February 15,2019

ራስ አሉላ እንግዳ ( አሉላ አባ ነጋ) ” አባ ነጋ አሉላ ካሥመራ ቢነሳ እንዳንበሳ ሆኖ እሳት እያገሳ የችግር ምስጋና ባይነሳ ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ”

No photo description available.

 ራስ አሉላ በ1847 በተምቤን ዙቁሊ ሚካኤል እንደተወለዱ ማሞ ውድነህ በ1987 የዶጋሊ ጦርነትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት በተዘጋጀው ልዩ የመታሰቢያ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ ይገልፃሉ፡፡ በጊዜዉ የሚሠጠዉን ትምህርትም በዙቁሊ ሚካኤልም ከመምህር ወልደጊዮርጊስ እንደተማሩ ማሞ በጽሁፋቸዉ ገልፀዋል፡፡

አሉላ ወዲ ቁቢ የጉርምስና ጊዜያቸዉን በአጼ ዮሐንስ አጎት በራስ አርአያ ድምፁ ቤት አሽከር በመሆን እንደጀመሩ ንጉሴ አየለ (ፕ/ር) “Ras Alula and Ethiopia’s Struggle Against Expansionism and Colonialism 1872-1897” በተሰኘ መጣጥፋቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕ/ር ንጉሴ ገለፃ ራስ አሉላ በስተኋላ ወደ ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ (ኋላ አፄ ዮሐንስ ፬ተኛ) ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሹመትን በሹመት በመደረብ ወደፊት ገሰገሱ፡፡ በመጀመሪያ እልፍኝ አስከልካይ ቀጥሎም አጋፋሪነትን ተሾሙ፡፡

በ1873 ደጃዝማች ካሳ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ሲባሉ አሉላ የሻለቅነትን ማዕረግና የንጉሱ ሊጋባነት ማዕረግን ደርበው ያዙ፡፡ አሉላ ወዲ ቁቢ ሁለንተናቸው ስሁል፣ ንቁ እና አርቆ አሳቢ እንደነበሩ ብዙ ጸሐፊዎች፣በጦር ሜዳ ውሎ የሚያውቋቸው፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚውቋቸው ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሆነው ነገን የሚመረምሩ ከራስ በላይ ሀገርን የሚስቀድሙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ አሉላ ወዲ ቁቢ፡፡

መርዕድ ወልደ አረጋይ (ፕ/ር) “Alula, Dogali and Ethiopian Unity” በሚል ጽሁፋቸው ከአሳዛኙ የአፄ ቴዎድሮስ የመቅደላ ፍፃሜ በፊትም ሆነ በኋላ አፄ ቴዎድሮስን የመሰለ አንድ ሰው ቢኖር አሉላ አባ ነጋ ብቻ ናቸው ይላሉ፡፡ እንደ ፕ/ር መርዕድ ገለፃ ከሆነ ራስ አሉላ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በተክለ ሰውነት መመሳሰል ባለፈ በሰብዕና እና በአመለካከት እንዲሁም በአርቆ አሰተዋይነት እና በመንፈሳዊ ልዕልና ይመሳሰላሉ፡፡ ግብርን ለሀገር ጥንካሬ ከማዋል ባለፈ አንድ የጦር መሪ ከተራው ወታደር የተለየ መብላት እና መልበስ እንደሌለበትም ሁሉቱ የኢትዮጵያ ጅግኖች ተመሳስሎ እንደሆነ ፕ/ር መርዕድ ያስረዳሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማሞ ውድነህ “The Life and Works of Alula Aba Nega” በሚለው መጣጥፋቸው አሉላ ወዲ ቁቢ በ1847 እንደመወለዳቸው ስለ አፄ ቴዎድሮስ ጀግንነት እና ትልቅነት እየሰሙ ማደጋቸውን ያብራራሉ፡፡

ራስ አሉላ ከነበራቸው የጦር ብልሀት እና እንዲሁም ደግሞ የተዋጣለት ዲፕሎማት መሆን የተነሳ በአፄ ዮሐንስ ፊት ሞገስ እና ክብር ነበራቸው፡፡ ለዛም ነው ከአሽከርነት እስከ ራስነት ሹመት የደረሱት፡፡ በታሪክ ዘመናቸው በዋናነት ለአፄ ዮሐንስ የቀኝ እጅ በመሆን በወቅቱ ንጉሱን ከገጠማቸው የስልጣን ሽኩቻ በተለይ ከጎጃም እና ከሸዋ ከማደላደል ባሻገር ከሶስት ዋና ዋና የኢትዮጵያ የወቅቱ ጠላቶች ጋር ተዋግተዋል፡፡ ከህዳር 16 ቀን 1875 ከተደረገው የጉንደት ጦርነት እስከ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ/ም እስከተደረገው የዓድዋ ጦርነት ድረስ ራስ አሉላ አባ ነጋ አስራ ሁለት ጦርነቶችን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር የተዋጉ ሲሆን በዋናነትም ከኦቶማን ግብጽ ተስፋፊዎች፣ ከማህዲስት የድርቡሽ ወራሪዎች እና ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር ያደረጓቸው ናቸው፡፡ ስለ ራስ አሉላ አባ ነጋ ጀግንነት በርካታ ጸሐፍት ብዙ ብለዋል።

ከነዚህ መካከል ኢጣሊያዊው ተርጋሊኖ ጋንዶልዬ ጽፎት በማሞ ውድነህ በተተረጎመው ” አሉላ አባ ነጋና የኢጣሊያ ሰላዮች” በተሰኘው ፅሁፍ ይህን ማራኪ የራስ አሉላ ቃል እናገኛለን… ” የኢትዮጵያን ወታደሮች አታውቃቸውም? እንደ ወፍ ይበራሉ! እንደሰስ ይሮጣሉ ወደ ጠላታቸው ምሽግ ለመገስገስ ከቶ አያመነቱም። እውነተኛውን የጀግንነት ሙያ በእውነተኛው ቦታ ላይ ያሳያሉ፤ ያስመሰክራሉ። ተራራና ገደል ወንዝና አሸዋ አያግዳቸውም። በመሬት ላይ ምን ቢሆን የእነርሱን ብርታት የሚፈታ ችግር የለም….” ልክ በዛሬው እለት በ1889 ዓ.ም በተወለዱ በሰባ አመታቸው አርፈው ዓድዋ በሚገኘው አባ ገሪማ ገዳም ተቀበሩ። የጣሊያን ጋዜጣም “ጎራዴውን ወደ እኛ እንደመዘዘ ወደአፎቱ ሳይመልሰው አሉላ ሞተ” ብሎ ዘገበ።

ከእረፍታቸው በኋላም ህዝብ እንዲህ ሲል አንጎራጉሯል

እነዚህ ጣልያኖች እጅግ ተደሰቱ

የአሉላ ጎራዴ ሲበርድ ስለቱ

በሮም አደባባይ መድፍ ተተኮሰ

ምጽዋም ተሰምቶ መድፍ ተተኮሰ

አሥመራም ተሰምቶ መድፍ ተተኮሰ

የተደአሊ ደሙን ብድሩን መለሰ

ዓድዋ ያረረውን አንጀቱን አራሰ

አሉላ አባነጋ ክንዱን ተንተራሰ

ጣልያን እልል አለ የልቡ ደረሰ።