February 16, 2019

መጋቢት 29 4ኛው ዙር የህዝብና ቤት ቆጠራ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ግን ቆጠራዉ የሚደረገው ከዚህ በፊት በነበሩ ካድሬ ሰራተኞችና በፊት በነበረበው ግልጽነት በሌለውና ፖለቲካዊ በሆነ አሰራር ነው።
እንግዲህ በሚከተሉት አምስት ነጥቦች የሕዝብ ቆጠራው እንዲራዘም እጠይቃለሁ።
አንደኛ – የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይኽው ስልጣን ከያዘ አንድ አመት ሊሞላው ቢሆንም፣ ሕግና ስርዓትን ማስጠበቅ አልቻለም። በብዙ የአገሪቷ ክፍል ዜጎች በነጻነት መንቀሳቀስ አይችሉም። ከሚናገሩትና ቋንቋና ከብሄረሰባቸው የተነሳ አንገታቸውን የደፉበት፣ የሚፈናቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው። በኦሮሞ ክልል ምን አልባት እንደ አዳማ ካሉ አካባቢዎች ውጭ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይችላል፣ ከኦሮሞዎችና ከኦሮሞ ቡድኖች ውጭ መንቀሳቀስ ማንም አይችልም። ጽንፈኛ ቄሮዎች በየደጃፉ እያሉ፣ እንደ ኦነግ ያሉ ቡድኖችና ታጣቂዎች ህዝቡን እያሸበሩ፣ እንዴት ተደርግ ነው ቆጠራ ሊደረግ የሚችለው? በትግራይ አሁንም ሕወሃት ነው ያለችው። ወልቃይት ጠገዴጋና ራያ ሕዝቡ ትግሬ ነኝ ብሎ ፎርም ላይ ካልሞላ ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ሕዝብን ያፈና የክልል፣ የዞንና የወረዳ መንግስታት ባሉበት ሁኔታ የሚደረግ ቂጠራ እንዴት ነሳና ፍትሃዊ ሊሆን ይችላል። በአማራ ክልል በጎንደር ቅማንት፣ አማራ እየተባለ የለየለት ጦርነት ነው ያለው። ከሰማኒያ ሺህ በላይ የጎንደር ነዋሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለዋል።
ሁለተኛ – የሕዝብ ቆጠራዉን የሚያደርገው የስታቲስቲክ ኤጀንሲ ገለልተኛ በሆነ መልኩ አልተዋቀረም። አሰራሩ ከዚህ በፊት የነበረው ፖለቲካዊ አሰራር ነው። በተለይም ለፖለቲካ ተብሎ ሆን ተብሎ የሕብረ ብሄራዊው የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጓል። የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር ቀንሷል።
ተቋሙ ሳይሻሻል፣ ብቃት ያላቸው፣ ገለልተኛ የሆኑ ባለሞያዎች ሳይካተቱ፣ የኢሕአዴግ አባላት በሆኑ በሰራተኞች ቆጠራውን ማካሄድ ከወዲሁ የቆጠራውን ውጤት ጥላሸት መቀባት ነው። ሃያ አባላት ያሉት የሕዝብ ቆጠራ አማካሪ ካዉንስል ተቋቁሟል። ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልል መስተዳድሮችና ከፌዴራሽን ምክር ቤት የተወጣጡ አባላት ናቸው። ሁሉም በኢሕአዴግ ስር ካልይ ተቋማት።
ሶስተኛ – ለሕዝብ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ይፋ አልሆኑም። ሕዝብ አልመከረባቸውም። አስተያየት አስልተሰጠባቸውም። ለምሳሌ “ብሄር” የሚሉትን ሲጠይቁ፣ አንድ ሰው “ብሄሩ” የሚለካው በምን መስፈርት ነው? ለምሳሌ አንድ ሰው ኦሮሞ ነኝ ሲል፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ በመሆኑ ነው? በኦሮሞ ክልል በመወለዱ ነው? እናቱ ወይንም አባቱ ኦሮሞ ስለሆኑ ነው? ወይንስ ራሱን ኦሮሞ ብሎ ስለሚጠራ? መመዘኛው ግልጽ ባልሆነት ጥያቄዎች መጠየቅ ስቸጋሪ ነው።
አንድ ሰው “እኔ ኦሮሞ ነኝ” ስላለ “ኦሮሞ” ተብሎ የሚመዘገብ ከሆነ ፣ የዚያን ሰው ማንነት በትክክል ያንጸባርቃል ማለት አይደለም። የኦሮሞ ክልል አፓርታይዳዊ ክልል እንደመሆኑ፣ አንድ ዜጋ ኦሮሞ ነኝ ካላለ ሁለተኛ ዜጋ፣ መጤ ተደርጎ ነው የሚታይበት፣ ለመኖር ሲል ኦሮሞ ባይሆንም፣ ወይም በአባት ኦሮሞ በ እናት ሌላ ቢሆንም ፣ ኦሮሞ ነኝ ነው የሚለው። ከላይ እንደጠቀስኩት፣ በትግራይ ትግሬ ነን ካላሉ ዋጋ ስለሚከፍሉ፣ ትግሬ ባይሆኑም ዜጎች ትግሬ ነን ይላሉ። በዚህ መልኩ በተጽእኖ ዜጎች ያልሆኑትን ነን የሚሉበት ሁኔታ ይኖራል። ስለዚህ መመዘኛ በሌለበት “ብሄር፡ የሚሉትን መጠየቅ ሳይንሳዊ አይደለም።
በኔ እይታ “ብሄር” የሚለው ጥያቄ መሰረዝ ያለበት ጥያቄ ነው። ትርጉሙ አሻሚ ስለሆነና ትክክለኛዉን የዜችን ማንነት ገላዥ ባለመሆኑ።
የሚሻለው፣ ሳይንሳዊም የሆነው፣ ዜጎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውንና በተደራቢነት የሚናገሩትን ቋንቋ ከተጠየቀ በቂ ነው ባይ ነኝ። በመጠየቅ እንደ አካባቢው፣ አስፈላጊዉን አገልግሎት በአፍ መፍጫ ቋንቋቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
አራተኛ – የሕዝብ ቆጠራ ውጤት እንደሚደረግ፣ ኢትዮጵያዉያን የመንግስት ሰራተኞች ፎርም ለማስሞላት ቤታቸው በሚመጡበት ጊዜ ፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ ያለቸውንም መብት እንዲያዉቁ በቂ ቅስቀሳ አልተደረገም። ለተወሰኑ ወራት ትልቅ የሕዝብ ግንኙነት ስራ መሰራት ያለበት መሰለኝ።
አምስተኛ – በቆጠራ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ማጭበርበሮችን፣ ኦዲት የሚያደርግ ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም። ለምሳሌ ከላይ እንደገለጽኩት፣ በኦሮሞ ክልል ካለው አለመረጋጋት የተነሳ፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ አልተቻለም። ስለዚህ ኦሮሞ ያልሆኑ የስታቲስቲክ ኤጀንሲ ሰራተኞች፣ በኦሮሞ ክልል ያለ ምንም ችግር መስራትና መንቀሳቀስ አይችሉም። ማንን ተማምነው ነው ለምሳሌ ጽንፈኛ ቄሮዎች ባሉበት በምእራብ አርሲ፣ በሃረርጌ፣ ኦነጎች ባሉበት በቀሌምና ሆሩ ጉርዱ፣ ምእራብ ወለጋ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ሄደው ፎርም የሚያስሞሉት?
በኔ እይታ የሕዝብ ቆጠራው ከላይ የተቀመጡት መሰረታዊ ችግሮች እስኪስተካለሉ ድረስ መራዘም አለበት አይ ነኝ። የዶ/ር አብይ አስተዳደር ለፖለቲካ ፣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ ቆጠራው ለማድረግ ቢጣደፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚበልጥ ከወዲሁ ማሳሰብ እወዳለሁ። የሕዝብ ቆጠራ ውጤት የፖለቲካ ዉክልናን የሚወስን እንደመሆኑ ፣ ያንን ሂደት ፍትሃዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ካልተቻለ፣ በዚህ ቁጠራ መሰረት የሚመጣም የፖለቲካ ዉክልና ስልጣን ተቀባይነት አይኖረውም። ከጋሪው በፊት ፈርሱ መቅደም አለበት።