው። እኛን ያልመሰለ ተብሎ ወደጠርዝ የሚገፋ ባህል፣ እምነት የለም። ዋናው ነገር ህግ ማከበር ነው። ይህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ አላማወች ናቸው። ሀገር የጋራ እንደሆነች ሁሉ የጋራ ሀገርን በጋራ በተመረጠ መንግስት ያስተዳድራሉ። ዳኝነት ለሕዝብ ምርጫ የተሰጠ ነው። እናም ዳኞች በየግዜው የዳኝነት ወንበር ላይ ለመቀመጥ የሕዝብ ይሁንታ ይፈልጋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ብዙሀን የመረጠው በአንድ ቁጥርም በላጭ ቢሆን ቦታውን ይይዛል። እነዚህ የዴሞክራሲ ዋና መሰረቶች ናቸው።
ባጭሩ ዴሞክራሲ ማለት የብዙሀን አስተዳደር ማለት ነው። ሊበራል ዴሞክራሲ ማለት በብዙሀን አስተዳደር ውስጥ የግለሰብ ነጻነት ፍጹም እና የማይነካ ብሎ ያስረገጠ ስርአት ማለት ነው። የግለሰብ ነጻነት ሲከበር የብዙሀን አስተዳደር ይከበራል ብዙሀኑ የግለሰብ ስብስብ ነው ማለት ነው። የግለሰብ ነጻነት ስንል፣ በማንኛውም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩች ሁሉ የግል ነጻነት እና መብት ክቡርንትን መቀበል ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ዛሬ አሜሪካ ስሙን ማንሳት የምትፈራው ከክላሲካል ማርክሳዊ ፍልስፍና ተያያዥ የሆነው በስም ከሶሻሊዝም ጋር ስለሚመሳሰልባት ሶሻል ዴሞክራሲን በመጋረጃ ልትጠቀልለው ብትሞክርም ወደማይቀረው ስርአት እያንደረደራት መሆኑ ጤና እና ሕክምና “ሰበአዊ መብት ነው” የሚለው መፈክር ስር እየሰደደ እና የሀገሪቱ 1/6ኛውን ኤኮኖሚ የሚይዘው ግዙፍ የግል እና የውድድሩን ሜዳ በትቂት ተጫዋቾች ይዞ የተንሰራፋውን የሜዲካል ኢንሹራንስን እና የህክምና ዘርፉን ሁሉም ዜጋ ያለጥያቄ እንዲዳረሰው ከ 50 ያለነሱ አመታት ሲደረግ የቆየው ትግል ዳሩ እየተቃረበ መምጣት አንዱ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ፍትህን የመቀበል ግዴታ መቅረቡን አመላካች ነው። በኤኮኖሚው ዘርፍ ሊብራል ዴሞክራሲ የሀብት ሽግሽግን የማይመለከተው ግን የግለሰብ ነጻነትን ከናጠጠ ቢሊየነርነት እስከ መናጢ ድህነት የሚያከብር ስርአት ማለት እንደሆነ ይታያል።
ዴሞክራሲ በተለያዩ ሕዝቦች እና ባህሎች በተለያየ አሰራር ሊተገበር ይችላል። ለምሳሌ ምእራባውያን ግለሰባዊነት ትልቅ ባህል ነው። ሁሉም ሰው ስለእራሱ ይጨነቃል። ጎረቤቱ ምን ይኑረው ወይንም ይብላ አለያም ጦሙን ይደር ጉዳዩ አይደለም። ይህ ባህል ነው። ሰው ስለራሱ እንጅ ስለሌላ ማሰብ የለበትም። እናም ሊብራል ዴሞክራሲ ከዚህ አይነት ባህል ጋር ይቆራኛል።
የተውሶ አይዲዮሎጅ እና ቤተ ሙከራ
ለዚህ ነው ብዙ ግዜ የተውሶ አይዲዮሎጅ ሊሰራም ላይሰራም ይችላል። ለምሳሌ ዴሞክራሲ መሰረታዊ እና ለሁሉም የሰው ዘር ሊያገለግል የሚችል ዩኒቨርሳል ነው። ሊብራል ወይንም ሶሻል ስንጨምርበት ግን እንደባህል ላንዱ በጥሩ ሊሰራ የቻለ ለሌላው በሁሉም መልክ ላይሰራ ይችላል ማለት ነው።፡ለዚህ ዋናው የሕዝብ ልማድ፣ ወግ፣ አብሮነት እና ተያያዥ ባህላዊ እሴቶች ከግምት ሊገቡ ይገባል።
ትዝ ይለኛል 1967 ታህሳስ ወር ግዜያዊ ወታደራዊ መንግስት “ሕብረተሰባዊነት” አወጀ። ስሙንም የኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊነት አለው። ይህ አባባል በየስብሰባ አዳራሽ ሁሉ ውግዝ ተባለ። አውጋዥ ምሁራንም ሶሻሊዝም አንድ ነው አሉ! የኢትዮጵያ ብሎ ሶሻሊዝም የለም አሉ። ተከራካሪወች በጎን የታንዛኒያ ሶሻሊዝም ለታንዛኒያ ከሰራ እንዴት የኢትዮጵያ የኢትዮጵያው አይሰራም በሚል ተሟገቱ ግን ተረቱ። ያለው ሳይንሳዊ እና አንድ ብቻ ነው በሚል የተውሶ አስተሳሰብ መላ የሀገሪቱ ልሂቃን ሁሉ ልባውልቅ ክርክር አደረጉበት እና እረቱ “ከሳይንሳዊው አውሮፓ ፈጠሩ ሶሻሊዝም ጋር ወደፊት በሚል ማርሽ አገቡ እና ሁሉም ከነፈ”። ደርጉም አመነ እና ሰጥቻችኋለሁ ብሎ አረፈው። ሚያዚያ 1968 “አዲሱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት” በመኢሶን ይሁንታ እና እረቂቅ ከቻይና ተገልብጦ ታወጀ። ሀገራችንም የካፒታሊዝምን ጭቆና ሳትቀምስ በአዲሱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ተሻግራ ሶሻሊስት ትሆነለች ተባለ። ያ የቻይና ግልብጥ ፍልስፍና ለኢትዮጵያ እንዲሰራ ሰው መቆረጥ እና መፈለጥ ወይንም ተጠርቦ መስተካከል ነበረበት ማለት ነው።
በቀጣይ እስክመለስ ትችት፣ አስተያየት ተገቢ ነው።
በሕገመንግስት የተያዘው የዘር ፖለቲካ እንዲፈርስ እንታገል ትግሉን እና ያገኘነውን ነጻነት እናስቀጥል– አዲዮስ ህወሓት!

e