February 17, 2019t


በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄውን በማቅረቡ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቦታው እንደሚንቀሳቀሱ ተገለጸ።

የጸጥታ ችግሮችን አስመልክቶ የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አለምነው አየነ እና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዋነኝነት ግጭቱን ለመቆጣጠር ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ እና የጸጥታው ችግር ከመሻሻል ይልቅ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ተጨማሪ ሃይል አስፈልጓል ብለዋል በመግለጫቸው።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄውን ማቅረቡን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቦታው እንደሚንቀሳቀሱ ተገልጿል።

በተጨማሪም በዋነኝነት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከክልሉ ፖሊስ አባላት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር የሚገኙ ሚሊሻዎች በፌደራል መንግሥት እና በክልሉ መንግሥት እገዛ ካልተጠየቁ በስተቀር ማንኛውንም መሳሪያ ይዞ መዘዋወር እንደማይፈቀድላቸ ተገልጿል።

ከጎንደር-መተማ መስመር ፣ ከጎንደር ሑመራ መስመር ከመንገድ ግራ እና ቀኝ እስከ 5 ኪ.ሜ ክልል በቡድን ሆኖ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል።

በዋነኝነት ማሕበረሰቡ ለፌደራል ፖሊስ እና ለመከላከያ ፖሊስ አባላት ተገቢውን ትብብር በማድረግ በአካባቢው እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ችግር እንዲፈታ ጥሪ ቀርቧል።

በተስፋዬ ጫኔ