February 14, 2019

ዶ/ር መለሰ_መኮንን፣ የደሴ ከንቲባ ናቸው። “ላለፉት 27 አመታት ደሴ ከተማ ላይ ምንም አይነት የመንግስት መስሪያቤት አልተገነባም !በንጉሱ እና በደርግ ግዜ የተሰሩ ያረጁ ህንፃዎች ናቸው አገልግሎት እስከ አሁን እየሰጡ ያሉት ተገነባ ከተባለ የብአዴን/አዴፓ/ ህንፃ ብቻ ነው” ይላሉ።

ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ጽፊያለሁ። የአማራ ክልል ሰፊ ክልል ነው። ለአስተዳደር አያመችም። የክሉ መንግስት ባህር ዳርና ባህር ዳር አካባቢን ከማስደግ ውጭ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎⶭ ይሄን አድርጓል ማለት አይቻልም። እነ ሸዋ፣ እነ ወሎ …በአማራ ክልል ተረስተዋል።

ህዝቡ የአስተዳደር አገልግሎት ፍለጋ ከአንኮበር ደብረብርሃኑ እያለለት፣ ከአብርሃጂራ ጎንደር እያለለት፣ ከሃይቅ ደሴ እያለለት ባህር ዳር የሚመጣበት ምንም ምክንያት የለም።

ክልሉ ፈርሶ ሸዋ፣ ጎንደር፣ ወሎና ጎጃም በሚሉ ፌዴራል መስተዳደሮች ቢቀየር እነ ደሴ፣ እነ ጎንደር፣ እነ ደብረብርሃን እነ ደብረ ማርቆስ ያድጋሉ። ለአስተዳደር አመችድ ነው። ህዝብ አይጉላላም።

ያ ብቻ አይደለም ይሄ የአማራ ክልል የሚለውም ዘላቂ ሰላምም ለማምጣት አስቸጋሪ ነው። የጎንደር መስተዳደር ቢኖር አማራ፣ ቅማንት፣ ትግሬ ብሎ ነገር አይኖርም። ወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራ ጠለምት ወደ ጎንደር ለመቀላቀል ይመቻል። ለምን ወልቃይት ጠገዴ መቼም የአማራ ክልል ሆኖ አያውቅም፤ ለምን የአማራ ክልል የመጣው አሁን ነዉና። ግን የጎንደር ክፍለ ሃገር አካል ነበር። ስለዚህ የታሪክ መከራከሪያ እናቅርብ ብንልም የአማራ ክልል ነበር ማለት አንችልም።

ስለዚህ በሁሉም መስፈርት፣ የዘር አከላለል መፍረስ አለበት።