February 6, 2019

በኔዘርላንድ የጤፍ ባለቤትነት ይገባኛል ያሉ ኩባንያዎች ጥያቄ በሄግ ፍርድ ቤት ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤትነት መብቷ ተመለሰላት፡፡

ከአመታት በፊት የጤፍ ዱቄትን አገኘሁ በሚል ከኔዘርላንድ መንግስት የባለቤትነት ፍቃድ የወሰደው ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል የተባለ የሆላንድ ኩባንያ ነበር።

ኩባንያው ከሆላንድ አልፎ በጣሊያን፣በቤልጄም፣ በኦስትሪያና በእንግሊዝ በጤፍ ላይ የባለቤትነት ፍቃድ ነበረው።

ከዚህ በፊት አንድ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ጋር በጤፍ ላይ በጋራ ለመስራት በገባው ውል መሰረት ወደስራ ገብቶም ነበር፡፡ ይሁንእንጂ ኩባንያው በመክሰሩ ድርጅቱን ዘግቶ የጤፍ መብቱን ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል ለተባለው ኩባንያ መሸጡ ይታወቃል፡፡

ይሄው ድርጅትም ማለትም ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል ጥራቱን የጠበቀ የጤፍ ዱቄት ባለመብት ነኝ ብሎ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ጉዳዩ በሄግ ፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ የባለቤትነት መብቱ አልኝ ሲል የነበረው ኩባንያ የፈጠራ ስራ የባለቤነት መብት እንደማያሰጠው ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በውሳኔው መሰረትም በጤፍ ባለመብት ላይ ኩባንያውም ሆነ ሌላ አካል የባለመብትነት ጥያቄ ያቀረበ ባለመኖሩ በኔዘርላንድ የጤፍ ባለመብት አለመኖሩን አሳውቋል፡፡
ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት አምባሳደር ፍፁም አረጋ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ ባለቤትነት መብት ለመመለስ ቀላል እንዳደረገው ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ህዳር የጤፍ ዱቄት ማግኘት የጤፍ ባለቤትነት መብት አያሰጥም በሚል ሙሉ መብቱን ቢሰርዝም መዝገቡን እስከ ትላንት ድረስ ለይግባኝ ክፍት እንደነበር ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው በጤፍ ዱቄት ላይ ምንም ዓይነት የፈጠራ መብት እንደሌለበትና በተልምዷዊ ዝግጅት የሚገኝ በመሆኑ ጭምር ነው ተብሏል፡፡

ሆኖም የኔዘርላድ መንግስት ድጋፍ እንዲሁም በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የበላቤትነት መብቱን ለማስመለስ የተደረገው ዘመቻ ተፅእኖ ፈጥሮ ሙሉ የባለቤትነት መብቱን ማስመለስ መቻሉን አምባሳደር ፍፁም ገልፀዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ደግሞ ጤፍና ተያያዥ የባለቤትነት መብት ጉዳዮችን ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመፍታት መስሪያ ቤታቸው ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑንና ለዚህም የህግ ተቋም መቅጠሩን አስታውቀዋል፡፡

በብሩክ ያሬድ/EBC