February 16, 2019

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ባልነበረበት ምን አልባትም ተሰምቶ በማያቅበት ከዚህ አለፍ ካለም ፈላጭ ቆራጭ ስርዓት በነገሰበት ከዛሬ መቶ ምናምን አመት በፊት ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነው አማርኛ አገራዊም የስራም ቋንቋ ሆኖ እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ጥቅም ላይ ውሏል። ይህ ጉዳይ አሁን ባለንበት ዘመን መስፈርት ሲለካ መሆን ያልነበረበት የታሪክ አጋጣሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይሁን እንጅ መሆን ባልነበረበት መንገድ ሄዶም ቢሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በአማርኛ ቋንቋ መግባባት ስለሚችል በብዙ ሰዎች “የጨቋኞች ቋንቋ” ነው እየተባለ ቢወቀስም በታሪክ አጋጣሚ የሆነ ክስተት ነውና በ1985 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ ህገመንግስትም የፌዴራል የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል እውቅና ተሰጥቶታል። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ክልሎችም ቢሆኑ አማርኛ የስራ ቋንቋቸው እንዲሆን ወስነው እየተጠቀሙበት ነው። ለነገሩ በአለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም ከዚህ ውጭ ሊሆን የሚችልበት የተሻለ መንገድ የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ባለንበት ወቅት ደግሞዘመኑ የኛ ነውየሚሉ ሰዎች ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ካልሆነ ወየውላችሁ እያሉ ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይሁን ሲሉ መከራከሪያ አድርገው እያቀረቡ ያሉት አብላጫ (Majority) ስለሆንን የሚል ነው። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እርስ በርሳቸው ሲነፃፀሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በዛ ያለ ቁጥር አላቸው የሚል እንጅ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ አብላጫነት አላቸው ማለት አይደለም። አንድ ህዝብ ወይም ቡድን ወይም ስብስብ አብላጫነት አለው ሊባል የሚችለው ቢያንስ 50+1 በላይ ቁጥር ሲኖረው ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ኦሮምኛ ተናጋሪው ህዝብበኢትዮጵያ አብላጫነት ያለው አይደለም። ስለዚህ ኦሮምኛ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ የመሆን አውቶማቲክ (Automatic) የሆነ መብት የለውም።

በርግጥ ጥያቄው እንደጥያቄ መቅረቡ በራሱ ችግር አይደለም። እንዲያውም ዴሞክራሲያዊ መብት ስለሆነ ሊበረታታ ይገባዋል ባይ ነኝ። በሌላ በኩል ይህ ከሌሎቹ ጋ በተነጣጣይ ሲነፃፀር በዛ ያለ ቁጥር ያለው ህዝብ መግባቢያ የሆነው ኦሮምኛ ቀርቶ አቅም ከፈቀደ ሌሎችም ቋንቋዎች የፌዴራሉ መንግስት የስራ ቋንቋ ቢሆኑ ህዝብ ለህዝብ ያስተሳስሩ እንደሆነ እንጅ የሚያስከትሉት ጉዳት ብዙም አይታየኝም። የእኔ ዋነኛ ተቃውሞ ያለው የትኛውም አይነት ቋንቋ  “ዘመኑ የኔ ነው” እያለ የሚያስብ ሃይል ስለፈለገ ብቻ በአዋጅ በሌላው ህዝብ ላይ ሊጫን አይገባም የሚል ነው። ይህ መሆን የለበትም የምለው ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊ፣ አምባገነናዊና  ማን አለብኝነት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን አላዋቂነትና ከመቶ አመት በፊት የነበረ አስተሳሰብ  እንዲሁም ያለንበትን የ21ኛው ክፍለ ዘመን አይመጥንም ወይም አይዋጅም  ብየ ስለማስብ ነው።

በእኔ እምነት ጉዳዩ በጣም ስስና (Sensitive) የዜጎችን መብት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚነካ ስለሆን እጅግ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው። በመሆኑም የሃገሪቱ ሉዓላዊ ስልጣን (Sovereignty) ባለቤት የሆኑት ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሊሳተፉበት የግድ ይላል። ይህን ማድረግ የሚቻለው በቀጥታ በሚካሄድ የህዝብ ውሳኔ (Referendum) ነው። የህዝብ ውሳኔው ተዓማኒነት ሊኖረው የሚችለው ደግሞ በሚቀጥለው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተወዳድሮ በሚመጣ መንግስት ሲሆን ነው። ይህ ሲሆን አንድም ህዝብ በመንገስት ላይ አመኔታ ያሳድራል። ሁለተኛ ህዝብ ለህዝብ እንዲቀራረብና እንዲተማመን ስለሚያደርግ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን በአብላጫ ድምፅ የሚመረጠውን ቋንቋ የመማር ፍላጎት ያነሳሳል። በዚህ ረገድ ያለፍላጎት እንዲላስ የተደረገ ማር እንደ እሬት የሚቆጠር መሆኑን ማስታወስ ይበጃል።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በዜጎች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት እየፈጠረ ያለው የፌዴራል የስራ ቋንቋ የመሆን ጥያቄ ብቻ አይደለም።  የባንዴራና የፌዴራል መንግስቱ በማንነት ላይ ተመስርቶ የተዋቀረው አስተዳደር (አንቀፅ ሰላሳ ዘጠኝን ጨምሮ) ጎራ አስለይተው እያቧቀሱ የሚገኙ ምናልባትም ለአገር አንድነት አደጋ እየሆኑ ያሉ አንገብጋቢ ችግሮች ሆነዋል። ስለዚህ የባንዴራና የፌዴራል መንግስቱን አወቃቀር በተመለከተ ልክ እንደ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ የመሆን ጥያቄ ሁሉ ነፃ፣ ግልፅና አሳታፊ ሆኖ በሚካሄድ  የህዝብ ውሳኔ (Referendum)  ሊፈቱ ይገባቸዋል። ባጠቃላይ ከዚህ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ከሆነው የህዝብ ድምፅ/ውሳኔ ውጭ ያሉ መንገዶች ሁሉ አሁን ያለንበትን ዘመን የማይመጥኑ አጥፊ መንገዶች ስለሆኑ ባይሞከሩ ይሻላል ባይ ነኝ።