እናንተየ ሰዉ እኮ ጨርሶ ማሰብ ማገናዘብ ተሳነው ምን ይሻላል??? የሰዉ የማሰብ የማገናዘብ አቅም ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ ጭንቅላቱ ንፍሮ ሆኖ ቁጭ ብሏል፡፡

እስኪ የዋሃኑን ያነቃቸው እንደሆን የበረከትን ክስ ምሳሌ ላድርግና አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው፦

የዐቢይ አሥተዳደር ወይም ወያኔ/ኢሕአዴግ በረከትን ማሰርና ለፈጸማቸው ወንጀሎች ተጠያቂ በማድረግ፣ ለግፍ ሰለባዎቹ ፍትሕ በማሰጠት፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን ቢፈልግ ኖሮ የገዛዘፉ ወንጀሎቹን ትቶ ወራት የወሰደ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ስሠራ ቆየሁ!” እያለ ይሄንን ዋስትና እንኳ የማያስከለክል መናኛ ክስ ይመሠርት ነበር ወይ???

መረጃ ጠፍቶስ ይመስላቹሃል ወይ ከባባድ ወንጀሎቹ ተጠቅሰው ክስ ያልተመሠረተበትና በቀላል ወንጀሎች ብቻ ክስ የመሠረቱበት??? የእነ አቶ በረከት እስር ዐቢይ የአውሮፓውያን በሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት መስጠት ያቆሙትን እርዳታ፣ ቀጥተኛ የባጀት ድጋፍና ብድር እንደገና መስጠት እንዲቀጥሉ ለማግባባት ካደረገው ጉዞ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነበር እሱም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ከዚህ የተለየ ዓላማ የለውም፡፡ ከባድ ክስ ያልተመሠረተበትም የተፈለገው ታሰረ የሚለው ዜና ብቻ በመሆኑና እስሩ አውሮፓውያኑን ከመደለያነት ያለፈ ባለመሆኑ ነው፡፡

ሲጀመር አቶ በረከት የጥረት የቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆኑ የተመሠረቱበት ክሶች በቀጥታ እሱን የሚመለከቱ ወይም እሱን ተጠያቂ የሚያደርጉ አይደሉም!!! ሌሎቹን ባለሥልጣናትንም ለሌላ ወሳኝ ጊዜያት ወይም ሁነቶች መቆመሪያነት እየቆጠቡ በየተራ ይጠቀሙባቸዋል እንጅ እስሩ የውሸትም ቢሆን ሁሉንም በአንዴ እንሰር አይሉም፡፡ ጠብቁ ነገ ታገኙታላቹህ፡፡

ወገኔ እንቅጩን ልንገርህ??? በዚህ አገዛዝ አንድም የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣን ተጠያቂ አይሆንም!!! የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በፈጸሙት ወንጀል ልክ ቅጣታቸውን ያገኛሉ፣ የሕግ የበላይነትም ይረጋገጣል፣ ፍትሕ ይሰፍናል፣ የሕዝብ ዕንባ ይታበሳል፣ የግፍ ሰለባዎች የፍትሕ ጥያቄ ይመለሳል ብለህ ካሰብክ በቅዠት ዓለም ውስጥ እንዳለህ ዕወቅ!!! ይሄ ነገር ሊሆን የሚችለው በወያኔ/ኢሕአዴግ መቃብር ላይ ብቻ ነው፡፡

ምክንያቱም የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ይሄንን ሁሉ ወንጀል በሕዝብና በሀገር ላይ የፈጸሙት ለወያኔ/ኢሕአዴግ ህልውና ሲሉ በመሆኑ አንዱ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣን ከሌላው ተለይቶ ተጠያቂ ሊደረግ አይችልም!!!

በሥርዓት ደረጃ ነው የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ወንጀለኛነቱ፡፡ አንድ አገዛዝ ወይም ሥርዓት በአገዛዝ ወይም በሥርዓት ደረጃ ወንጀል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሀገር ክህደት፣ ምዝበራና ዝርፊያ ከፈጸመ በተናጠል እከሌን ወይም እከሊትን ተጠያቂ ሊያደርግ አይችልም!!! ይሄንን ቢያደርግ ሥርዓቱ ወዲያውኑ እንደ እንቧይ ካብ ይናዳል፡፡ ይሄንን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ስለሆነም አያደርጉትም!!! ለዚህም ነው እነ ደብረጽዮን ለተፈጸሙ ጥፋቶች ተጠያቂነት የሚመጣ ከሆነ ሁላችንም ነን ተጠያቂ መሆን ያለብን፡፡ ጥፋቱንም ልማቱንም ሁላችንም በጋራ ነው ያደረግነው!” ሲሉ የሚደመጡት፡፡

በእርግጥም የለውጥ ኃይል ነኝ!” የሚለው አካል ወንጀል የፈጸመ ባለሥልጣንን ሕግ ፊት አቅርቤ በፈጸመው ወንጀል ልክ ቅጣቱን እንዲያገኝ አደርጋለሁ፣ የሕግ የበላይነትን አረጋግጣለሁ፣ ፍትሕን አሰፍናለሁ፣ የሕዝብን ዕንባ አብሳለሁ፣ የግፍ ሰለባዎችን የፍትሕ ጥያቄ እመልሳለሁ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብት አረጋግጣለሁ…!” በማለቱ የሚሆን ከሆነ ለማየት ሲል ሕዝቡ ድጋፉን የለውጥ ኃይል ለሚባለው ሰጠ እንጅ እንደ ሥርዓት የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ በዚህች ሀገርና ሕዝብ ላይ ለፈጸመው ወንጀል፣ ግፍና ክህደት፤ ላደረሰው ውድመት፣ ኪሳራና ጥፋትማ በእርግጥም ሁሉም የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናትና አባላት በሙሉ በየደረጃው ተጠያቂ ነው!!!

እነ ደብረጽዮን ሁላችንም ተጠያቂ የማንሆን ከሆነ ማንም ተጠያቂ መሆን የለበትም!” በሚሉት መሠረት ዋና ዋናዎቹ ግፈኛ፣ አረመኔ፣ ዘራፊ፣ ሌባና ወንበዴ ባለሥልጣናት በሕዝብና በሀገር ላይ በፈጸሙት ወንጀል ልክ አንድ ሁለቱ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ከባባድ ወንጀል ፈጻሚዎች የማይጠየቁና የማይቀጡ ከሆኑማ እኮ ለምን ብሎ ነው ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወያኔ/ኢሕአዴግ ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት የሚገደደው???

አንዳንዶች ደግሞ ምን ይላሉ እስሩ የእውነት ባይሆን ኖሮ እነ በረከትን የሚያክል ቱባ የወያኔ ባለሥልጣን ለውሸት እስር ብሎ እራሱን አዋርዶ ለእስር ይዳረጋል ወይ?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄ ወያኔዎችን ጠንቅቆ ካለማወቅና ሰዎቹ ለዓላማቸው መሳካት ሲሉ ለውሸት እስራት አይደለም እስከሞት ድረስ ዋጋ ለመክፈል የቆረጡና በዚህ መሠረትም ታግለው ለዚህ እንደደረሱ ካለማወቅ ካለመገንዘብ የሚመነጭ ደካማ እሳቤ ነው፡፡

እናም እባክህን ወገን ሆይ! በከንቱ የማይሆን ነገርን በመመኘት ወርቃማ ጊዜህን አታባክን??? ሽህ ዓመት እንኳ ወያኔ/ኢሕአዴግን ብትጠብቀው ነገ ዛሬ እያለ ዕድሜህን በከንቱ ያስፈጅሀል እንጅ ይሄንን ፈጽሞ አያደርግም!!! እነሱም የሚፈልጉት አንተን በከንቱ ምኞት ዘፍቀው ከዛሬ ነገ ተጠያቂ ይሆናሉ!” እያልክ ስትጠብቅ ዕድሜያቸውን ማራዘም ነው!!! ይሄ ነው ስልታቸው ሌላ አይደለም፡፡ እናም እባክህን ንቃ???

የማጃጃያ ልፈፋቸው አዚም ሆኖብህ ማስተዋልህን ጋርዶብህ ነው እንጅ፣ አፍዝዞ አደንዝዞህ ነው እንጅ ወንጀልን በየዓይነቱ እስከአፍንጫቸው የተነከሩበት ወንጀለኛ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አሁንም በዐቢይ ካቢኔ (ሸንጎ) ውስጥ ያሉ መሆናቸውን በማየት ብቻ እንኳ የዐቢይ አሥተዳደር ወይም ወያኔ/ኢሕአዴግ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ፍትሕን የማስፈን፣ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ የሞራል ብቃትና ፍላጎት የሌለው መሆኑን መረዳት እንዴት ያቅታል??? በተለይ ፊደል ቆጠርኩ የሚለው ክፍል ይሄንን መረዳት እንዴት ይሳነዋል???

ወያኔ/ኢሕአዴግ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥና ለፍትሕ መስፈን ቁርጠኛ ቢሆንና የሚፈልግም ቢሆን ኖሮ እነኝሁ ወንጀለኛ ባለሥልጣናቱ የቀደመው ወንጀላቸው ሳይበቃቸው አሁንም የዘረፉትን የሕዝብ ገንዘብ እየረጩ የሕዝብን ደም እንደፈለጉ በየቦታው እንዲያፈሱ፣ የሀገርን ሰላምና መረጋጋት እንዲያውኩ፣ የሕዝብን አብሮነትና አንድነት እንዲበጠብጡ፣ የሀገርን ህልውና ለአደጋ እንዲዳርጉ በመፍቀድና ይሄንንም ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙም ከሥልጣን የተባረሩ የለውጥ አደናቃፊዎች ናቸው!” እያለ በደረቁ ከመወንጀል ያለፈ ነገር ባለማድረግና በዝምታ በመመልከት አይነኬ ናቸው!” የሚል መልእክት ለሕዝብ እያስተላለፈ በነፍስህ ይቆምርብህና ይቀልድብህ ነበረ ወይ???

ሲጀመር የለውጥ አደናቃፊ ተብሎ የሚኮነነው ኃይል የለውጥ ኃይል ከሚባለው ኃይል አቅም በላይ ሆኖ በሀገሪቱ በፈለገው አካባቢ ረብሻ ቀውስ መፍጠር፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨትየሚያስችል ጠንካራ መዋቅርና አቅም ያለው ከሆነና የለውጥ ኃይሉ ይሄንን የለውጥ እንቅፋት በቁጥጥር ስር ማዋልና አደብ ማስገዛት የሚያስችል አቅም የሌለው ከሆነ እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ የለውጥ ኃይል የሚባለው የሕግ የበላይነትንና ፍትሕን ያሰፍናል!” ተብሎ ተስፋ ሊጣልበት የሚችለው???

ኃይልና ጉልበቱ ያለው የለውጥ እንቅፋት የሚባለው ከሆነስ እንዴት የለውጥ ኃይል ለሚባለው ሥልጣን ሊለቅ ቻለ??? ወዶ ከለቀቀስ ለምንድን ነው ሀገር የሚያውከው??? የለውጥ ኃይል የሚባለው ሕግን ማስከበር የማይችል ከሆነ፣ የለውጥ እንቅፋት የሚባለውም ለሕግ የማይገዛ ከሆነ እንዴት ሆኖ ነው ከዚህ በኋላ በዚህች ሀገር የሕግ የበላይነት ሊረጋገጥና ፍትሕ ሊሰፍን የሚችለው??? አንድ ሕዝብ ቃዣታም ካልሆነ በስተቀር እንዴት በዚህ ውሉ በጠፋበትና በተሳከረ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በአገዛዙ ተስፋ ሊሰንቅ ይችላል??? ወያኔ/ኢሕአዴግ ሁኔታውን ለምን በዚህ መልኩ እንደሚያስኬደው ታውቃላቹህ??? ይህ ቁማር ዕድሜ ዘመናቹህን በነገ ዛሬ እየቃዣቹህለት ለመግዛትና ዕድሜውን ለማራዘም ስለሚያስችለው ነው ሌላ አይደለም!!!

የዐቢይ አሥተዳደር ወይም ወያኔ/ኢሕአዴግ ወንጀለኞችን ለፍርድ አቅርቦ በፈጸሙት ወንጀል ልክ ተጠያቂ የማድረግ ወኔ ብቃትና ቁርጠኝነት ቢኖረው ኖሮ የሕዝብ ቁጣና ጥያቄ ትኩስ በነበረበት ሰዓት ነበር ተጠያቂ ያደርጋቸው የነበረ፡፡ ነገር ግን ወንጀሉ የአንድና የሁለት ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆን እንደሥርዓት በሙሉ የአገዛዙ ወንጀል በመሆኑና ተጠያቂ እናደርጋለን!” እያሉ አንተን ከማጃጃል ውጭ እራሳቸውን ተጠያቂ አድርገው በራሳቸው ላይ የመፍረድ ቁርጠኝነት፣ ፍላጎትም ሆነ የሞራል (የቅስም) ልዕልና ፈጽሞ ስለሌላቸው ነው ያላደረጉት፡፡ እስከአሁን ያላደረጉትን ደግሞ እያስመሰሉ ያጃጅሉህ እንደሆነ ነው እንጅ ወደፊትም አያደርጉትም!!!

እናም እባክህን ወገን ሆይ ንቃ??? ወርቃማ ጊዜህን በከንቱ አታባክን??? በጊዜ ንቃና ወያኔ/ኢሕአዴግን ገርስሰህ ጥለህ የሀገርህ፣ የመብትህ ባለቤት የሚያደርግህን ነጻነትህን አረጋግጥ???

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com