February 7, 2019


ነገሮችን አርቆ ማሰብ የሚችሉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ግን አለቦታው ነገሮችን አርቆ የሚያስቡ ሰዎች ራሳቸውም አደጋ ላይ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ከእነጭርሱም እነዚህን ሰዎች በጣም የሚፈሩ ባለሥልጣናት ስላሉ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ላይ ኤክስፐርት መሆን የሚችሉ ግን መረጃና እውቀቱ የሌላቸው የአገሪቱን ቁልፍ ቦታ ይዘዋል፡፡ ሰሞኑን የጤፍን ፓተንት አስመልክቶ ብዙ መሠረታዊ እውቀትና እውነትነት የጎደላቸው መረጃዎች እየተሰራጩ ነው፡፡ የጤፍን ፓተንት ጉዳይ አስመልክቶ እኔ የተሻለ ብቻም ሳይሆን ፓተንቱን የሚቃረን በላቦራቶሪ የተደገፈ መረጃ ፓተንቱ ከመጽደቁ በፊት (ዛሬ 10 ዓመት አልፎታል) ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አቅርቢያለሁ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ይሄው የጤፍ ጉዳይ ይወራል ግን አንድም እልባት አልተገኘለትም፡፡ እልባት ማግኘቱ ቀርቶ የፓትንቱን ይዘት እንኳን ተረድቶ መረጃ የሚሰጥ የለም፡፡ ግን በዚህ ፓተንት ሰበብ ትልልቅ ኮሚቴ ምናምን የሚባሉ ተቋቁሞ ሲሰራ ነበር፡፡ እንደገባኝ አውሮፓ ድረስ ተሄዶም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙሀንም ሆነ ፓተንቱን እንከታተላለን በሚሉ ሰዎች የሚሰጠው መረጃ ከፓተንቱ ይዘት ጋርም ሲገናኝ አላየውም፡፡ በድፍኑ የጤፍን የባለቤትነት መብት የእኛ ነው በሚል ነው ሁሉም የሚያወራው፡፡ ጤፍን እንደ ጤፍነቷ የባለቤትነት መብት የጠየቀ በሌለበት ሁኔታ ስለጤፍ የባለቤትነት መብት ለመከራከር ነው ኮሚቴ ተብለው የተሰየሙት ሲነግሩን የነበረው፡፡ በመሠረቱ በአለም ዓቀፍ ሕግ መሠረት አንድን የብዝሀ ሕይወት ሀብት(ጄኔቲክ ሀብት) የባለቤትነት መብት መጠየቅ አይቻልም፡፡ ይሄ ቀደም ባሉ ስህተቶች በፈጠሩት ትልልቅ ውዝግብ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ማንኛውም ከጄኔቲክ ሀብት ጋር የተያያዘ የባለቤትነት መብት ለማንም ቢሆን አይሰጥም፡፡ ይሄን ማንም ሊጠይቅ አይደፍርም፡፡ እንግዲህ የጤፍን ጉዳይ እንከታተላለን የሚሉት የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ይሄ ግንዛቤ ምን ያህል እንዳላቸው ከሚሰቱት መረጃ አንጻር አጠያያቂ ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትና መገናኛ ብዙሀንም እንዲሁ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ነው የሚዘግቡት፡፡ የሚከተሉት በቢቢሲና በኢቢሲ ከወቱት ማመሳከሪያ ይሁናችሁ

ቢቢሲ አማርኛ

https://www.bbc.com/amharic/news-47143089?ocid=socialflow_facebook&fbclid=IwAR3ArWYowgf5irpKJsp-HtJ1DzPc-pcsUyVEIIuDYP41_S1NvIpHYZWLqF0

ኢቢሲ አማርኛ

የጤፍ ጉዳይ ፓተንት የተጠየቀው በአጭሩ ጤፍ በተፈጥሮ ከሌለው ባሕሪ ውጭ ጤፍን ለዳቦና ለመሳሰሉት ምግቦች እንዲውል የሚያደርግ የዱቄት አዘገጃጀት ዘዴ ፈጥረናል በሚል ነው፡፡ ለዛም ጤፍ በተፈጥሮ ሊኖረው የሚችለውን የጥራት ደረጃ በአሕዝ በተደገፈ ሁኔታ አሻሽለንው ለዳቦና ለመሰል ምግቦች ጥራት ያለው እንዲሆን አድርገንዋል ነው፡፡ ይሄን የምለው ተራው ህዝብ እንዲገባው ነው፡፡ የጤፍ ዱቄት ጥራትን ማሻሻሉን ፎሊንግ ነምበር ከፍ እንዲል ወይም አሚሌስ አክቲቪቴ ዝቅ እንዲል አድርጋለሁ ነው ፓተንቱ ላይ በግልጽ የተቀመጠው፡፡ እነዚህ ተረድቶ እውን ጤፍ በተፈጥሮ ይሄ የተባለው የዱቄት ብቃት የለውም አለው ብሎ በመለካት የተጠየቀውን ፓተንት ማስቀረት ይቻል ነበር፡፡ በእርግጥም ይህን ማድረግ እኔ በግሌ ችዬ ነበር፡፡ ሆኖም 19 የጤፍ ዝርያዎችን ዱቄት ፎሊንግ ነበር ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕወት ጥበቃና የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋማት ብሰጣቸውም መረጃውን መጠቀምና የተጠየቀውን ፓተንት ማስቀረት ቀርቶ መረጃዬን ሊያጣጥሉብኝ ነው የሞከሩት፡፡ በዚህ ምክነያት ብዙ ደክሜ ከኢትዮጵያ ብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ተቋም እንድ ቡድን እንዴት እንደሰራሁት ለማየት የሠራሁበት ላቦራቶሪ ድረስ ወስጄ እዛው በአሉበት የጤፍ ዝርያዎችን ዱቄት ፎሊንግ ነበር ከመሳሪያው በቀጥታ አንብበዋል፡፡ ምስክር ከተባሉት ዶ/ር ተወልደንም ስለሁኔታው በአካል ባላገኛቸውም በስልክ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ ዶ/ር ተወልደ ሁኔታውን በእርግጥም ትኩረት ቢሰጡትም ግን በግልጽ ጉዳዩን እሳቸው መከታተል እንደማይችሉ ነግረውኛል፡፡ የጤፍ ጉዳይ ከጅምሩ ከኢትዮጵያ ወደ ኒዘር ላንድ የሄደበት መንገድ እጅግ አሳፋሪና በሆነ መልኩ ነው፡፡ ይሄን ጉዳይም ራሱ መንግስት ተብየው አሳምሮ ያውቃል፡፡

ሰሞኑን ታዲያ ፓተንት ተጠብቆለት የነበረው ሰው ፓተንቱ ተሻረበት በሚል ብዙ የተምታቱ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ መረጃዎች እየወጡ ያሉት ከመንግስት ባለስልጣናትና ከመንግስት መገናኛ ብዙሀን ነው፡፡ ሰሞኑን የሆነው ግለሰቡ ፓተንቱን ያጣበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ የባለቤትነትም ሆነ ሌላ ጥቅም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ጉዳዩ የሆነው አንድ ሌላ ካምፓኒ ከጤፍ ዱቄት ተመሳሳይ ምርቶችን በማምረቱ ምክነያት ባለ ፓተንቱ የፈጠራ መብቴን ተጋፍቷል ብሎ ይከሳዋል፡፡ ያኛው ደግሞ ፓተንቱ ምንም አይነት ፈጠራ የለውም ይልቁንም ሰብሉ በተፈጥሮ ያለውን ጥራት ነው ፓተንት ያደረገውና ስለዚህ ማንኛውም ሰው የፈለገውን አይነት ምግብ ከጤፍ ዱቄት ሊሰራ ይችላል በሚል ነው፡፡ ይሄንንም በመረጃ በማቅረቡ ፓተንቱ ተነሳ፡፡ ግን ልብ በሉ 10 ዓመት ሆኖታል አሁን፡፡ በቃ የሆነው ይሄው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ሲጀምር ሰውዬው የጤፍን ባለቤትነት መብት አልጠየቀም፡፡ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌላ ጤፍን እንዳያመርቱ አልከልከለም፡፡ ፓተንቱ ከጤፍ ዱቄት የሚመረቱ ምብቦች ላይ ነው፡፡ እንጀራን አይመለከትም፡፡ ጤፍ የባለቤትነት መብት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ ብሎ መዘገብ ስለሆኔታው አለማወቅ ነው፡፡ ከዛም በላይ አላስፈላጊ የሆነ ጥያቄ እንዲነሳ የሚጋብዝ ነው፡፡  ለማንኛውም ለመረጃ ያህል እኔ የሰራሁትን በሚከተለው ሰንጠረዥ እዩት FN (falling number)፡፡ ልብ በሉ ፓተንቱ ላይ 250 እና ከዛ በላይ ፎሊንግ ነበር ለዳቦና መሰል ምግቦች ተስማሚ ነው ሚል በግልጽ ተጽፏል፡፡ ከእነዚህ ዝርያዎች ውስጥ ከ250 በታች የሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

No.Variety FN for flour passed through 132µ sieve
1DZ-Cr-44263
2DZ-01-1681238
3DZ-Cr-37400+
4DZ-01-787400+
5DZ-01-196349
6DZ-01-1285255
7DZ-Cr-255241
8DZ-01-974265
9DZ-01-899395
10DZ-01-99222
11DZ-01-1281400+
12DZ-Cr-236240
13DZ-01-2675400+
14DZ-01-354284
15DZ-Cr-82237
16DZ-Cr-387276
17DZ-01-1287290
18DZ-01-2053236
19DZ-Cr-358266

ከዚህ በላይ ግን ይሄ ፓተንት ተሰጥቶት የነበረው ድርጅት (ሥሙን በየጊዜው ይቀይራል) ከኢትዮጵያ ጋር ውል ገብቶ ነበር፡፡ ውሉ ውስጥ ለኢትዮጵያ መክፈል ያለበት ገንዘብ አለ፡፡ ጤፍ በጤፍነቱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር በምርምር ያወጣቸው ዝርያዎችን ነው መጀመሪያ ሲጠቀም የነበረው፡፡ ለዛ ደግሞ ለኢትዮጵያ በሚያመርተው ምርት ብዛት ሊከፍል ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ሥሙን ቀይሮ በሌላ ሥም እሱ ቀጠለ ውሉ ውሀ በልቶት ቀረ፡፡ የፓተንቱ ጉዳይ ከባለቤትነት ይልቅ ዓለም አቀፍ ድርሻን መረጃ በመስጠት መወጣትና ሌሎችም ለኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት እንዲያደርጉ ነው፡፡ ከአንድ ድርገጅት ይልቅ አለማአቀፋዊ ድርሻ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ውሉ የኢትዮጵያ መንግስትና አንድ ተራ ነጋዴ ስለነበር ኋላ ውሉ ሲፈርስ የኒዘር ላንድ መንግስት አያገባኝም ነው ያለው፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ መንግስትና ተራ ነጋዴ በዚህ መልክ መዋዋል የአገርንም ክብር የሚያጎድፍ ነው፡፡ ይሄንንም ስለተረዳ ነው ሰውዬው እንደፈለገ የሚቆምረው፡፡

አሁንም እላለሁ ስለዚህ ጉዳይ በቂ መረጃ አለኝ፡፡ ሕዝብም ስለሁኔታውም ምን ማለት እንደሆነ ይወቀው፡፡ ከዛ በላይ ግን ምን ተጠቀምን ምን ተጎዳን የሚለውን ግልጽ መኆን አለበት፡፡ ለመራጃው ምንም ቅርበት አንኳን የሌላቸው በተዛባ ሁኔታ የሚያናፍሱት ነገር አገርን ሳይቀር ግምት ውስጥ የሚከት ነው፡፡ በእርግጥ እኔም አዝኛለሁ፡፡ እንዴት እንደ ሰው እንኳን ይጠፋል? እንደ እውነቱ ካምፓኒው ውሉን ያፈረሰው በፓተንቱ ላይ በአስቀመጣቸው የተዛባ መረጃዎች ነው፡፡ በላቦራቶሪ መረጃን ማረጋገጥ ሳያስፈልግ የፓተንት ማመልከቻውን አንብቦ ማንም ከውሉ ጋር የሚቃረን ነገር እንዳለው ይረዳ ነበር፡፡ እንደገባኝ ግን ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ ምን አልባትም በገል ከካምፓኒው ጋር በሚኖር የጥቀማ ጥቀም፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው ሌላ ስህተት ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ ለፖለቲካ ይጠቅማል ብለው አስበው እንዳይሆን እነ አቶ ፍጹም ዛሬ የተዛባ መረጃ በመልቀቅ ሕዝብን በስሜት ሊያግሉት የሞከሩት፡፡ እንዲህ ያለ ቁማር ይቁም፡፡ በዚህ አይነት ኃላፊነት በጎደለውና ሕዝብን በስሜት እንጂ በእውነት መሠረት ላይ ለመምራት አለመቻል አገርን ያወድማል፡፡ አሁን በምናያው ሁኔታ ትውልዱን ከስሜት ያለፈ እንዳያገናዝብ እንዳደረጉት ትልቅ ዋቢዎች አሉ፡፡ የጤፍ ፓተንት መሻር ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው ብሎ አንደም ከኢትዮጵያ ጋር ያለተገኛኘን ጉዳይ እንዲህ ማጮህ ስህተት ነው፡፡ ራስንም ግምት ውስጥ ይከታል፡፡ ቀጥሎም ሎሎች እንደፈለጋቸው እንዲዋኙ ይጋብዛል፡፡  የፓተንቱ ጉዳ ዓለምአቀፋዊ እውቅናን የሚያሰጥ የአንድ አገር በአላት ሀብት ያላትን መረጃ ብቃት ለማሳየት ይጠቀም ነበር እንጂ በቀጥታ ከጤፍ ባለቤትነት ጋር አይገናኝም፡፡ ስለ ሰብሉ ሙሉ መረጃ እንዳለን ቢያውቁ ግን ጤፍን አስመልክቶ ለሚሰሩት ሥራ ሁሉ እኛን ያሳትፋሉ፡፡ ጤፍ ብቻም ሳይሆን ሌሎችንም፡፡ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ የሄደ ቡና እንዲሁ ሌሎች በፓተንት ጉዳይ ሲጨቃጨቁበት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ የሄደ ገብስ የአሜሪካ ገበሬዎችን ገብስን ከማምረት ውጭ ያደረጋቸውን በሽታ ተቋቁሞ ገበሬዎቹ እስከዛሬም ገብስ አምራች ሆነዋል፡፡ ይሄ በአሜሪካ መንግስት ትልቅ ግንዛቤ የተሰጠው ነው፡፡ የቀድሞው ሴናተር አልጎርም በመጽሀፋቸው ይሄንኑ እውነት ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ያለብን ችግር ብዙ ሀብት እጃችን አለ ግን ምንም እውቀቱ የለንም፡፡ መንግስት ተብዬው ዜጎችን የሚደልልለትን ፖለቲካ እንጂ ዜጎችን  የአገሪቱን ሀብት ተጠቅመው ወደተሻለ ኑሮ የሚሄዱበትን ሥራ አይሰራም፡፡ ጭራሽ በየጊዜው ባለስልጣን የሆነ አገር ጎብኝቶ በመጣ ቁጥር ይሄን ነው የሚሰራው እያለ በፖሊሲና ስትራቴጂ የማትንቀሳቀስ የማንም ግለሰብ ሀሳብ መንግስት የሚሆንባት አገር ነች፡፡ ሁሉንም በዘመቻ እንጂ በእቅድ አይሰራም፡፡ እኔ ከዚህ በፊት በሌላ ሀብት አጠቃቀም ላይ በሰጠሁት ሀሳብ ብዙዎች ብዙ ሚሊዬን ብር ሊያገኙ ችለዋል፡፡ የሀሳቡ ባለቤት እኔ መሆኔን የሚያውቅ እንኳን የለም፡፡ ብዙዎች ከእኔ ሀሳብ በተቃራኒ ሞክረው ነበር፡፡ አብይ ሀሳብ ሀሳብ የሚል ብዙ ንግግሮቹን ሰምቻለሁ፡፡ መጀመሪያ ሀሳብ ሊያፈልቁ የሚችሉ ሰዎችን ማወቁ ነው የሚጠቀመው፡፡ ሀሳብ በሚል ማንም እየተነሳ የሚያነሳና የሚጥለው አደለም፡፡ ለምንድነው እኔ የዚህን ያህል የታየኝን የጤፍን ጉዳይ አንድ ሰው እንኳን በጥቂቱ ያልታየው? እንደ እውነቱ ኢትዮጵያ አዳዲስ ሀሳብ የሚያፈልቁ ሰዎች አደጋ ላይ የሚወድቁባት አገር እንደሆነች በራሴም አይቼዋለሁ፡፡ እነ ኒኮላስ ተስላና ቶማስ ኤዲሰን ስኬታማ የሆኑት አሜሪካ ውስጥ ስለሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ ሀሳብ እብደት ነው፡፡ አሁን ራሱ ብዙ ትልልቅ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች በማስተናገድ ፋንታ በጣም የወሮበላ አይነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉን ነው መንግስት ትልቅ ቦታ ሰጥቶ የምናየው፡፡ አሁን ስለጤፍ ሳይሆን ሌሎች ከኢትዮጵያ ጅኔቲክ ሀብት ጋር በተያያዘ ከነዳጅ የበለጠ ገንዘብ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት አንደሚቻል አውቃለሁ፡፡ ዓለም ስለእኛ ጄኔቲክ ሀብት በአግራሞት ነው የሚያወራው፡፡ ከእኛ ጋር መስራት ይፈልጋል፡፡ ግን ማን ትኩረት ይሰጣል? ዓላማው ሁሉ በብጣሽ ፕሮጄክት አበል እየተከፈለው ለመኖር በሆነበት ዘመን ምሁርም ማግኘት ያስቸግራል፡፡ የኢትዮጵያ ጄኔቲክ ሀብት ግን ጠንካራ አቋም ቢኖር በቢሊየን ዶላር ከፍለው ምርምር ሊሰሩና ወደፊትም መታወቅ የሚፈልጉ ብዙ ሳይንቲስቶች አሉ፡፡ የሉሲን አጽም ጉብኝት በሚል ለሌላ አገር አሳልፎ የሰጠ ቡድን እንዲህ ያለ ሀብት እንዴት ይገባዋል? ይቆየን

ልዑል እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን