February 2, 2019

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ምክርቤት ቀርበው በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ላይ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች በጥሞና ለመከታተል ሞክሬያለው። እንደተለመደው ንግግራቸው ከሞላ ጎደል ጥሩ የሚባል እና አቀራረባቸውም አስደማሚ ነው። ይሁንና ብዙ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡዋቸው ማብራሪያዎች በጥቅል እውነታዎች (General truth) የተሸፋፈኑ፣ ግልጽነት የጎደላቸው እና የአገሪቱ የበላይ ለሆነው አካልም የሚቀርብ ሳይሆን በሌሎች መድረኮች ላይ የሚሰጡ ማብራሪያዎች ነው የሚመስሉት።

በርካታ ጥያቄዎችን በመለሱበት ማብራሪያቸው ውስጥ በርካታ እና ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው የሚችሉ ነገሮችን ያነሱ ቢሆንም ምላሻቸው ግን በዝርዝር መረጃዎች የተደገፉ አልበነሩም። እንዲህ ያሉ ንግግሮች ብዙ ሰዎችን ሊያግባቡና ማንንም ሊጎረብጡ የሚችሉ ባለመሆናቸው ለአቅራቢውም ሆነ ለሰሚው ጥሩ መስለው ይታያሉ። ነገር ግን እንደ አገር በግልጽ በስም፣ በጊዜ እና በቦታ ተጠቅሰው ሊነገሩ እና ውይይት ሊካሔድባቸው የሚገባቸው እውነታዎች ከላይ ከላዩ እየተነካኩና በጥቅል ዳሰሳ እየተሸፋፈኑ መታለፋቸው የማይበረታታ አጉል አካሄድ ነው።

ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በንግግራቸው ውስጥ በወንጀል ተጠርጥሮ በመንግስት እየተፈለገ ያለ ነገር ግን ያልታሰረ ሰው የለም የሚለው ንግግራቸውን መውሰድ እንችላለን። በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጡት ማብራሪያ ሁለት መሰረታዊ ግድፈቶች አሉበት። የመጀመሪያው እነዚህን ማንነታቸው የሚታወቅ እና ጉዳይም የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን ነገር በጥቅል መግለጻቸው በእኔ እምነት ትክክለኛ አካሔድ አይደለም። ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ሰማቸውን ጠቅሶ እና የፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ አውጥቶ ሊይዛቸው ካልቻላቸው ሰዎች መካከል አንዱ እና ግንባር ቀደሙ አቶ ጌታቸው አሰፋ መሆናቸው ይታወቃል።

እኚህ ሰው ተደብቀው ሳይሆን የክልሉ መንግስት አሳልፌ አልሰጥም በማለቱም እንደሆነ የአደባባይ ሃቅ ነው። ይባስ ብሎም እኝህ ሰው የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ተደርገው መሾማቸውም ይታወቃል። ይህን ሃቅ በገደምዳሜ ለምክር ቤት ማቅረብ ምን ይሉታል። መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ የገጠሙትን ችግሮች በግልጽ ማስረዳት ነበረበት። ከክልሉ መንግስት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ያደረጋቸው ውይይቶች እና የተወሰዱ እርምጃዎችም ካሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝርዝር ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር። የትግራይ ክልል ግለሰቡን አሳልፌ አልሰጥም ብሎም ከሆነ በግልጽ ተነግሮ ምክር ቤቱ የውሳኔ አቋም እንዲወስድበት መደረግ ነበረበት። የፌደራል መንግስቱም አቅም አንሶትም ከሆነ ምክር ቤቱ ሁኔታውን በግልጽ ሊነጋገርበት እና የመፍትሔ እርምጃም ሊወስድ ይገባ ነበር። ከዛ ይልቅ ጠቅላይ ሚንስትሩ በስላቅ መልክ የሰጡት ምላሽ ደረጃውን ያልጠበቀ እና ተቀባይነትም የሌለው ነው።

እኛ ባናስራቸውም ግለሰቦቹ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው እራሳቸውን በመደበቃቸው ስለተገደበ እንደታሰሩ ነው የሚቆጠረው የምትለዋ አገላለጽ ውሃ የምትቋጥር አይደለችም። አንድም የፌደራል መንግስቱ በመላ አገሪቱ ተንቀሳቅሶ ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር አቅም ያነሰው መሆኑን ነው የሚያሳየው አለያም ግለሰቡን ለፍትሕ የማቅረቡ ጉዳይ ከፖለቲካ እንድምታ የዘለለ የሕግ አስከባርነት ቁርጠኝነት በፌደራሉ መንግስት በኩል ጉድለት ይታይበታል ማለት ነው። ሌላው ቢቀር የትግራይ ክልላዊ መንግስት እኚህን ሰው ከሰጣቸው ስልጣን ማንሳት እና ከአባልነት ማሰናበት ይጠበቅበት ነበር። ይህ አለመሆኑ በራሱ ከግለሰቡ መታሰር ባሻገር በክልሉ እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ጡዘት እልባት አለማግኘቱን ነው የሚያሳየው። ይህም ሆነ ከሆነ ነገሩ ለፓርላማው እና ለሕዝብ በይፋ ሊገለጽ የሚገባበት ጊዜ አሁን ይመስለኛል። እንዲህ አይነቱን ነገር እየሸፋፈኑ ብዙ መጓዝ አይቻልም።

ሁለተኛው የጠቅላይ ሚንስትሩ ግልጽነት የጎደለው እና በቂ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባው የነበረው ጉዳይ በምዕራብ ወለጋ ከኦነግ ጋር በተያያዘ የሚታዩት ችግሮች ላይ ነው። በጥቅል ንግግራቸው ውስጥ በቀጥታ ኦነግን የሚመለከቱ ነገሮችን ጠቃቅሰዋል። ጠንከር ባሉ ቃላትም ወርፈዋል። ይሁንና ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ግልጽ ጥያቄዎች አንዳንድ ፓርቲዎች፣ አንዳንድ ቡድኖች፣ አንዳንድ …… የሚጠቅሷቸው ስም አይጠሬዎች በማንነት፣ በጊዜ እና በቦታ ተጠቅሰው ያለው ሁኔታ በግልጽ ለምክር ቤቱ መቅረብ ነበረበት። መንግስት ከኦነግ ጋር የገባው እሰጥአገባ በምን መልኩ እንደተፈታ፣ የተደረጉ ድርድሮች ምን መልክ እና ይዘት እንዳላቸው፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል በቂ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብዮ ጠብቄ ነበር። በየመገናኛ ብዙሃኑ የኦነግን ነገር ለክልሉ መንግስት የተተወ የሚመስል አካሄድም አግባብ አይመስለኝም። ከየትኛውም ድርጅት ጋር የሚደረጉ እና የአገርን ልዑአላዊነት እና ጸጥታ የሚመለከቱ ጉዳዩች መያዝ ያለባቸው በፌደራል መግስቱ በኩል ነው።

ሦስተኛው የመሳሪያ ዝውውርን በተመለከተ ከየትኛውም ክልል በከፋ ሁኔታ መሳሪያ በአደባባይ ሲንቀሳቀስ እና ሲዘዋወር የሚታየው በአማራ ክልል ነው። ይህንንም በተመለከተ መንግስት ጥብቅ የሆነ እርማጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዝርዝር የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባሉ ብዮ ጠብቄ ነበር። ነገሩ ከኮንትሮባንድ ንግድ በላይ እና አሳሳቢ ደረጃም ላይ እየደረሰ ያለ ስለመሆኑ ብዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ እና ተደረጉ ያሏቸው የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ እጅግ የሚያስመሰግን እና ሊደገፍ የሚገባው የመንግስት ትልቅ የመሻሻል እርምጃ ስለሆነ እሱን ሳልጠቅስ ማለፍ አልወድም።

በቸር እንሰንብት!