4ኛው ዙር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሕዝብና ቤት ቆጠራ የካቲት 29,2011ዓ.ም. እንደሚጀምር ተነግሯል፡፡ ይሄ ቆጠራ በዘመነ ወያኔ ከተደረጉት ሁለት የተጭበረበሩ ቆጠራዎች በባሰ መልኩ ሊጭበረበር እንደሚችል ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡
የጥርጣሬየ ምንጭም በዋናነት ከከረምንበት በባሰ መልኩ በአሁኑ ጊዜ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ የሆነ ብሔራዊ መግባባት (national consensus) የሌለን መሆኑና ነገሮች መሬት ላይ ባለው እውነታ ላይ ተመሥርተው ሳይሆን ሥልጣን በጨበጠው ኃይል ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ውሳኔ የሚፈጸሙ መሆናቸው የተባባሰበት ወቅት ላይ ያለን በመሆኑ ነው፡፡
ከዓመታት በፊት ማሳያዎችን በመጥቀስ “ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት አየር ትክክለኛ ቆጠራ ቢደረግ ያለአንዳች ማጋነን የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ቁጥር ይዞ ይገኛል!” ብየ ተናግሬ ነበር፡፡ በዚያ ጽሑፍ ላይ የአማራ ሕዝብ ቁጥርን ከትክክለኛው ቁጥሩ አሁን ባለበት ደረጃ ቀንሶ እንዲገኝ ያደረጉት ነጥቦች ብየ ከጠቀስኳቸው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ከሆኑት ምክንያቶች አንድ አንድ ልጥቀስ፦
እንደምታውቁት የደርግ አገዛዝ ወድቆ የወያኔ አገዛዝ እንደተተካ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ላይ መዘመቱና ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ መጨፍጨፋቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያም በኋላ አማራ በመላ ሀገሪቱ እንደአውሬ እየታደነ በምን ዓይነት አስከፊ ሁኔታ እንዳለፈ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
ይህ በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የኖረ አስፈሪ የዘር ማጥፋትና ተያያዥ ጥቃት በርካታ የአማራ ተወላጆችን እራስን ከዚህ ጥቃት ለማዳን ሲሉ አማራነታቸውን ቀይረው በየሚኖሩበት አካባቢ ያለውን ብሔረሰብ ማንነት ይዘው “ኦሮሞ ነን፣ ትግሬ ነን፣ ጉራጌ ነን፣ ሲዳማ ነን፣ ሀዲያ ነን!” ወዘተረፈ. እንዲሉና ከማንነታቸው ጋር እንዲራራቁ አስገድዷቸዋል ወይም አድርጓቸዋል፡፡ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሚጠራው የሀገራችን ክፍል ብቻ ከሰባት እስከ ዐሥር ሚሊዮን የሚሆኑ አማሮች በሁኔታዎች ተገደው ማንነታቸውን እንዲቀይሩና ያልሆኑትን እንዲሆኑ ማድረጉ ሲሆን፡፡
ወደ ማኅበራዊው ምክንያት ሳልፍ ደግሞ አማራ በባሕሉ ልጅን መቁጠርና ማስቆጠር የማይወድ መሆኑ ነው፡፡ እንኳን ልጆቹን ከብቶቹን እንኳ መቁጠርና ማስቆጠር አይወድም፡፡ ግድ ቢሆንበት እንኳ ዐሥር ልጆች ያሉት ስድስቱን ትቶ አራት ናቸው ይላል እንጅ ዐሥር ልጆች አሉኝ አይልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሴቶችን ከነአካቴውም ያለመቁጠር ልማድ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ከአማራ ሕዝብ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆነው የሚኖረው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህ ባሕል ያለው የገጠሩ ነዋሪ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ በእንዲህ ያለ ባሕላዊ አመለካከት ታስሮ ባለበት ሁኔታ በሚሰጠው የተሳሳተ መረጃ ነው እንግዲህ አማራ ተቆጠረ የሚባለው፡፡ በከተማም ቢሆን እንዲህ የሚያስበው አማራ ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይገመታል፡፡
“አሁን በሚደረገው ቆጠራ እነኝህ ችግሮች ፈተና አይሆኑም ወይ?” ከተባለ መጀመሪያ ላይ የጠቀስኩትን ችግር በተመለከተ የተለወጠ ነገር ስለሌለ እንዲያውም በባሰ ሥጋት ላይ ያለ ስለሆነ “ኦሮሞ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ጉራጌ ነኝ፣ ሲዳማ ነኝ፣ ሀዲያ ነኝ!” ወዘተረፈ. ብሎ የሚኖረው አማራ ወደ ማንነቱ ተመልሶ “አማራ ነኝ!” ይላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በተለይም ኦሮሚያ በሚሉትና በወልቃይት በራያ የሚኖሩ አማሮች፡፡ በነዚህ አካባቢዎች እንኳንና ቀደም ሲል ጀምረው ማንነታቸውን የቀየሩት ቀርቶ አማራ ነን ብለው ለቆጣሪዎቹ መረጃ መስጠት ለሚፈልጉትም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሚፈቀድላቸው አይመስለኝም፡፡
ማኅበራዊውን ምክንያት በተመለከተም እስከአሁን ባለው ጊዜ ችግሩን ለመቅረፍ ምንም የተሠራ የንቃት ሥራ የለም፡፡ በመሆኑም የአማራን ቁጥር ለመቀነስ ከሚሠራው አሻጥር በተጨማሪ እነኝህ ሁለት ችግሮች አሁንም የአማራ ትክክለኛ ቁጥር የሚታወቅ አይሆንም የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
የአሁኑ ቆጠራ ደግሞ ቆጠራው የሚኪያሔደው እንደ ቀድሞው በወረቀት መዝገብ ሳይሆን ታብሌት (ሠሌዳ) በሚሉት የእጅ ስልክ (መናግር) መሰል መሣሪያ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሕዝቡ በአግባቡ መቆጠሩንና የሰጠው መረጃ በአግባቡ መመዝገቡን ማረጋገጥ የሚችልበትን ዕድል አይሰጥም፡፡ ይሄ መሆኑም ከባድ ሥጋት ፈጥሮብኛል፡፡
ቆጣሪዎቹ አምና በዚሁ መሣሪያ የቅኝት ቆጠራ አድርገው ነበር፡፡ ተቆጣሪው ዜጋ መረጃ ይሰጣል እንጅ “የሰጠሁትን መረጃ በትክክል መዘገበው ወይ?” ብሎ ለማረጋገጥ የሚችልበትን ዕድል አይሰጥም፡፡ የከዚህ ቀደሙ ግን የወረቀት ቅጽ ስለሆነና በግልጽም ስለሚታይ ተቆጣሪው የሰጠው መረጃ በትክክል ለመመዝገቡ ማረጋገጥ የሚችልበት ዕድል ነበረው፡፡ የሰጠው መረጃ በትክክል መመዝገቡን አረጋግጦም መዝገቡ ላይ የሚፈርምበት አሠራር ስለነበር፣ የወረቀቱም ቅጽ ተከታታይ ቁጥር (serial number) ያለው ስለነበር ቆጣሪው ሸፍጥ ቢያስብ እንኳ ሰነዱ ሊጠፋ እንደማይችል ለተቆጣሪው መተማመንን የሚፈጥር ነበር፡፡ ችግሩ ያለው ከላይ በመሆኑ ማጭበርበሩን መከላከል አልተቻለም እንጅ፡፡
ያኔ የነበረው ችግር ቅጹ የሚሞላው በእርሳስ መሆኑና ቆጣሪው ተንኮል ካሰበ አጥፍቶ ሌላ መረጃ ሊሞላ የሚችልበትን ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ነበር፡፡ በእርሳስ የሚሞላበትን ምክንያት ሲገልጹ ቅጹ ሲሞላ ስሕተቶች ስለሚፈጠሩ ሰነዱን ከስርዝ ድልዝ ለመጠበቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ሁለቱንም ችግሮች ቅጹ ተሞልቶ ከተጠናቀቀና ተቆጣሪው ዜጋ ፊርማውን ካኖረ በኋላ እዚያው ላይ የእርሳሱን ጽሑፍ በእስክርቢቶ ጽሑፍ በመቀየር መቅረፍ ይቻል ነበር፡፡
የአሁኑ አመዘጋገብ ግን በኤሌክትሮኒክ (በነርኃላዊ) መሣሪያ በመሆኑ በዚህ ላይ ደግሞ እኔ እንደታዘብኩት ወያኔ የአማራ ክልል በሚለው የሀገራችን ክፍልና በአዲስ አበባ ቆጣሪ ተብለው የተመደቡት ትግሮችና ካድሬዎች በመሆናቸው ማጭበርበሩ በቆጣሪ ደረጃም ሊደረግ የሚችልበትን ሰፊ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በአዲስ አበባና በአማራ ክፍላተ ሀገር ቆጣሪዎቹ ትግሮችና ካድሬዎች መሆናቸው ፈጽሞ የአጋጣሚ አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ በሌሎችም አካባቢዎች ቆጣሪዎቹ ከካድሬዎቹ የሚወጣ አይመስለኝም፡፡
የቆጠራው ውጤት ማጭበርበር የሚፈጸምበት ቁጥር በመቀነስ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ቁጥር በመጨመርም ማጭበርበር ይፈጸማል ብየ እገምታለሁ፡፡ ቁጥር በመጨመር ማጭበርበር ይፈጸምበታል ብየ ከምገምተው የቆጠራ ውጤት ዓይነቴዎች አንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ቁጥር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ቁጥር ባለፈው በ1998/99ዓ.ም. በተደረገው ቆጠራ ሬሾውን በዐሥራአንድ ሚሊዮን (አእላፋት) ቀንሶ ነበር የተገኘው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የመናፍቃኑ ቁጥር በዐሥራአንድ ሚሊዮን ተጨማሪ ተከታዮች አግኝቶ ታይቷል፡፡
በደርግ ጊዜ በተደረገው ቆጠራ በ1976ዓ.ም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ሕዝብ 54.02% ያህሉን ትይዝ ነበር፡፡ የመናፍቃኑ ደግሞ 6.46% ያህሉን ይይዝ ነበር፡፡ ይሄ አኀዝ ከዚያ በኋላ በተደረጉት ሁለት የወያኔ ዘመን ቆጠራዎች በመናፍቃኑ የሚወሰደው ሰው እጥፍ እጥፍ እየጨመረ መጥቶ በ1998ዓ.ም. ላይ መናፍቃኑ 19.2% ሲያሻቅቡ የእኛ ደግሞ ወደ 43.5% አሽቆልቁሏል፡፡ የዚህን ሬሾ ይዘን ስናሰላ በዘንድሮው ቆጠራ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተከታይ ቁጥር ከ22-20% ድረስ በማሽቆልቆል በእጅጉ አስደንጋጭ የሆነ አኀዝ ይገኛል ተብሎ ሲገመት፡፡ ከዚህም ወርዶ ሊገኝ ይችላል፡፡ መናፍቃኑ ደግሞ 38% እና ከዚያም በላይ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡
ታች አምናም አቦይ ማትያስ የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ቤተክርስቲያኗ ይሄ ኪሳራ ሊደርስባት የቻለው ወያኔ “የአማራንና የኦርቶዶክስን አከርካሪ እንዳያንሰራራ አድርገን ሰብረናል!” እስከማለት ድረስ ያበቃውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ከመናፍቃንና ከአጽራረ ቤተክርስቲያን ጋር በመቀናጀት በቤተክርስቲያን ላይ ስለፈጸመባት ነው፡፡
በዚህም መሠረት የቤተክርስቲያኗ ተከታይ ቁጥር እጅግ አስደንጋጭ ስለሚሆንና ይሄም ቁጣን ሊቀሰቅስ ስለሚችል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ቁጥር ከሚገኘው ከትክክለኛው ቁጥር ተጨምሮበት ማጭበርበር እንደሚፈጸም ያለጥርጥር እጠብቃለሁ፡፡ እንግዲህ ሁሉንም የምናየው ይሆናል፡፡
ሲደመደም በአንድም በሌላም ምክንያት ትክክለኛው የቆጠራ ውጤት ይፋ እንደማይደረግና እንደሚጭበረበር ብናውቅም ለታሪክ ምስክር ይሆን ዘንድ የተጭበረበረውን ውጤትም ቢሆን እንፈልገዋለንና ውጤቱን በጉጉት እንጠብቃለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com
