February 9, 2019,አሰፋ በድሉ
ህወሃት ሁሉን ዝግጅት አጠናቋል፡፡ለሶስተኛው ወያናይ፡”ለቀይ ኮከብ ዘመቻ”፡፡
ፖለቲከኛው፤ደራሲው፤ጋዜጠኛው፤ምሁሩ፤ዘፋኙ፤ጡረታ የወጣው ጄኔራል፤ደህንነቱ ሁሉ ጥሪ ተደርጎለት ፤መቀሌ ከትሟል፤ተሳፍሯል፡፡ምናልባት ይህንን ዜና ያልሰማ ቢኖር አቶ ገዱ ሊሆን ይችላል፡፡ነገር ካለቀ ከደቀቀ ይደርሰዋል፡፡በነገራችን ላይ ለገዱ ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡በሁለት ምክንያት፡፡እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ህወሃትን ከውስጥ ሆኖ መድፈርና መጋፈጥ እንደሚቻል ከኦዲፒ በፊት እሱ ይመስለኛል የጀመረው፡፡ከአባይ ወልዱ ጋር፡፡ያ ምሳሌ ለፈጣኖቹ ኦዲፒወች ህወሃትን ለመገዳደር ጥሩ ትምህርት የሰጠ ይመስለኛል፡፡ይሄን የማነሳው ለታሪክ ሽሚያ አይደለም፡፡እንደ ለማ የማደንቀውም፤የማከብረውም የለኝም፡፡ሁለተኛ ገዱን ቀረብ ብለን ካነበብነው ከማንም በላይ ዴሞክራት ነው፡፡እውነት እንነጋገር ከተባለ እንደ አማራ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፌሽናል የመንግስት ሚዲያ አልነበረም፡፡ኦቢኤን ኋላ ላይ ቢቀላቀልም ያው አመጹን ነበር የመራው፡፡ለዚህ የሃሳብ ብዝሃነት ገዱ ቡራኬ ነበረው፡፡የአቶ ንጉሱ አስተዋጽኦ ከኦሮ-ማራ በተጨማሪ እንደተጠበቀ ነው፡፡ሌላው ክፋወች ታውረው አያዩለትም እንጂ አንደ ጠቅላያቸን ቅን ልብ ከታደሉት ነው፡፡
የሆነ ሆኖ የአማራ ህዝብ ከመንግስትም ይሁን በተቃዋሚው ካምፕ በመሪ ድርቅ አንደተመታ ነው፡፡Proactive and Charismatic leader የለም፡፡አሁንም ያለው ድፍረት እንጂ ዕውቀትና ስልታዊ አመራር አይደለም፡፡ልደቱ ብቅ ብሎ ከክህደቱ ጋር ጠፋ፡፡ሌላ እስከ አሁን አላየሁም፡፡ሊታሰብበት ይገባል፡፡ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አማራ ለረጅም ጊዜ የፖለቲካ ድብርት ውስጥ መቆየቱ ይመስለኛል፡፡የትግራይ ህዝብም ከዚያ ተንኮለኛ መለስ በኋላ አርጧል፡፡የሴረኛ ጥርቅም ነው አሁን ያለው፡፡የጌታቸው መጫወቻ ሆኗል፡፡ደቡብ ባዶ ነው፡፡የሚሻለው ኦሮሚያ ነው፡፡ከሶሚሊያ ክልል ግን ለአገር የሚተርፋ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ወደ ህወሃት ልመለስ፡፡ስለ አምሳለ ቀይ ኮከብ ዘመቻው፡፡ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ትንፍሽ እንዳይል ተጠርንፏል፡፡በዚህ ሁኔታ እያለ አንድ ዛዲግ የሚባል ደራሲ ኦሮማይ ቁጥር ሁለትን በ 5 ገጽ አሳጥሮ ደረሰው፡፡ህወሃት ግዑዝ ነው፤አይለወጥም አለን፡፡ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፡፡ራያም ራያ ሆነ፤እናም ኦሮማይ ይልሁሃል ይሄ ነው፡፡ህወሃት ከዚህ በኋላ የሚያካሂደው ማንኛውም መወራጨት እስከ ሞት ድረስ ያለውን ታሪካዊ ሂደት ለማጠናቀቅ ነው፡፡አሁን ጉልበት ያለው ሌላው ጋር ነው፡፡አንድ ድርጅት የቱንም ያህል ድጋፍ ቢኖረው በግማሽ ክፍለ ዘመን ውስጥ እርጅና ግድ ነው፡፡ያ ድጋፍም ቸግሮች አፍጥጠው ሲመጡ መቀጠሉ የሚታይ ይሆናል፡፡
ህወሃትን በምልሰት ለማስታወስ ያህል-
የህወሃት ሳንባ የፈረንጆቹ የከፋፍለህ ግዛው ስልት ነው፡፡ህወሃት መኖር የሚችለው አባትና ልጅን ሳይቀር ለማለያየት በመስራት ነው፡፡የኮለኔል ደመቀ አባትን ማስታወስ ነው፡፡ብዙ አብሮን ቢቆይም ህወሃትን ያጤኑት ጥቂቶች ናቸው፡፡ዛሬ ሁሉም በስሜት ሊያብድ ጓደኞቼ ብዙ ባትሪ አስጨርሰውኛል፡፡የኦሮሞም የብቻ ትግል ፍሬ አልባ መሆኑን ልብ ያሉት ፕ/ር መራራ የሚጋጩ ህልሞች በሚለው መጽሃፋቸው ህልሞቻችንን ማቀራረብና በጋራ መቆም ትግሉ የሚጠይቀው ዕውነት መሆኑን መግለጻቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ይህንኑ ሰሞኑን ፓርቲወች መድረክ ጽሁፍ ሲያቀርቡ አንስተውታል፡፡ነውጤ ቢሆኑም ከመድረክ እንዳይጠፋ ከምፈልጋቸው ውስጥ ናቸው፡፡በነገራችን ላይ ሰሞኑን የሙሉ ፕ/ር ማዕረግ ስላገኙ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለወት እላለሁ፡፡ እናም ከ27 ዓመት በኋላ በመጨረሻ ጣና ኬኛ ተወለደና ሃሳቡን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ገዝተውት በአንድ ላይ በመቆም ህወሃት ቢያንስ ክፋ ስራውን ወደ ጀመረበት ምሽግ እንዲመለስ ተገዷል፡፡
እንደተባረረ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ዕርቅ አዲስ አበባና መቀሌ እያምታታ፤የትግራይ ህዝብ ሳይመክር፤ወዘተ…በማለት ሊያውክ ሞከረ፡፡አልተሳካለትም፡፡የኤርትራውን ትይንት ከአየ በኋላ ደግሞ እንደ ለመደው የማጭበርበሪያ የድጋፍ ሰልፍ ጠራ፡፡ለብቻውም ግንኙነት ሞከረ፤የኤርትራ ቲቪ አንዲዘግበው፤ደብዳቤ በመጻፍ፡፡ኢሳያሥ ዕኛ ግንኑነታችን ከኢትዮጵያ ጋር ነው አለ፤ተባለ፡፡ከዚያ በኋላ የተንጠለጠለው ህገ-መንግስት ተጣሰ በሚል አብዲ ኢሌን ማትረፍ ነበር፤ይህም አልተቻለም፡፡በአፋር በኩል ሞከረ በደንብ ከሸፈበት፡፡ከዚያ በኋላ የቀረው ስፖንሰር የሚያደርጋቸውን ግጭቶች በማሳያነት በማንሳት የአብይ መንግስት አቅም የለውም በማለት አቶ በረከትን ጥናት አቅራቢነት ሾሞ አለመረጋጋቱን ማስቀጠል ነው፡፡ግንሹመቱ ሹመት ሆነ ቀረ…
በሃዋሳ ኢህአዴግ ጉዳኤ አብሮ አቅጣጫ የሰጠበትን የወሰንና የማንነት ኮሚሽን እውነት ሆኖ በተግባር ሲቋቋም አበደ፡፡ዛዲግ ደግሞ መጨረሻ ላይ ህወሃት የሰወች ስብስብም እንደሆነ በሚጠቁም መልኩ የኦሮማይን የመጀመሪያ ገጽ ሲገልጥ ተቃጠለ፡፡ እናም ኮሚሽኑ ስራውን ሳይጀምር ህወሃት ከቅማንት ኮሚቴ ጋር ስራውን በይፋ ጀመረ፡፡ይህንን በማድረግም ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹን ገብሮ ያመጣውን የዴሞክራሲና የነጻነት አየር በማጠልሸት ለማክሸፍ ያለ የሌለ ሃይሉን በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡በኋላ እኔ የለሁበትም ፤አልተሳተፍሁም ለማለት እንዲመቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽኖ በማሳደር አንዳንድ የኮሚሽኑ አባላት ራሳቸውን እንዲያገሉ እያደረገ እንደሆነ እየተዘገበ ነው፡፡ህገ ወጥ በሆነ ሁኔታ የክልሉ ም/ቤት ፤ በተወካዮች ም/ቤት አዋጅ ላይ ድምጽ እንዲሰጥበት የተደረገው፤በውስጠ ታዋቂ ተግባራዊ እንዳይሆን አስፈጻሚው ማንኛውንም እርምጃ እንዲወስድ ስልጣን ሰጥቶኛል ለማለት መሰለኝ፡፡ዕኛ አልገባን አለ እንጂ እነሱ እንደ ሉአላዊ አገር እየሰሩ ነው፡፡ይህ ደግሞ ህገ መንግስታዊ ስርዐቱን አደጋ ላይ መጣል ነው፡፡
ምስጋና ለወገኔ ዛሬ ትግራይ ኦን ላይንና አይጋ ፎረም ብቻ አደሉም ጎግል ውስጥ ያሉት፡፡እነሱ ዛሬም አሉ፡ተልኮ ቀይረው፡፡ኢሳት ክሊክ ሲደረግ ያ አስጠሊታ ዲስፕሌይ ዛሬ የለም፡፡ሰውም ብዙ አወቀ፤ሃሳብ ተለዋወጠ፡፡አጠቃቀማችንም የበለጠ ደግሞ ይሻሻላል፡፡ ብዙሃንም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፡፡የተለያየ ሬዲዮ፤ቲቪ፤ማህበራዊ ሚዲያ ወዘተ….ነጻ ነን፡፡አስታውሳለሁ የኦሮሞ ወጣቶች ሲረግፋ፤የአማራ ልጆች ግንባራቸውን ሲባሉ ፌስ ቡክ አይዘጋም ነበር፡፡የእነሱ ሰው በስህተት መረጃ እንኳን ተነካ ከተባለ ፌስቡክ ወዲያው ይዘጋ ነበር፡፡የወለጋውን ኬዝ የሚያስታውስ ካለ…፡፡ሌላው ዜጋ ጥበቃ አይደረግለትም ነበር፡፡ዛሬ ለሁሉም እኩል ይዘንባል፡፡ደስ የማይሉ አዝማሚያወች ግን አሁንም አሉ፡፡ጃዋር ባክህ ረፍ! ይህንን ነጻነትና ዴሞክራሲ ለመቀማት ነው ወንጀል እየሰሩ ያሉት፡፡ይሄ ነገር በምንም ተአምር መፈቀድ የለበትም፡፡ህወሃት ቀይ መስመር ሊሰመርለት ይገባል፡፡ብርሃን አይተን እንደገና ወደ ጨለማ እንዲመልሰን መፈቀድ የለብንም፡፡
የአማራ ክልል የጸጥታና ሰላም ቢሮ ሃላፊ ብ/ጄ/ አሳምነው ጽጌ በ30/5/2011 ለኢሳት አንደገለጹት ከሆነ ሁለት አማራ በብዛት የሚኖርባቸው ቀበሌወች ወድመዋል፡፡ለዘመናት አብረው የነኖሩት ቅማንትና አማራ ተሰደዋል፡፡እድሜ ለህወሃት፡፡ይሄ ነገር የሁለት ክልሎች ጉዳይ የመሰለው ካለ ትናንትን ረስቷል፡፡አማራ ለራሱ መሆን አያቅተውም፡፡ግን ጉዳዩ አራት ኪሎንም መነቅነቁ አይቀርም፡፡ስለሆነም የሁሉም ነው፡፡
ቀጣይ እርምጃ
ከጠቅላያችን
1ኛ፡ወንጀለኞች ወንጀል በሰሩበት ቦታ እንዲዳኙ ክልሉን በይፋ ትዕዛዝ መስጠት፡ይገባቸዋል፡፡Your Excellency you are Commander in chief ፡፡አልታዘዝም ካለ ህገ መንግስታዊ ስርዐቱን አደጋ ላይ ስለ ጣሉ ያለ ክልሉ ፈቃድ የፌደራል መንግስት ጣልቃ መግባት ይችላልና አድኖ መያዝ አለበት፡፡ጠቅላያችን ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆመው ማውረድ ሲያቅተወት እያየን ነው፡፡ህወሃትን ራስወ ተራራ አሳከሉት፡፡በጣም መረዳት ተቸግረናል፡፡የባለፈው የፓርላማ ራሱን አሰረ የሚለው ንግግር ሁሉም በአንድ አፍ የተቸው ስለሆነ እሱን በሚያርም መልኩ ቆፍጠን ያለ ትዕዛዝ ማስተላለፍ አለበወት፡፡ለህዝባችን ያልሆነ ስዕል ዕየሰጡ ነው፡፡እንደ ዘመናዊ መሪ ነው የማናየወት እናም ህዝብም የማዳመጥ ግዴታም አለበወት! ምስጢር ሆኖብናል፡፡
2ኛ፡ የቅማንት ጉዳይ ከቁጥጥር እየወጣ ነው፡፡ለክልሉ ብቻ ባይተውት ጥሩ ነው፡፡ውሎ አድሮ የመንግስትወን ስም የሚያጠይም ነው፡፡ቁጥራችን አናሳ በመሆኑ ዘር ማጽዳት ተካሄደብን ብሎ ህወሃት የለመደውን ዶክመንተሪ አስይዞ ሌላው ቢቀር አለማቀፍ ሚዲያ መላኩ አይቀርም፡፡የአገር ውስጡን እየሰራ ስለሆነ፡፡ስለሆነም መከላከያ ጭምር ታክሎበት ሕወሃት ከዚያ አካባቢ ዝር እንዳይል መደረግ አለበት፡፡ከነዋሪው ጋርም ተደጋጋሚ ቀጥተኛ ውይይት ማድረግ ይገባል፡፡ተላላኪወችም ከህዝቡ የሚያገናኛቸው ድልድይ መሰበር አለበት! እነሱም በቁጥጥር ሊውሉ ይገባል፡፡በዚህ ረገድ የተገኘ መረጃ ካለ ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ጠቀሜታ አለው፡፡ገበሬ በሞርታር ሲዋጋ እንደተገኘ፤ማሰልጠኛ ቦታወች እንደተገኙ የክልሉ መንግስት ሃላፊወች መግለጻቸውን ማስታወስ እወዳለሁ…
3ኛ, ህወሃት የወሰን ኮሚሽኑን ስራ በይፋ በም/ቤት ተቃውሞ የጦርነት ዝግጅቱን አጠናቆ ስራውን ጎንደር ላይ ጀምሯል፡፡እነ ዛኢድና መሰሎቻቸውን ማበረታታት ለነገ የማይባል ነው፡፡ህወሃት እንደ ድርጅት 6 ሚሊዮን ህዝብ አሳፍሮ ወደ ገደል እየተንደረደረ ስለሆነ፤ሚሊዮኖችን ማዳን ግድ ይለወታል፡፡የሁሉም መሪ ነወትና፡፡ ይህ ወንጀሉ በመረጃ በየበታው ከሚያካሂደው የሽብር ወንጀል ጋር በመረጃ ተደግፎ ለህግ የሚቀርብበት ሁኔታ ካልተመቻቸ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ማራመድ አይቻልም፡፡
ከኢትዮጵያ ህዝብ
1ኛ፡ህወሃትን ወደ ዳር የገፋነው በጋራ በመቆማችን ነው! የተገኘውን ነጻነትና ዴሞክራሲ ሊቀማን በቅማንት በኩል እየገዘገዘን ይገኛል፡፡የትግራይን ህዝብም 3ኛው ወያናይ በማለት ለሌላ ዙር ጦርነት እያዘጋጀው ነው፡፡የአሁኑ ፍጹም የተሳሳተ ስሌት ነው፡፡በህወሃት ቤት ደርግን የጣሉት እነሱ ናቸው፡፡እናም ቅዠቱ ያንን እንደግማለን ነው፡፡ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ነው፡፡እሱ የሚታይ ይሆናል፡፡እናም ይህን ህዝብ ዋጋ ሊያስከፍሉት ነው፡፡ይሄንን ለማወቅ የጦር መሪ መሆን አይጠይቅም፡፡እናም ጠቅላያችን ላይ ጫና ማሳደር አለብን፡፡እንዴት ነው ወንድ ልጅ ሲያኮላሽ ፤እግር ሲቆርጥ የኖረ ወንጀለኛ አልሰጥም የሚባለው? በዚህ ጉዳይ ጠቅላያችን ፊት ሰጥዋል፡፡እናም ልክ እንደ ሰኔ 16ቱ ያለ መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ “ህወሃት፤ጌታቸው አሰፋና ሌሎች ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ” የሚል ሰልፍ ተደርጎ ተጎጂወች ፍትህ ማግኘት አለባቸው፡ህወሃትም ልኩን አውቆ ኦሮማይ ይታወጅ!
ድል ለዴሞክራሲ
