ከመንግስቱ ሙሴ ፌስ ቡክ የተወሰደ
ስም ያለው ስሙ ከመቃብር በላይ እንዳበበ ይኖራል የሌለው ስሙ በተነሳ ቁጥር ይረገማል።
አቶ ዳዊት ዮሐንስን እልፈት በተመለከተ እዚህ በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ተመለከትሁ። አንዳንዶችም ባህላዊውን ነፍስ ይማር እያሉ ያለፉም አየሁ። የሰው ልጅ እድሜው ይህችን ያክል መሆኗ በዚህ ሰው መርዶ የሚታይ ነው። ለዚህች አጭር እድሜ ግን ሰው የራሱን ክብር አጉድሎ፣ የሌሎችን ሕይወት አመሰቃቅሎ ሲያልፍ አለፈ ይባላል። በየዘመኑ ግፍ ሞልቶ ተርፎ ነው ከዘመን ዘመን ተለውጦ አላየንም። የሰው እድሜ አጭር ናት በዳይም ተበዳይም መንገዱ አንድ ነው። ከሞቱ በኋላ ሽህ ዘመን የዘለቁ ግን ሞልተዋል (ቅዱስ ላሊበላን፣ ዘረ ያእቆብን ያስታውሷል) ለምሳሌ በላይ ዘለቀን በስሙኒ (25 ሳንቲም) ገመድ አንጠለጠሉት እና ገደሉት።
የበላይን አሟሟት የሰማ አንጎራጓሪ ሊያምን ተሳነው እና እንዲህ ብሎ አንጎራጎረ
ተሰቀለ ቢሉኝ ጀበርናው ነው ብየ
ተሰቀለ ቢሉኝ በልጅጉ ነው ብየ
ተሰቀለ ቢሉኝ ዝናሩ ነው ብየ
ለካ በላይ ኖሯል ታላቁ ሰውየ።
ያች እንጉርጉሮ ዘመን ተሻግራ የጎበዛዝትን አሞት ለኳሽ ሆነች።፡ግፈኞች በስሙኒ ገመድ አንጠለጠሉ እና ገደሉት ታሪኩ ግን ስንት ጀግናን ፈጥሮ ሜዳ ላይ አውሏል። መመማያ እና ቃል ማሰሪያም ሆኗል። የጀግንነት ልክ ሲለካ በላይ ዘለቀ ከፊት ቆሞ ይታያል። የዚያን ጀግና ስም ሳይነሳ የሚውልበት ቀን የለም ማለት ይቀላል።
ዳዊት ዮሐንስ አለፈ ሲባል ይገርማል አይ የሰው እድሜ?? ብለን እንድንጠይቅ ሆነ። በነበረበት ዘመን ስንት ቤት ተዘጋ? ስንት ወጣት አፈር ለበሰ? ስንቱ ያኔ አማራነህ ተነስ ተብሎ መባረር ዋና ነው እና “ነፍጠኛ” ልቀቅ ተብሎ መዳረሻ ያጣው ዜጋ ቤቱ እና አምላክ ብቻ ነው አዋቂው። ለዚህች አጭር እና ብጣሽ እድሜ ማለት ነው። መሞቱን የሰማ ሁሉ ምን እንዳለ ልቦናውን ይወቅ- ብኩን እና “ባንዳ” የሚመጥን ስም ስያሜውም ለዚህ አይነቱ ብኩን እኔን እኔን እንዲህ ባጭር ለሚኬደው ሰው ለምን ብኩን ጎዳና ይከተላል? ጮማ ቢቆረጥ እንደቀልቀሎ ለሚነፋ እና ቅርጽ ለሚያበላሽ ሆድ ነው። የዚህ አይነቱ አሟሟት በታሪክ በክፉ የሚነሳ (ከተነሳ ማለት ነው) አለበለዚያ በቃ ትቢያ ሆኖ መቅረት የሁሉም ስጋ የለበሰ የመጨረሻው ስጋው ወደአፈርነት ይቀየራል ስም ያለው፣ ለሀገር የሰራ፣ ለወገን የቆመ ትእቢትን እና ክፉነትን አሽቀንጥሮ ደግነትን የተከተለ በምድር ስሙ እስከዘለአለም ይኖራል (በላይ ዘለቀ ጥሩ ምሳሌ ነው) የላይኛው ቤቱም ለደግነቱ ክፍት ሆኖ ይጠብቀዋል ብለው ሁሉም ሀይማኖቶች ያስተምራሉ።
በአሜሪካን ሀገር በጥቁሮች ላይ ግፍ ሰሪው እና ለነጭ ዘረኝነት ትልቅ ተምሳሌት የነበረው George C. Wallace ለአለባማ ስቴት ጋቨርነር ሆኖ ለውድድር በሄደባቸው አመታት 1964፣ 1968፣ 1972 የጥቁር አሜሪካውያንን የእኩልነት እና ከአሜሪካን ህብረተሰብ አብሮ መኖር፣ መምረጥ፣ መመረጥ፣ የትምህርት እድል፣ እና በእኩልነት እና ነጻነት መኖርን ተጻርሮ የቆመ ብቸኛው አስተዳዳሪ ነበር። በመጨረሻ እድሜው ንስሀ ግብቶ፣ ይቅርታ ጠይቆ አለፈ። በታሪክ ስሙ እና ለከፉ ስራ ተምሳሌ ነው። እንደሰው ስህተቱን ተቀብሎ አርሞ እና ይቅርታን ጠይቆ በማለፉ ደግሞ ብዙ ሰው ይቅር ብሎታል፡፡ ተበዳዮች እና ግፍ ቀማሾች ይቅር ብለውታል። በሀገራችን ይህ የለም። ከ George Wallace ያላነሰ ብዙ ግፍ የሰሩ የሰሩትን ይቅር በሉኝ ሳይሉ የሄዱትም ሄደዋል ያሉትም ለዚህ አይነቱ ንስሀን ተቀብሎ የበደሉትን ይቅርታ ጠይቆ ማለፉ ያልተለመደ ነው እናም እስካሁን የሞከረው የለም ወደፊትም ይታያል። ባጭሩ ሌላ ቢቀር ትውልድ ማስተማር ያሰበ እና ለይቅርታ የተዘጋጀ አንደበት እስካሁን አላጋጠመንም ንስሀ ብሎ ነገር የለም። ቢገቡም በሚስጥር ይይዙታል የበደሉትን ይቅር በሉኝን ሳይጠይቁ ያልፋሉ። ይህ ጥሩ ያልሆነ ነው ወይንም ድፍን ጭንቅላት ይዘው በደልን ሳይሉ እነሱ እንደተበደሉ ሆነው ይሄዳሉ። ትንኝም አልገደልሁ ያለው የቀይሽብሩ አባወራም ያው ዛሬ እንዳለፈው አይነት ጉድ ነው።፡ትውልድ እንዲማር ቢያንስ የሰራነውን ስህተት እንቀበል። ለማስመሰል ከንፈር መምጠት ይቅር እና ትውልድ ይማር። ወደፊት የሚመጡ ትውልዶች ያለፈውን አይከተሉ። ይልቅ ስማቸውን ከመቃብር በላይ እንዲኖር ደግ ስራን ተግተው ይስሩ በደልንም እየተቀበሉ ለሀገር እና ወገን ያስቡ።
እናም እንዲህ በድፍን ያለንስሀ፣ የበደሉትን ይቅር በሉኝ ሳይሉ ከማለፍ ይሰውር!
ነፍስ ይማር
