Source: https://fanabc.com/2019/02/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8B%8D%E1%88%AE%E1%8D%93-%E1%88%85%E1%89%A5%E1%88%A8%E1%89%B5-%E1%8A%AE%E1%88%9A%E1%88%BD%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%8A%A4%E1%88%AD%E1%89%B5%E1%88%AB-%E1%8B%88%E1%8B%B0%E1%89%A6/

On Feb 8, 2019

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የኤርትራ ወደቦችን ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር  የሚያገኛኙ መንገዶችን መልሶ ለመገንባት የ20 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ይፋ አደረገ፡፡

የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ህብረቱ የኤርትራ ወደቦችንና ኤርትራን  ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን መልሶ ለመገንባት የ20 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ያስታወሱት የህብረቱ ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኔቨን ሚምካ፥ የአውሮፓ ህብረት ሁለቱን ሀገራት ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት በማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ለሁለቱ ሀገራት ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

የኤርትራ ወደቦችንና ኤርትራን ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን መልሶ ለመገንባት ፕሮጀክት ድጋፍ  ከህብረቱ የአፍሪካ ትረስት ፈንድ የተገኘ ነው።

ድጋፉ በተባበሩት መግስታት የፕሮጀክት አግልግሎት በኩል እንደሚለቀቅም  ነው መግለጫው የሚያመላክተው፡፡

ድጋፉ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ በመጀመሪው ዙር ለተያዘው ፕሮጀክት ይፋ የተደረገ ሲሆን÷ በሚቀጥሉት አመታት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩትም ነው የተገለጸው፡፡

የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኔቨን ሚምካ በዛሬው ዕለት  ለይፋዊ የስራ ጉብኝት  ወደ ኤርትራ አቅንተዋል።

በኤርትራ በሚኖራቸው ቆይታም ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው በቀጠናው፣ በአውሮፓ ህብረትና በኤርትራ ጉዳዮች ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡