Source: https://mereja.com/amharic/v2/93639
– ባህልና ቋንቋን የሥልጣን መስፈርያ ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው
– የበዳይ ተበዳይ ታሪክ ማራገቡ ጠቃሚ አይደለም
– ታሪክን እንደ ትዝታ ማየት መልመድ አለብን

አንዳንድ የኢትዮጵያ ልሂቃን ታሪክን የውዝግብና የግጭት ምንጭ በማድረግ ረገድ ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕ/ር አህመድ ዘካሪያስ፤ ታሪክ እውቀት እንጂ እምነት መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ምን ማለት ናቸው? ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በታሪክ ዙሪያ ሰፊ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ እነሆ፡
የዛሬው የኢትዮጵያ ቅርፅ እንዴት መጣ?
በአጠቃላይ ዛሬ የምናየው የኢትዮጵያ ቅርፅ እንዴት መጣ የሚለው በአግባቡ መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አፍሪካን ቅኝ ገዥዎች ሲቀራመቷት፣ ድንበር ገፍተው ገፍተው፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ቅርፅ አበጁልን፡፡ ይሄ ውጫዊ ማለትም፣ እኛ ፈልገን ያመጣነው ቅርፅ አይደለም፡፡ እኛ ያመጣነው ከመንደር ወደ ትልቅ የተጠናከረ ሃገርነት የመለወጥን ቅርጽ ነው፡፡ ትልቅ ኢምፓየር የመሆን ጉዳይ፣ በኛ ህልም የመጣ ነው፡፡ የግዛት መሳሪያ መሬት ነው፡፡ አቅም ያለው በየጊዜው መሬቱን ያሰፋ ነበር፡፡ ጠመንጃን ቀድሞ ያገኘና የሰው ኃይሉ የተደራጀ፣ በየትኛውም ዓለም ከሱ በጉልበት አናሳ የሆነውን ሲያጠቃልል ነው የኖረው፡፡ የአብዛኞቹ የዓለም ሃገራት አመሰራረት ከዚህ እውነት የራቀ አይደለም፡፡ አሁን ምናልባት የመረጃና የስልጣኔ ዘመን ነው፤ ይህ አይነቱ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ቀድሞ ግን ጠመንጃ የያዘ አካል ድምፁም ዝናውም ያስፈራራል፡፡ ዓለም ራሷ የሰፋችው ጠመንጃና ቀድሞ ቴክኖሎጂ በእጃቸው የደረሰ ኃይሎች፤አዲስ አለም ለማሰስ ባደረጉት ጥረት ነው፡፡ ነገሩን ሰፋ አድርገን ማየት አለብን፡፡ ሁሉም ተጣልቶ፣ ተዋግቶ፣ ተላልቆ፣