ሐዋርያ
ልዩ ዕትም፤
ነሐሴ 2010 ዓ.ም (August 2018)
ልብ ያዳምጣል፤ ልብ ይናገራል;

እያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ ብዙኃን ነው። ማህበራዊ ግንኙነቱንና አካባቢውን መርምሮ ከእሱነቱ ጋር በምልዓት የሚግባባበትና የሚረዳበት የራሱ መዝገበ-ቃላትና ቋንቋ አለው። የጥበብና የዕውቀት መለኪያውም ይህን ረቂቅ የሆነንና በእያንዳንዱ ሰብ ህሊና ውስጥ የተቋጠረን ግላዊ እሳቤና እውነታ ተንትኖ በማጤን አጠቃላይ ማህበራዊ አንደምታ በመስጠት አነጻጽሮና ደምሮ መተርጎም መቻሉ ነው።

ተቀድቶ ከማያልቀው የሰው ልጅ የአእምሮ ባህር ላይ ስለ ህልም ወይም ራዕይ የተጨለፈ ሚስጥር ቢኖር በህልም ውስጥ ሊገለጽና ሊጨበጥ የሚችል እውነት መኖሩን ነው። ጥያቄው ግን፤ ‘በእውናችን አስበን የተረዳነው ነገር ህልም እየሆነ ነው፤ ወይስ ህልም ከሰው ልጆች ሩሓዊ የማሰብ ችሎታ በላይ ከጥሬ ሃሳቦች ላይ ተፈልቅቆና ተቀናብሮ የተፈጠረ እውነታ ነው’ የሚለው ነው። በቀኑ ተግባራዊ ውሏችን በዐይናችን በጎና ክፉውን እያዬን፤ አንዳንዴም ከህሊናችን ጋር የተጣረሰውን እየፈጸምንና አያስፈጸምን ስንቀሳቀስ እንውልና የህይወታችን ዝኃ የሆነው ህሊናችን ደክሞና ዝሎ ስንተኛ በእንቅልፋችን ዓለም ከህልማችን ጋር ቆይታ እናደርጋለን።

በህልማችን የውስጣችን እፀጽ እያየን ወይም የፈራነው እየደረሰብን ከሚያስጨንቀን ስሜትና ሌላ ጊዜ ደግሞ ደስ ከሚለውና ከሚያባብለን ህልማችን ጋር ቆይታ አድርገን ስንነቃ ብዙዎቻችን ባሸለበ ስብዕናችን የታዬንን በነቃ ግንዛቤያችን ትርጉም ሰጥተን ልንፈታው እንሞክራለን። አንዳንድ በውስጣችን የመዘኑ እሳቤዎች አልፎ አልፎ ድንገት እውን ሲሆኑ ቀደም ብለን ያብሰለሰልነው የእንቅልፉ ዓለማችን ጣፋጭ ህልም ከህይወታችን የጋለ ፍላጎትና የማሳካት ብርቱ ጥረት ጋር ይቀናጅልንና “ታእምር ተፈጠረ!” ያሰኘናል። ከዚህም አንጻር ነው ዛሬ በኢትዮጵያችን ነግሦ ያለው ሁኔታ ቁመን በእውናችን በተራዘመ ትግል የፈተነውንና በእዝነ-ልቦናችን ስንመኘው የኖርነውን፤ ተኝተን ደግሞ በምናባችን ከራሳችን ጋር የተጫወትነውን ስሜት ልንዳስሠው በምንችል ሁኔታ ፊታችን ላይ ደቅኖብን እንዲህ የሚያቅበጠብጠን።

በእርግጥም የተስፋ ድምጽ ይሰማል፤ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ደምቃለች። ድቅድቁ ጨለማ ሰማይ ላይ ባንዣበበች ሙሉ አግማስ ጨረቃና ከአድማስ አድማስ በሚወረወሩ የክዋክብት ብርሃን ጸዳል ተጋርዷል፤ እየነጋና ፀሐይ ልትወጣ ለመሆኑ የወፎች ዝማሬና ከአድማስ የሚታየው ወጋገን ምልክት ነው። እነዚህ የተፈጥሮ ጸጋዎች በጊዜ ውስጥ ይኖራሉ። ይሄዳሉ ይመጣሉም። ይሁን እንጅ ፈጣንና ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ተፈጥሯዊ ሚናቸውን እንዳይወጡ ሊያውካቸው ይችላልና የለበሙ ፈጥነው ይገሰግሱባቸዋል፤ ሠርተውምም ያፈሩባቸዋል። በዚህ የተጉም ከዘላለም ማህበራዊ ባርነትና ቅስም ሠባሪ ድህነት ነጻ ሊወጡ ይችላሉ። የሰውን ልጅ ባህርይ ላልተላበሱ ፍጥረቶችና እንዝላል ለሆኑ የሰው ልጆች ደግሞ እነዚህ ተፈጥሯዊ ኩነቶች ሲደርሱ የሚደምቁባቸው፤ ሲያልፉ ደግሞ ጠውልግው ወደ ድይናቸውና ቅጥቃጤያቸው የሚገቡበት ማቆሚያ የለሽ አዙሪት ይሆናል። ይህንም ስናስብ ዛሬ በኢትዮጵያችን አዲስ የፖለቲካ ቅኝትና አቅጣጫ መጀመሩ ሃቅ ነው። በዚህ አዲስ ጅምር ውስጥ የሁኔታዎችን መነሻና አቅጣጫ መርምሮ መረዳትና ዘላቂነት ወዳለው አስተማማኝ ግብ መድረስ እንዲቻል ፈጥኖ የበኩልን አስተዋጽዖ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አጋጣሚ ነው።
የሀገር ግንባታ በቀጣይነት የሚሠራ ታሪክ ነውና በየአጋጣሚው ተሠርተው የሚገኙ ጡቦችን ማጠራቀምና ማቀበል ሃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ተግባር መሆን ይኖርበታል።

በሀገራችን የተጀመረው ፖለቲካዊ የመፍትሄ ሂደት ለየት ባለ አቀራረብና አካሄድ ከደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ሥነ-መንግስታዊ ሥርዓት ማክተሚያ ሂደት ጋር የሚመሳሰል ባህሪዎች ያሉት ይመሳሰላል። እንደሚታወቀው የከረመው የሀገራችን ፖለቲካዊ ጣጣ ነጭና ጥቁር ተብሎ አይፈረጅ እንጅ፤ ኢትዮጵያዊያን በሥርዓቱ አራማጆች አመካይነት ከዜግነት መገለጫቸው ውጭ በማንነታቸውና በቋንቋቸው ተለያይተው፤ በአሰፋፈራቸውና በእንቅስቃሴያቸው ተገትተው እርስ በርሳቸው አልቃሽና አስለቃሽ ሆነው እንዲቆዩ መደረጉ የሚካድ አይሆንም። ይህ የብዙዎቹን ህሊና እያደማ፤ በሥጋና አጥንታቸው ፋፍቶ የቀጠለ አስቀያሚ የፖለቲካ ስሌት ከውስጥና ከውጭ ባጋጠሙት ፈታኝ ቅራኔዎችና ተጋድሎዎች እንዳሰበው በዘለቄታ መቀጠል አለመቻሉ የተረጋገጠ ሆኗል። በደቡብ አፍሪካም እንደተስተዋለው የአፓርታይዱ ዘረኛና ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት መሪዎች ከዚያ ሁሉ አስቀያሚ የአስተዳደር ሥርዓታቸው በሁዋላ፤ ሰቆቃ የዋጀውን የግፍ ሥርዓት ለመለወጥ ሥልጣናቸው ላይ እንዳሉ ዋና ተጫዋች ሆነው ወጡ። በእንቅስቃሴው ጅምር ላይ በግፍ ያማቅቋቸው የነበሩትን የፖለቲካ እሥረኞች ከእሥር ፈቱ። ታዋቂው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላም በጉልህ ከሚታወቁት ታጋዮች መካከል በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው። እኒህን ታላቅ የፖለቲካ ሰውና የትግል ባልደረቦቻቸውን አካተው ደቡብ አፍሪካን ይመሩ የነበሩ ነጮች በታሪክ ምእራፍ ላይ ተመዝግቦ ያለፈውን የሰላምና እርቅ ሂደት ጀመሩ። ከትውልድ ትውልድ ተሻግሮ ሲወሳ ለሚኖር መልካም አርዓያነት በመድፈራቸውና በመትጋታቸው፤ እንዲሁም ደግሞ ለዚህ የተቀደሰ እንቅስቃሴያቸው ከሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ ስለተቸራቸው ህልም የነበረውን እውን አድርገው አረጋግጠዋል። ዛሬስ ያን መሰሉ የደቡብ አፍሪካ ታሪክ በእኛዋ ሀገር በኢትዮጵያችን ለእኛ በሚገባንና በሚያመቸን መንገድ ሊከሰት ይሆን? ከደቡብ አፍሪካው የመፍትሄ አውድ ጋር ጎን ለጎን ሊሄድ የሚችልና የኢትዮጵያ ‘ስልት’ ተብሎ ሊጠራ የሚችል የሰላም ማፍለቂያ ጽንሰ ሃሳብ ልናበረክት ቢሆንስ?

የሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ጥፋቱ እንጅ ልማቱ ብዙም አይታወቅም። በሀገራዊ ሃሳብ የተነሳ ከመጠላላት እስከ መጋደል መበርታታችን ሚስጥር አይደለም። እስከዛሬም ይኸው ባህርያችን በአመዛኙ እንደተጠናወተን አለ። አገር የእያንዳንዱ ዜጋ አይደለች ይመስል አብዛኞቹ ተደራጅተውም ይሁን በግል ስመ-ጥር ሆነው አቅም ያገኙ ሁሉ የሀገሪቷ ባለቤትና አሳቢዋ እነሱ ብቻ እየመሰሉ ብዙኃኑን ከምክክር ሲያገሉት፤ ከተሳትፎ ሲነፍጉት ከማየት በላይ እንደ አላዋቂ መቁጠራቸውም ትልቁ ወንጀል ሆኖ ኖሯል። በሀገር ጉዳይ ላይ እርስ በእርስ ጥርጣሬንና ፍርሃትን ማንገስ ከግብዝነትና ካለመረዳት እየተደረገ ይሆናል እንጅ ከዚያ ውጭ የለየለት የጠላትነት ምግባር ነው። “እባብ ያየ በልጥ ደበየ” የሚለው ዘይቤያችን አስተምህሮቱ ቦታና ጊዜ ሊኖረው ቢገባም፤ ዛሬ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደ ግለሰብና ህብረተሰብ በህዋሳቶⶫችን እየሰማን፤ እያዬንና እዬዳሠስን ከምንገነዘበው እውነታ ውጭ አባባሉን ከተረዳነው ግትሮች ያስብለናል። እንደ ዜጋ ግራ ቀኙን እየፈተሹ በቅን መንፈስ መወያየቱና ውጤቱን በጊዜ ሂደት ውስጥ መፈተን ምንጊዜም አስፈላጊ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ስህተት የሚሆነው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደሚታሰብ ዘላቂ ሕዝባዊ ድል ደረጃ በደረጃ ለማሸጋገር የበኩልን አስተዋጽዖ ከማድረግና አጋጣሚውን ከመጠቀም ይልቅ በተለመደ አዙሪት ውስጥ የመሽከርከሩ ፍሬ አልቦ ወትግል ነው። እያንዳንዱ ዜጋ፤ የሀገሪቱ ምሁራንና ፖለቲካውን ጨምሮ በልዩ ልዩ የዓላማ አውታሮች ላይ የተደራጁ ክፍሎች ሁሉ፤ ይህ አመች ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይዳከምና እንዳይቀለበስ ዋስትና ለመስጠት የማይቻለውን ሁሉ ለማድረግ መድፈር ያለባቸው ወቅት አሁን ነው። በአርቆ አሳቢነትና በይቅር ባይነት ያለፈውን የፍዳ ዘመን ምእራፍ በይቅርታና በምህረት ዘግቶ አዲስ የቃል ኪዳን ምእራፍ መጀመር የዚህ አሻጋሪ ትውልድ ሊከፍለው የሚገባ እዳው ሊሆን ይገባል። ፍላጎቱ ካለ መንገዱ አይጠፋምና፤ ‘ይህን አደርጋለውሁ’ ከሚለው በጎ ምግባር በላይ ‘ምን እናድርግ’ በሚለው የጋራ መፍትሄ ላይ መረባረብ ለዘለቄታዊ ውጤት ዋስትና ነው።

ሌላው ትልቅ ቁምነገር ደግሞ፤ ነጻና ጠንካራ የሆኑ ተቋሞች በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ በሀገራችን እንዲፈጠሩና እንዲያብቡ መሪ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል። እያንዳንዱ ዜጋ ይህን ጉዳይ የእኔ ብሎ ሊያበረታታና ሊደግፍ ይገባዋል። ያለ ጠንካራ እና ነጻ ተቋሞች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሀገር ደረጃ ለመንገንባት ማሰብ ህልም እንጅ እውን እንደማይሆን ሁሉም ሊረዳው ይገባል። የአንድ ዜጋ ክቡርነቱ በራሱ አስቦ፤ ከራሱ ጋር ተማክሮ በነጻነት አቋሙንና እምነቱን ማንጸባረቅ መቻሉ ነው። ይህን መብቱን ለማስጠበቅ ደግሞ ጋሻ የሚሆኑት የእሱው ሙሉ ድጋፍ የማይለያቸው ዙሪያውን የሚያጅቡት ነጻ ተቋሞች ናቸው። “ተስፋ በጠፋበት ቅድስና” እንዲሉ፤ ባለፉት ብዛት ያላቸው ዓመታት ከሀገራችን ርቀን በዓለም ላይ እንደ ጥሬ ተዘርተን ሥንኖር፤ አድገዋል ከሚባሉት የምዕራብ ሀገሮች ውስጥ የተማርነው ትልቅ ሚስጥር ቢኖር፤ የሥርዓቱን ሚዛን የሚጠብቁ ነጻና ጠንካራ ተቋሞች መኖራቸው ነው። እነዚህ ነጻ ተቋሞች አገልግሎታቸው እንደተቁቋሙበት ባህርይ ቢለያይም ዋና ዋና የወል ባህሪያቸው ሆኖ የሚገኘው ሀገራዊ ህግ እንዳይጣስ በያሉበት ዘብ መቆማቸው፤ ሕዝብ ስለ ሀገሩ ሁለገባዊ ጉዳይ አውቆ የመደገፍና የመቃወም መብቱን ማስከበራቸው፤ ሕዝብ መሪዎቹን የመምረጥና የመጣል ያልተገደበ መብትና ሥልጣን እንዳለው አውቀው ዘብ መቆማቸው … የመሳሰሉት ይገኙበታል። አሁን በሀገራችን ለተጀመረው የሰላም እንቅስቃሴ ዘለቄታ ስኬት በየደረጃው በነጻ የሚንቀሳቀሱ ሁነኛ ተቋሞች ማበብ ይኖርባቸዋል። ሰበሰብን ብለን እንዳንበትንም ህግና ደምብ ባለው መንገድ የሀገርንና የሕዝብን አንድነት በጠበቀ ሁኔታ ሁሉም መብቱንና አግዴታውን ተረድቶ የሚሳተፍበትን መደላድል ማመቻቸት ያስፈልጋል። በግለሰብ ደረጃም እያንዳንዱ ዜጋ ከብዙ ምኞቱና ፍላጎቱ ጋር የሀገሩ እኩል አባወራ እንዲሆን በነጻ አስቦ በነጻ የሚሰጥበትን ዕድል ማጎናጸፍ ይገባል።
መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን፤
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ልታገኙን ለምትፈልጉ፦
hawarya.services@gmail.com